ስደተኞችና የዕርዳታ ችግር | ዓለም | DW | 17.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ስደተኞችና የዕርዳታ ችግር

እንግሊዞች በጉልበትም፤ በስብከትም፤ በብልጠትም፤ በስደትም እያሉ-ከአዉትሬሌያ እስከ ካናዳ፤ ከኒዉዚላንድ እስከ ናጄሪያ፤ ከዩናይትድ ስቴትስ እስከ ደቡብ አፍሪቃ፤ ከፎክላንድ ደሴቶች እስከ ኬንያ ወደ ገሚስ ዓለም ተሰደዉ፤ብዙ ሐገር-ሐገራቸዉ ሆኗልም።እንግሊዞች የተሰደዱ፤ የሠፈሩበት ሐገራት ሕዝብ ዛሬ ሲሰደድ ግን በራቸዉን ይከረችሙ ይዘዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:07

ስደተኞችና የዕርዳታ ችግር

የዩናይትድ ስቴትስ ወግ አጥባቂ (ሪፐብሊካን) ፖለቲከኞች የሠሞኑ ክርክር ኦባማን የሚተካዉ ፕሬዝደንት እግረኛ ጦር ወደ ሶሪያ ያዝምት-አያዝምት የሚል ነዉ።የዓለም አንደኛ ሐያል-ሐብታም ሐገር ከ2011 ጀምሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሶሪያን የሚነደዉን ጦርነት በቀጥታም፤ በተዘዋዋሪም በግንባር ቀደምትነት ታቀጣጥላለች።ጦርነቱ ያሰደደዉ ሶሪያዊ ቁጥር ከአጠቃላዩ የሊባኖስ ሕዝብ ሊስተካከል ትንሽ ነዉ የቀረዉ።አራት ሚሊዮን ገደማ።ትልቂቱ፤ ሐያሊቱ፤ ሐብታሚቱ፤ የሶሪያዉን ጦርነት ዘዋሪቱ ዩናይትድ ስቴትስ ጦርነቱ ካሰደደዉ ሶሪያዊ ያስጠጋችዉ ሁለት ሺሕ አይሞላም።የጦርነቱ ወላፈን የሚለበልባት ትንሺቱ፤ ደሐይቱ ሊባኖስ ግን ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ የሶሪያ ስደተኛ ታስተናግዳለች።የስደተኞ ብዛት፤ የመሰደዳቸዉ ምክንያት፤ስደተኞችን ለመርዳታ ዓለም ማንገራገሩ የዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።

እንግሊዞች በጉልበትም፤ በስብከትም፤ በብልጠትም፤ በስደትም እያሉ-ከአዉትሬሌያ እስከ ካናዳ፤ ከኒዉዚላንድ እስከ ናጄሪያ፤ ከዩናይትድ ስቴትስ እስከ ደቡብ አፍሪቃ፤ ከፎክላንድ ደሴቶች እስከ ኬንያ ወደ ገሚስ ዓለም ተሰደዉ፤ በገሚስ ዓለም ሠፍረዋል።ብዙ ሐገር-ሐገራቸዉ ሆኗልም።እንግሊዞች የተሰደዱ፤ የሠፈሩበት ወይም ይቆጣጠሯቸዉ የነበሩ ሐገራት ነባር ሕዝብ ዛሬ ሲሰደድ ግን በራቸዉን ይከረችሙ ይዘዋል።

የፈረንሳዮች የተለየ ዓይደለም።ከሕይቲ እስከ ሴኔጋል፤ ከቬትናም እስከ ጀቡቲ፤ ከኩቤክ እስከ ማዳጋስካር ዘምተዉ፤ ተሰደዉ፤ ተቆጣጥረዉ ተሰራጭተዋል።የዘመኑን ፈረንሳዊ በጣም ከሚያሳስቡት አንዱ በመቶ የሚቆጠሩ የአፍሪቃ እና የእስያ ስደተኞች ወደ ፈረንሳይ መግባታቸዉ ነዉ።ፈረንሳዮች ወደ ሐገራቸዉ የገባ ስደተኛ ወደ ሌላ ሐገር ዳግም እንዲሰደድ ሲገፋፉ፤ -እንግሊዞች ባንፃሩ ስደተኛዉ ፈረንሳይን አቋርጦ ወደ ግዛታቸዉ እንዳይገባ ድንበራቸዉን ያጥራሉ።።

የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዳቬድ ካሜሩን ባለፈዉ ወር።የመጀመሪያዉ እና ሁለተኛዉ በሚባሉት ጦርነቶች ወቅት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ጀርመናዊያን ወደተለያዩ ሐገራት ተሰደዉ ነበር።በጦርነቶቹ ፍፃሜ ደግሞ ሚሊዮኖች ከየነበሩበት ሐገራት ወደ ሐገራቸዉ ተባርረዋል። ተመልሰዋል።የቀድሞዉ የምዕራብ ጀርመን መንግሥት በ1950 እንዳስታወቀዉ ከጦርነቱ ፍፃሜ እስከ 1950 በነበረዉ አምስት ዓመት ብቻ፤ ከምሥራቅ አዉሮጳ ሐገራት ብቻ፤ 11, ሚሊዮን ጀርመናዊ ወደ ሐገሩ ተመልሷል።ወይም ተባርሯል።

ካለፈዉ ዓመት ጀምሮ ስደተኞችን ማስተናገድ ወይም አለ ማስተናገድ ጀርመን ፖለቲከኞች አከራካሪ ርዕስ ነዉ።ቀኝ ፅንፈኛ ጀርመናዊያን ደግሞ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን በእሳት ያነዳሉ።መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ባለፈዉ ሐምሌ ከአንዲት ፍልስጤማዊት ወጣት ስደተኛ ለቀረበላቸዉ ጥያቄ-በሰጡት መልስ እንዳሉት ግን ጀርመን ትሁን ሌሎቹ ሐብታም ሐገራት ሁሉንም ስደተኛ ማስተናገድ አይችሉም።

«እንደምታዉቂዉ ሊባኖስ ዉስጥ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ስደተኞች አሉ።ሁሉም ይምጡ ብንል፤ አፍሪቃዉያን በሙሉ ይምጡ ብንል (ማስተናገዱን) አንችለዉም።»የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተደጋጋሚ እንዳስታወቀዉ እስከ አምና ድረስ የተሰደደና የተፈናቀለዉ ሕዝብ ቁጥር ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ ታይቶ ከማይታወቅበት ደረጃ ደርሷል። ከሥልሳ-ሚሊዮን በላይ።ይሕ ሁሉ ሕዝብ በተሰወኑ ሐገራት ይስፈራል ማለት የማይታሰብ፤ሜርክል እንዳሉትም የማይቻል ነገር ነዉ።

ይሁንና ሐብታም-ሐያሉ ዓለም ስደተኛ እንዳይመጣበት ወይም እንዳይበዛበት በጦር ሐይል፤ በግንብና በሽቦ አጥር በሩን መዝጋትም መፍትሔ ሊሆን አይችልም።የስደተኛዉን ቁጥር መቀነስ ከተፈለገ-የስደቱን ዋና ዋና ምክንያቶች ማስወገድ ወይም መቀነስ እንጂ አብነቱ።የስደቱ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ ጦርነት ወይም ግጭት ነዉ።

ከ1948 ጀምሮ ሐገሩን የተቀማዉ ስድት ሚሊዮን ፍልስጤማዊ ሊባኖስ፤ ሶሪያ፤ ዮርዳኖስ፤ ግብፅ ሌላዉምጋ ለሰወስተኛ ትዉልድ እንደተበተነ ነዉ።ከሁለት ሺሕ ዘመን በላይ በድፍን ዓለም ተበትነዉ የስደተኛነትን ሥቃይ መከራ ከማንም በላይ የሚዉቁት እስራኤላዉያን በተራቸዉ የሌላ ሐገር ቀሚ፤ አሰዳጅ፤ ግዛታቸዉን በግንብ-አጣሪ፤ ስደተኛን አባራሪ ሲሆኑ ሐያል ሐብታሙ ዓለም ለስልሳ ሰባት-ዘመን መፍሔ ያለማበጀቱ ሊያነጋግር በተገባ ነበር።

ግሪክ የገባ አንድ ኢራቃዊ ስደተኛ በቀደም እንዳለዉ ካለፉት ሁለት ሰወስት ዓመታት ወዲሕ የዓለም የጧት ማታ ዜና ሶሪያ በመሆኑ ኢራቅ ተረስታለች።«እየጠበቅሁ ነዉ።ግን አይረዱኝም።ሶሪያዊያኑን ብቻ ነዉ የሚረዱት።ምክንያቱም (አስተናጋጆቹ) ኢራቅ፤ፓኪስታን፤ ኢራን የሚሆነዉን አያዉቁም።ከኢራቅ መምጣቴን ስነግራቸዉ ወደ ሐገርሕ ተመለስ ይሉኛል።ኢራቅ ጥሩ ነዉ።ጦርነት የለም ይሉኛል።ኢራቅ ስላለዉ ምንም አያዉቁም።»የካፒታሊስት-ኮሚንስት ጠላቶች በ1980ዎቹ አፍቃኒስታን ዉስጥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የገጠሙት ጦርነት እስከዚያ ዘመን ድረስ ከፍልስጤም እስከ አፍሪቃ፤ ከእስያ እስከ ደቡብ አሜሪካ በነበረዉ ጦርነት ለስደት የተጋለጠዉን ሕዝብ ስቃይ መከራ አስዘነጋ።

አፍቃኒስታን በአልቃኢዳ ጥቃት ሰበብ በ2000 ዳግም የዉጊያ አዉድ ስትሆን የከዚያ በፊቱ ግጭት ጦርነት ለስደት እንግልት ያጋለጠዉ ሕዝብ ተዘንግቶ ነበር።ከዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ሥደተኛ የምታስተናግደዉ ፓኪስታን ናት።2, 7 ሚሊዮን።አብዛኛዉ ስደተኛ አፍቃናዊ ነዉ።የአፍቃኒስታን ሕዝብ በጦርነት ማለቅ መሰደዱ የዓለም አንደኛ ርዕስ የነበረዉ ግን በ2003 ኢራቅ እስክትወረር ድረስ ነበር።ኢራቅ ዛሬም ከጦርነት አልተላቀቅችም።ከ1,5 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝቧ ዛሬም ስደተኛ ነዉ።

የዓለም ርዕስ ግን ሶሪያ በመሆኑ የኢራቅ፤የሶማሊያ፤ የደቡብ ሱዳን፤ የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፤የሊቢያ ስደተኛን ከባለ ጉዳይ ባለፍ የሚያስታዉሰዉ የለም።አንደኛዉ ጦርነት ሳይበርድ-ሌላ እየተቀጣጠለ፤ አንዱ ጦርነት ያሰደደዉ ሕዝብ በቅጡ ሳይሰፍር ሌላ እየተሰደደ የስደተኛዉ ቁጥር ንረት፤የችግር ስቃዩ ግዝፈት ሊያስደንቅ አይገባም።

ሐብት፤ ጉልበት፤ እዉቀት ብልሐቱ ሞልቶ የተረፈዉ ዓለም ጦርነትን ከማስቆም ይልቅ ጦርነትን እየለኮሰ ከጦርነት የሚሸሸዉ ሕዝብን ለመርዳት ማቅማማቱ በርግጥ አስተዛዛቢ ነዉ።በሊባኖስ የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ መልዕክተኛ ፋብሪሲዮ ካርቦኒ ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት የሶሪያዉ ጦርነትና ስደተኛ መፍትሔ ሳያገኝ ሌላ ቦታ ሌላ ጦርነትና የተፈጥሮ መቅሰፍት በመከሰቱ ለስደተኛዉ የሚሰጠዉን ርዳታ እንዲቀንስ አድርጎታል።

