ስደተኞችን የሚመለከተው የአውሮጳ ህብረት እቅድ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 23.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ስደተኞችን የሚመለከተው የአውሮጳ ህብረት እቅድ

የአዉሮጳ ሕብረት እና የቱርክ ባለሥልጣናት ስደተኞች በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አህጉሩ እንዳይገቡ ለማከላከል እንዲያስችላቸው ባለፈው ሳምንት የደረሱት ስምምነት ተግባራዊ ሆኖዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:04
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:04 ደቂቃ

አውሮጳ እና ስደተኞች

ይሁን እንጂ፣ ካለፈው እሁድ ወዲህ ወደ ግሪክ የገቡትን ስደተኞች ወደ ቱርክ የመመለሱ ርምጃ ገና አልተጀመረም። ሆኖም፣ የዶይቸ ቬለ ዘጋቢ ቤርንት ሪገርት እንደሚለው፣ የአውሮጳ ህብረት ይህን ለማሳካት የሚያስችለው «ጥሩ» የሚለውን እቅድ አዘጋጅቶዋል።
የአውሮጳ ህብረት እና ቱርክ በደረሱት ስምምነት መሰረት፣ ህብረቱ ወደ አህጉሩ ለመግባት ወደ ግሪክ የሚመጡትን አዳዲስ ስደተኞች ወደ ቱርክ ይመልሳል፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ቱርክ የሚገኙትን የሶርያ ስደተኞች ወደ አውሮጳ በማምጣት ያሰፍራል። ይሁንና፣ ከቱርክ ተጨማሪ ስደተኞች ወደ አውሮጳ መምጣት በቀጠሉበት ባሁኑ ጊዜ ካለፈው እሁድ ወዲህ ተግባራዊ የሆነው ስምምነት በርግጥ ስራ ላይ ሊውል መቻሉን የሚጠራጠሩት አልጠፉም። ይሁንና፣ ህብረቱ በስምምነቱ የሰፈረውን እውን ለማድረግ ጥረቱን መቀጠሉን የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ቃል አቀባይ ማርጋሪቲስ ሺናስ በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።
« የስምምነቱ ተግባራዊነት እንዲሳካ መስራት አለብን፣ እየሰራንም ነው፣ ምክንያቱም የ28 አባል ሀገራት ርዕሳነ ብሔር እና መራሕያነ መንግሥት ውሳኔ ነው። በዚሁ አኳያ አስተያየት ለመስጠትም ሆነ ለምታቀርቡዋቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ጊዜ የለንም። »


ወደ ግሪክ የሚመጡት ስደተኞች ጉዳያቸው በነፍስ ወከፍ በተገቢው መንገድ ሊታይላቸው ይገባል፣ ግን ይኸው ሂደት ግሪክ ውስጥ ከብዙ ዓመታት ጀምሮ አልነበረም፣ አሁንም የለም። በዚህም የተነሳ፣ የኮሚሽኑ ፕሬዚደንት ዦን ክሎድ ዩንከር ስደተኞቹ ባፋጣኝ ወደ ቱርክ የሚመለሱበትን ቀላል ያልሆነ ጉዳይ እንዲያፋጥኑ እና በቅርብ እንዲከታተሉ እስካሁን በግሪክ የስደተኞች ምዝገባ ማዕከላትን ሲመሩ የቆዩትን ከፍተኛ የኮሚሽኑን ባለስልጣን ማርተን ፈርቬን ልዩ ልዑክ አድርገው ሾመዋል። ለዚሁ ተግባራቸውም ማሳኪያም ከሀያ የህብረቱ ሀገራት የሚውጣጡ ተጨማሪ ቢያንስ 2,500 ሰራተኞችን ለማቅረብ እቅድ መያዙን የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ናታሻ ቤርትሯ ገልጸዋል።
« ሀሳቡ ሰራተኞችን በተቻለ ፍጥነት በግሪክ ደሴቶች ማሰማራት ነው። ባለፈው ዓርብ በደረስነው ስምምነትም የመጀመሪያው ስምሪት የፊታችን መጋቢት 28፣ 2016 ዓም ነው ገሀድ የሚሆነው። »
ስደተኞችን የመመዝገቡ ስራ እንደበዛባት ከማሳወቅ ወደ ኋላ ያላለችው ግሪክ 1,500 የመንግሥት ሰራተኞችን እና የሕግ ባለሙያዎችን ታቀርባለች። የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በስብሰባው እንዳስታወቁት፣ የመጀመሪያዎቹ የአውሮጳ ህብረት ሰራተኞች ግሪክ ከገቡ ከአንድ ሳምንት በኋላ ፣ ሚያዝያ አራት፣ 2016 ዓም የመጀመሪያዎቹ ስደተኞቹን የመመለሱ ሂደት ይጀመራል። ይህ እንደተጀመረም ከቱርክ ሶርያውያኑን ስደተኞች ወደ አውሮጳ የማምጣቱ ሂደት ይነቃቃል። በወቅቱ 18,000 ክፍት ቦታዎች ሲኖሩ፣ ተጨማሪ 54,000 ያስፈልጋሉ፣ ይህን ለማሟላት ግን በአውሮጳ ህብረት ውስጥ አዲስ ሕግ መውጣት እንደሚኖርበት ኮሚሽኑ በማስታወቅ፣ ኮሚሽኑ የህብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች ከቱርክ 72,000 ሶርያውያን ስደተኞችን በአውሮጳ ለማስፈር ያስቀመጡትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በወቅቱ በመነጋገር ላይ መሆኑን አመልክቶዋል። ይሁንና፣ ከግሪክ የሚመለሱት ስደተኞች ቁጥር አነስተኛ ስለሚሆን መሪዎቹ በአህጉራቸው ለማስፈር ያስቀመጡት ቁጥር የሚደረስበት እንደማይመስል የህብረቱ ዲፕሎማቶች ገምተዋል። እንደነርሱ አስተያየት፣ የአውሮጳ ህብረት እና ቱርክ ስምምነት ዋነኛ ዓላማ አዳዲስ ስደተኞች ቢመጡም ተመላሽ ስለሚሆኑ እንዳይመጡ ለማከላከል የታሰበ ነው። በዚህ ሁሉ መሀል፣ ግራ እያጋባ ያለው ነገር፣ በአዲሱ የአውሮጳ ህብረት እና ቱርክ ስምምነት ውስጥ ጉዳያቸው ያልተነሳው አሁን በግሪክ የኢዶሜኒ ደሴት የሚገኙት 50,000 ስደተኞች እጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን በግልጽ አልታወቀም።

ቤርንት ሪገርት/አርያም ተክሌ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic