1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደተኞችን ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለ መመሪያ ተዘጋጀ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 3 2016

ኢትዮጵያ ውስጥ እውቅና ያገኙ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሥራ መቀጠር የሚችሉበት እና ፍቃድ አውጥተው በንግድ ሥራ መሰማራት የሚችሉበት መመሪያ ተዘጋጀ።

https://p.dw.com/p/4i7At
መተማ የተጠለሉ የሱዳን ስደተኞች
ምዕራብ ኢትዮጵያ መተማ የተጠለሉ የሱዳን ስደተኞች። ምስል Amanuel Sileshi/AFP

ስደተኞችን የተመለከተው መመሪያ


 ስደተኞች በሥራ የሚሰማሩበትን ሁኔታ ለመወሰን ቀደም ብሎ የወጣው የአሠራር መመርያ ቁጥር 02/2012 በሥራ ላይ ቢሆንም፣ ስደተኞቹ እንዲያገኟቸው በአዋጅ የተደነገጉ መብቶችን ባለማካተቱ «እዉቅና ያገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሥራ መብት አፈጻጸም» የተባለ አዲስ  መመሪያ መዘጋጀቱን የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት አስታውቋል። ረቂቅ መመሪያው እውቅና ያገኙ ስደተኞች ወይም ጥገኝነት ጠያቂዎች የሥራ ፈቃድ ማውጣት ሳያስፈልጋቸው ተቀጥረው መስራት እንደሚችሉ፣ ስደተኛው ከኢትዮጵያዊ ዜጋ ጋር ሕጋዊ ጋብቻ የፈፀመ ወይም አንድና ከአንድ በላይ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው ልጆች ያለው ከሆነ የዚህ መብት ተጠቃሚ ይሆናል ይላል።

የረቂቅ መመሪያው ይዘት እና አዳዲስ ድንጋጌዎች

እውቅና ያገኙ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች እንዲሁም የተቀባይ ማኅበረሰቦች የኑሮ ሁኔታቸው እንዲሻሻል የስደተኞችን የመሥራት መብት ለማስፈፀም «ስደተኞች በሥራ ላይ የሚሰማሩበትን ሁኔታ ለመወሰን መመሪያ ቁጥር 2/2012» ተዘጋጅቶ በመተግበር ላይ ቢሆንም፣ በስደተኞች አዋጁ የተጠቀሱ መብቶችን በሙሉ የያዘ ሆኖ ባለመገኘቱ አዲስ መመርያ መዘጋጀቱን የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት አስታውቋል።

ይሄው መሥሪያ ከሚመለከታችው ተቋማት ጋር ያዘጋጀው መመርያ «እውቅና ላገኙ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ስለ ቅጥር ሥራ ፍቃድ፣ በንግድ ሥራ ስለመሰማራት እና ስለግብር ከፋይ መለያ ቁጥር» አወጣጥ በዝርዝር የሚገልጹ ድንጋጌዎችን እንዲሸፍን ተደርጓል። ስለ አዲሱ መመረያ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ የጠየቅናቸው የተቃሙ የኮሙኒኬሽን እና ውጫዊ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ በአካል ንጉሤ ከቀጠሩን በኋላ ስልካቸውን አያነሱም።

ለመመርያው መዘጋጀት መንግሥት እውቅና ያገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የመሥራት መብት እንዲኖራቸው በተለያዩ ጊዜያት ቃልኪዳኖችን የገባ በመሆኑ፤ የሀገሪቷ አቅም በሚፈቅደዉ መጠን የእነዚህን አካላት አያያዝ ለማሻሻል እና ለችግሮቻቸዉ ዘላቂ መፍትሓ እንዲያገኙ ለማስቻል የስደተኞች ጉዳይ የተመለከተ አዋጅ የወጣ በመሆኑ፤ እውቅና ያገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከተረጂነት ወጥተው ራሳቸውን የቻሉ እንዲሆኑ በሥራ ላይ መሰማራት እንዲችሉ በአዋጅ የተፈቀደላቸው በመሆኑ ነው ተብሏል። 

በአዲሱ መመርያ በስደተኞች አዋጅ ባልተከለከሉ የሥራ መስኮች ላይ ተቀጥሮ ለመሥራት የሚፈልግ ማንኛውም እውቅና ያገኘ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ፣ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ወይም ሕጋዊ ውክልና ከተሰጠው አካል የሥራ ፈቃድ ማውጣት ይችላል፣ በጠረፍ ንግድ እና ለዉጭ ሀገር ዜጎች የተሻለ መብት በሚሰጡ ሕጎች ለኢትዮጵያውያን ብቻ ከተፈቀዱ የንግድ መስኮች ውጭ መሰማራት ይችላል፣ በግል ወይም የንግድ ማኅበር አባል በመሆን በንግድ ሥራ ላይ መሰማራት ይችላል፣ ልዩ የእንደራሴ የምስክር ወረቀት አውጥቶ በንግድ እንደራሴነት መሥራት ይችላል፣ በንግድ ሥራ በመመዝገብ ከቻለም በንግድ ሥራ ላይ ለመሰማራት ይችላል ሲል ይደነግጋል።

