ስብርባሪ ከዋክብት፣ ፕሉቶና የኅዋው ምርምር | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 24.10.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ስብርባሪ ከዋክብት፣ ፕሉቶና የኅዋው ምርምር

ባለፈው እሁድ ፣ አንድ ስባሪ ኮከብ ወደ ማርስ ከዚያ በፊት ታይቶ ባልታወቀ ሁኔታ መጠጋቱ ፤ ለምን የሥነ ፈለክ ጠበብትን ትኩረት ሳበ? ስባሪ ከዋክብት ከየት ነው መነሻቸው? 9ኛው ፕላኔት አይደለም ተብሎ እ ጎ አ በ 2006 ከ ዝርዝር እንዲወጣ የተደረገው

ሆኖም ድንኩ ፕላኔት የሚሰኘው ፕሉቶ ፣ ወደ ቀድሞው ደረጃው ይመለስ ይሆን? 95 ከመቶ የሚሆነውን የኅዋ ክፍል ምንነት ማወቅ የተሣነው ሰው ፣ ስለፍጥረተ-ዓለም ሰፊ ግንዛቤ ለማግኘት ያለው ዕድል እስከምን ድረስ ይሆን? በዚህ ረገድ የአውሮፓውያኑ የኑልክየር ምርምር ጣቢያ ምንድን ነው ያለው ተስፋ ?

በብርሃን ዓመት የሚቆጠር ርቀት ያላቸውን የሰማይ አካላት ምንነት ለማወቅ፣ በኅዋ በተለይ ፣ ርኡይነቱ የጎላ የሩቅ ሰማያዊ አካል ማየት እንደሚቻል ያለፉት ጥቂት ዓመታት የምርምር ውጤቶች ፣ እዚህም ላይ ዘንድሮ ለኖቤል ሽልማት ያበቃው፣ ዘመናዊው «ናኖስኮፕ» ማጉሊያ መንጽር ሊጠቀስ ይችላል። በዚህ አዲስ የርኡይነት ደረጃና መለኪያ ባለው መሣሪያ በመታገዝም ነው ከፀሐያዊ ጭፍሮች ውጭ በሌሎች የተጫፈሩ ፕላኔቶች ጨረቃዎችና የመሳሰሉት፤ አንዳንድ ከዋክብትንና መሰል አካላትን በተሻለ ሁኔታ ለመመልከት የታቻለው።

በመሆኑም ባለፈው 2013 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ነበረ የአውስትሬሊያ የሥነ ፈለክ ጠበብት፤ ከሰሞኑ ጉድ! ያሰኘውን ሥባሪ ኮከብ ፤ ከኔፕቱን ምሕዋር ባሻገር --Oort Cloud የተሰኘውን መሥመር ከ አንድ ሚሊዮን ዓመት በፊት ለቆ ጉዞ መጀመሩን ከሞላ ጎደል መገንዘብ ያስቻለው።

ስብርባሪ ከዋክብት ፣ ማለት፤ ፍጥረተ ዓለም ከ 4,6 ቢሊዮን ዓመት ገደማ በፊት ፀሐይና ጭፍሮቿ ሲከሠቱ ፣ ለግንባታ እንደማያስፈልግ ፣ ጥቅም እንደማይሰጥ ፣ የተፈረካከሠ ድንጋይ ወይም ትርፍ ጡብ መሰል ቁስ ሆነው የቀሩ አካላት ናቸው፤ የላይኛው ክፍል በጥንታዊ በረዶ የተሸፈነ ነው። ወደ ጸሐይ ሲጠጉ፤ በረዶው በመቅለጥ የጋዝ ጅራት መሰል ነገር ይፈጥራል። በላቲን እንዲያውም ስባሪ ኮከብ Stella Cometa «ባለረጅም ፀጉር ኮከብ» ነው የሚባለው።

አንዳንድ ሳይንቲስቶች እንደሚገምቱት ከሆነ ፤ ስባሪ ከዋክብት ቁጥራቸው በብዙ ቢሊዮኖች የሚገመት ነው። እስካሁን የታዩት እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። ባለፉት 2,500 ዓመታት፤ ሰዎች በግምት 2,000 ያህል ስባሪ ከዋክብትን ለይተው ሳያውቁ አልቀሩም። ስባሪ ከዋክብት፣ የሚሽከረከሩባቸውን ምኅዋሮች እምብዛም በግልጽ መከታተል አዳጋች ሲሆን፣አንዳንዶቹ እንዲያውም አንድ ዑደት ለመፈጸም 40,000 ዓመታት ያህል ጊዜ የሚወስድባቸው ናቸው። በሥነ ፈለኩ ዓለምr ከብዙዎቹ ይበልጥ ጎልቶ ስማቸው የሚጠቀስ ስባሪ ከዋክብት፤ በብሪታንያዊው የሥነ ፈለክ ሊቅ ኤድመንድ ሃሊ እ ጎ አ በ 1682 ተለይቶ የተጠቀሰውና በ 1607 እንዲሁም በ 1531 ታይቶ ከነበረው ስባሪ ኮከብ ጋር ተመሳሳይ መሆኑ፤ እንደተነበየውም ሆነ በስሌቱ እንዳመላከተውም ፤ እርሱ ካረፈ በኋላ በ16ኛው ዓመት ፣ እ ጎ አ በ 1758 ያው ስባሪ ኮከብ ሊታይ ችሏል። በስሙ «የሃሊ ስባሪ ኮከብ»(ሃሊስ ኮመት) የተሰኘው ስባሪ ኮከብ እ ጎ አ በ 1986 ዓ ም ታይቶ ነበረ። ሃሊስ ኮሜት፤ 15 ኪሎሜትር ርዝማኔና 4 ኪሎሜትር ወርድ ያለው ነው።

ሌላው፣ ፀሐይን በ የ 6,6 ዓመት አንድ ጊዜ የሚዞረው ፣ 67P ቹርዩሞቭ-ጌራሲሜንኮ የተሰኘው ለመጀመሪያ ጊዜ ጎ አ በ 1969 በ ተማራማሪዎቹ ፤ ክሊም ቹርዩሞቭ እና ስቬትላና ጌራሲሜንኮ የተገኘው ፣ 4 ኪሎሜትር ያህል ርዝማኔ ያለው ስባሪ ኮከብ ሲሆን ፣ እርሱም የአውሮፓው« ሮዜታ » የምርምር መንኮራኩር ከቅርብ የሚከታተለው የኅዋ አካል ለመሆን በቅቷል። እ ጎ አ በ 1992 ከጁፒተር ከባቢ አየር ውስጥ ሲገባ፤ በሰዓት 210,000 ኪሎሜትር ፍጥነት በመክነፍ፤ ከ 21 ቦታ ተከፋፍሎ ፤ መሬትን በ 11,2 እጅ ወርድ ከሚበልጠው እጅግ ግዙፉ ፕላኔት ጁፒተር ጋር በመታለም ከእኛይቱ ምድር የሚበልጥ የእሳት ኳስ ፈጥሮ እንደነበረ ተጠቅሷል። የስባሪ ከዋክብት አደጋ እንዲህ ብርቱ በመሆኑም ነው ፣ ከሥጋት ጋር ብዙ የሚነገርለት። ልክ እንደ ፀሐይ ግርጃ ፣ ስባሪ ከዋክብትም በታሪክ መጥፎም ጥሩም ገድ እንዳላቸው ሲተረክላቸው ኖሯል። በጥሩ ገድ እንደ ብሥራት የሚቆጠረው ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ የታየው ኮከብ ሲሆን፤ ናፖሊዮን ሲወለድ ታየ የተባለው በመጥፎ ገድ ነው የተጠቀሰው። እ ጎ አ በ 79 ዓ መተ ምሕረት ፖምፔን ያጠፋት የቬሱቪየስ እሳተ-ገሞራ ፍንዳታ፤ በ 1665 የለንደንን ሕዝብ የፈጀው ወረረሽኝ በሽታ፤ ሁሉም በስባሪ ከዋክብት መጥፎ ምልክት የተፈጸመ ነው እየተባለ ነው በዓለም ታሪክ የተጠቀሰው። በመጀመሪያው የዓመተ ምሕረት፣ ምዕተ ዓመት ውስጥ የኖረው ግብጻዊው የሥነ ፈለክ ሊቅና ፣ ኮከብ ቆጠሪ ፣ቶለሚ ፣ ስባሪ ከዋክብት ጦርነት እንዲጫር ፣ በካባቢ አየር መጥፎ ሁኔታ እንዲከሠት፤ ወንዶችም ለእኩይ ተግባር እንዲነሳሱ የሚያደርጉ ናቸው ሲል ያስጠነቅቅ ነበር። («ኮከባቸው አልገጠመም፤ «ኮከቤ አይወደውም» ) የሚሉ ዓይነት አባባሎች በእኛ ባህል ውስጥ የሚነገሩት ለምን ይሆን?