«በዚሕ ዓመት በርካታ ቀዉሶች አሉ።ከሶሪያ በተጨማሪ ኢራቅ፤ የመን፤ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ሌሎችም ቀዉስ ዉስጥ ናቸዉ።በዚያ ላይ የኔፓል (መሬት መንቀጥ) እና ኢቦላ አለ።በዚሕም ምክንያት የስደተኛዉን ፍላጎት ለማሟላት በቂ ገንዘብ የለም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሶሪያ ስደተኞች መርጃ ባለፈዉ ዓመት 1,5 ቢሊዮን ዶላር እንዲሰጠዉ ጠይቆ ነበር። ገንዘቡ ሥላልተገኘ ሊባኖስ ለሰፈሩ ስደተኞች የሚሰጠዉን ርዳታ ለመቀነስ ተገድዷል።እስከ ዘንድሮ ድረስ ለአንድ ስደተኛ በቀን ሰላሳ አራት ዶላር ገደማ ይሰጥ ነበር።አሁን ግን ወደ አስራ-ሰባት ዶላር ዝቅ ብሏል።የተቀነሰዉ ስቡ ሳይሆን ጡንቻዉ ነዉ።ማጣፈጫዉ ሳይሆን ምግቡ ራሱ ነዉ።»

አንዲት ዩናይትድ ስቴትስ የሶሪያ እና የኢራቅ እስላማዊ መንግሥት (ISIS) የተሰኘዉን ቡድን በጦር ጄት መደብደብ ከጀመረች ካለፈዉ ዓመት ወዲሕ ከ2,7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከስክሳለች።አራት ሚሊዮን ለሚጠጋዉ ሶሪያዊ ስደተኛ የሁለት ዓመት ቀለብ ማለት ነዉ።አራት ሚሊዮን ከሚገመተዉ የሶሪያ ስደተኛ ዩናይትድ ስቴትስ እስካለፈዉ ሐምሌ ድረስ የተቀበለችዉ ግን ሁለት ሺሕ አይሞላም።

ዩናይትድ ስቴትስ በመልከዓ ምድር የሚርቋትን የአፍሪቃ፤ የእስያ እና የምስራቅ አዉሮጳን አይደለም የሐይቲ ዜጎችን እንኳ ከፈቀደቻቸዉ ዉጪ ወደ ግዛትዋ እንዲገቡ አትፈቅድም።ከሜክሲኮ ጋር የሚያገናኛትን ድንበርማ በግንብ ለስናዋለች።

ትንሺቱ፤ ደሐይቱ ዮርዳኖስ ግን 2,5 ሚሊዮን የሚደርስ ስደተኛ ታስተናግዳለች።ቻይና በሐብት ወይም በኤኮኖሚስቶቹ ቋንቋ በአጠቃላይ አመታዊ ምርት (GDP) ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሎ ከዐለም ሁለተኛዋ ሐገር ናት።የተቀበለቻቸዉ ስደተኞች ግን ከ300 ሺሕ አይበልጡም።አብዛኞቹ የአጎራባቾችዋ ሐገራት ዜጎች ናቸዉ።የዓለም ሰወስተኛዋ ሐብታም ሐገር ጃፓን ናት።

ሸቀጥዋን በመላዉ ዓለም ትቸበችባለች እንጂ ዓለምን ካጨናነቀዉ ስደተኛን በይፋ የተቀበለችዉ የለም።አራተኛዋ ሐብታም-ጀርመን ናት።ጀርመኖች ስደተኛ በዛብን እያሉ ነዉ።አምስተኛዋ ብሪታንያ ናት ብሪታንያ ስደተኛ እንዳይገባባት በሯን አሳጥራለች።ፈረንሳይ ስድተኛዋ ሐብታም ሐገር ናት።የፈረንሳይ መንግሥት ሐገሩ የገቡ ስደተኞች እንዲወጡ ይገፋፋል።

ሰወስቱ የአዉሮጳ ሐያል፤ ሐብታም መንግሥታት የሚመሩት የአዉሮጳ ሕብረት ከዩናይትስ ስቴትስ ጋር በመሆን በዩክሬኑ ጦርነት ሰበብ ከሩሲያ ጋር ተኩስ ቀረሽ ጠብ ከገጥሙ አመት አለፋቸዉ።የአዉሮጳ ሕብረትና ዩናይትድ ስቴትስ በሚደግፉት በዩክሬን መንግሥት ጦርና በሩሲያ በሚደገፉት አማፂያን መካከል የሚደረገዉን ጦርነት ከሚሸሸዉ ሕዝብ አብዛኛዉ መጠለያ ያገኘዉ ሩሲያ እንጂ ዩናይትድ ስቴትስ ወይም የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት ዉስጥ አይደለም።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ከሚሽነር (UNHCR) እንደዘገበዉ ሃያ-ሥምንቱ የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት ከአፍሪቃ፤ ከመካከለኛዉ ምሥራቅ፤ ከአፍቃኒስታን፤ ከዩክሬን ከተሰደደዉ ወደ ሐያ ሚሊዮን ከሚጠጋ ሕዝብ ጥገኝነት የሰጡት ሰወስት መቶ ሺሕ አይሞላም።