በተመሳሳይ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ስምምነት መሰረት እዉቅና ያገኙ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከኢትዮጵያዉያን ጋር የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚሆኑበት የከተማ ወይም የገጠር ፕሮጀክት ውስጥ እንዲሳተፍ ከተመረጡ የሥራ ፈቃድ ማውጣት ሳያስፈልጋቸው ከአገልግሎቱ የመኖሪያ ፈቃድ በማግኘት ብቻ በጋራ ኘሮጀክት ላይ ለመሰማራት ይችላል ተብሏል። በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ዜጋ ጋር ሕጋዊ ጋብቻ የፈጸመ ወይም አንድና ከአንድ በላይ የኢትዮጵያ

ዜግነት ያላቸው ልጆች ያሉት ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ ይህንን የሚያረጋግጥ የድጋፍ ደብዳቤ ከአገልግሎቱ ከተሰጠው በጋራ ፕሮጀክት ለመሳተፍ የመኖሪያ ፍቃድ ማውጣት አያስፈልገውም የሚሉ መብት ሰጪ ድንጋጌዎች በመመርያው ተካተዋል።

የኤርትራ ስደተኞች በትግራይ
ትግራይ ውስጥ ትምግርታቸው ተከታትለው ለመመረቅ የበቁ የኤርትራ ስደተኞች።ፎቶ ከማኅደር ምስል Million Haileselasie/DW

ይሁንና ማንኛውም ዕውቅና ያገኘ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ የመኖሪያ ፈቃድ ማውጣት የሚችለው፤ በአንድ የጋራ ፕሮጀክት በመታቀፍ ለመሥራት የፕሮጀክቱን መስፈርት ሲያሟላ እና አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በሚያወጣው አሠራር መሠረት ሲመረጥ፣ ስደተኛው ወይም ጥገኝነት ጠያቂው ከፀጥታና ወንጀል ጋር በተያያዘ በመጣራት ወይም በክስ ሂደት ላይ አለመሆን አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ሲያረጋግጥ፣ የስደተኝነት ወይም ጥገኝነት እውቅና ከተሰጠው በኋላ ሦስት ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ በስደተኝነት የቆየ ከሆነ ብቻ ነው። ያም ሆኖ የመኖሪያ ፈቃድ የተሰጠው እውቅና ያገኘ ስደተኛ ያለ መንቀሳቀሻ ፈቃድ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር እንዲሁም የመኖሪያ ፈቃዱን ባገኘበት የጋራ ፕሮጀክት ውስጥ የመስራት መብት ይኖረዋል፡፡

የኢሰመኮ የዘርፍ ዘገባና ጥሪ 

የኢትዮጵያሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከወራት በፊት ባወጣው የሁለት ዓመታት የዘርፉ ዘገባ ከስደተኞች ምዝገባ እንዲሁም ሰነድ የማግኘት መብት ጋር ተያይዞ በሚታዩ ችግሮች ምክንያት ስደተኞች ለተለያዩ የመብት ጥሰቶች ይጋለጣሉ ብሎ ነበር። በተለይ ያልተመዘገቡ ስደተኞች እና ከለላ ጠያቂዎች ምዝገባ ካቆመ ሦስት አመት በማለፉ ማኅበራዊ አገልግሎት ለማግኘት ሲቸገሩ መስተዋሉ ይነገራል። መታወቂያ ያገኙትም ቢሆን ሰነዳቸው በየጊዜው ባለመታደሱ ችግር ሲደርስባቸው ይታያል። የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የዘርፍ ሪፖርቱ በወጣበት ወቅት ለዶቼ ቬለ ይህንን ብለው ነበር።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኢትዮጵያ ውስጥ 1 ሚሊየን 51 ሺህ ስደተኞች እንደሚኖሩ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንን ጠቅሶ ባለፈው ሳምንት ባወጣው ዓመታዊ ዘገባ አስታውቋል። ከእነዚህም ውስጥ 78, 293 ያህሉ በአዲስ አበባ ከመጠለያ ጣቢያ ውጪ የሚኖሩ ፍቃድ ያገኙ ስደተኞች ናቸው ብሏል። ይህ የተዘጋጀው አዲስ መመርያ በዋናነት በከተማ ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞችን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