አንዲት ቱርክ ግን ባንድ በኩል የአዉሮጳና የአሜሪካ ተዋጊ ጄቶችን በሌላ በክል ከ1,6 ሚሊዮን የሚበልጡ የሶሪያ ስደተኞችን ታስተናግዳለች።የትንሺቱ ሊባኖስ ደግሞ ከቱርክም የባሰ ነዉ።በሚሊዮን የሚቆጠሩ የፍልስጤም ስደተኞችን ከ1967 ጀምሮ ታስተናግዳለች።አሁን ደግሞ 1,5 ሚሊዮን የሚጠጋ ሶሪያዊ ስደተኛ ለማስተናገድ ተገድዳለች።

«ሁኔታዊ በጣም አስቸጋሪ ነዉ።አሁን እንግዲሕ ሰወስት አራት ዓመት መሆኑ ነዉ።ሐገሪቱ (ሊባኖስ) በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ኮሚሽነር የተመዘገቡ ብቻ 1,2 ሚሊዮን ስደተኞች ተቀብላለች።ስደተኞች ከመምጣታቸዉ በፊት ራሱ የሊባኖስ የመሰረተ-ልማት አዉታሮች ማለት የጤና፤ የዉሐ፤ የኤሌክትሪክ እና የመሳሰሉት አገልግሎቶች በጣም ደካማ ነበሩ።በዚሕ ችግር ላይ 1,2 ሚሊዮን የተመዘገበ እና ከሁለት መቶ ሺሕ እስከ ሰወስት መቶ ሺሕ የሚገመት ያልተመዘገበ ስደተኛ ሲታከልበት ችግሩን መቋቋም አይቻልም።»

ሊባኖስ ለአመታት ካደቀቃት ጦርነት በቅጡ አላገገመችም።የሶሪያዉ ጦርነት በስደተኞች ከማጨናነቅ በተጨማሪ ወላፈኑ-በቦብ ፍንዳታና በብቀላ ግድያ እያደማት ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት UNHCR በ1951 የተመሰረተዉ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ እስከዚያ ዘመን ድረስ ወደየሐገሩ ያልተመለሰዉን አንድ ሚሊዮን ስደተኛ ለመርዳት ታስቦ ነበር።በስልሳ አራት-ዓመቱ ዘንድሮ ከስልሳ ሚሊዮን በላይ ስደተኛና ተፈናቃዮችን መርዳት፤ መርዳቱ ሲያቅተዉ መቁጠር ግዱ ነዉ።

ሐያል-ሐብታሙ ዓለም ስደተኛዉን በያለበት ለመርዳት እያቅማማ፤ ወደ ሐገሩ እንዳይገቡበት ግዛቱን እያጠረ፤ ለሰደት ሰበብ የሚሆነዉን ግጭት-ጦርነትም ለማስቆምም እያመነታ ነዉ።ዛሬም ፍልስጤም-እስራኤል፤ ሶማሊያ፤ አፍቃኒስታን፤ ኢራቅ፤ ሶሪያ፤ ደቡብ ሱዳን፤ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፤ዩክሬን፤ሊቢያ፤ የመን ዛሬም ሰላም የለም።ኤርትራ፤ ኢትዮጵያ፤ ዚምባቡዌ ሌሎችም አፍሪቃ ሐገራት ሕዝብን ከስደት የሚያቆም ብልሐት አይታይም። ሠላም ከሌለ፤ ሕዝብ ካልተረጋጋ፤ መሰደዱ፤በሕባር ዉሐ፤ በበረሐ ሙቀት፤ በጨካኖች ካራ ማለቁ አይቀርም።እስከ መቼ?

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ

Audios and videos on the topic