ባለፈው እሁድ ከማርስ በ 140,000 ኪሎሜትር ርቀት የታየው «ሳይዲንግ ስፕሪንግ» የተሰኘው ስባሪ ኮከብ ፣ አጠር ላለ ጊዜም ቢሆን ሥጋትንም ፣ ግርምትም አስከትሎ ነበር። ስባሪው ኮከብ ወደ ማርስ መጠጋቱ ፣ አቧራው ፣ በዚያ በሚሽከረከሩ ከመሬት በተላኩ የምርምር መንኮራኩሮች ላይ ሳንክ ያስከትል ይሆን? የሚል ጥያቄ በማጫሩም ነበረ የሥነ ፈለክ ጠበብትን ትኩረት የሳበው።

በጸሐያዊ ጭፍሮች ዙሪያ፣ ከፀሐይ ሌላ ፣ በፕላኔቶች ፣ ከዋክብት ፤ ስባሪ ከዋክብት ፣ ጨረቃዎችና በመሳሰሉት፤ ከዚያም አልፎ አያሌ የብርሃን ዓመት ርቀት ባላቸው ተመሳሳይ ክፍሎች ለማወቅ ምርምር በቀጠለበት ባሁኑ ዘመን ፤ በፀሐይ ዙሪያ ከሚገኙት ፕላኔቶች መካከል ፣ እ ጎ አ በ 2006፣ 9ኛ ፕላኔት መሆኑ ውድቅ የተደረገበት ፕሉቶ፣ አሁንም እንደገና በማከራከር ላይ ነው። ለክርክሩ አንደኛው መንስዔ ፤ በአታካማ በረሃ ቺሌ የተተከሉ የላቀ ደረጃ ያላቸው ቴሌስኮፖች ፤ የፕሉቶን ምኅዋር በትክክል መለካት በመቻላቸው ነው። ፕሉቶ ፤ ፀሐይን አንድ ጊዜ ለመዞር 248 ዓመታት የሚወስድበት ንዑስ ፕላኔት ነው።

አጠገቡ ያለው «ኢሪስ» የተባለው ሌላ ፕላኔት በመጠን እንደሚበልጠው በመታወቁም ነበረ ፕራግ ላይ እ ጎ አ በ 2006 በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሥነ ፈለክ ሊቃውንት ጉባዔ ፤ ከ9ኛ ፕላኔትነት ደረጃ የወረደው። ይሁንና እስካሁን «ድንክ ፕላኔት» በሚል ስያሜ መጠቀሱ አልቀረም። በጸሐይ ዙሪያ ከሚገኙ የሰማይ አካላት ፤ «ድንክ ፕላኔት» ለመባል የሚበቁ ከ 200 የማያንሱ አሉ። ያም ሆኖ በ 1930 የተገኘውና ለብዙ ዐሠርተ ዓመታት በ 9ኛነት ሲጠቀስ የኖረው ፕሉቶ በቀጣይ የሥነ ፈለክ ጠበብት ጉባዔ ምናልባት የቀድሞው ማዕረጉ ይመለስለት ይሆናል።

ስለስባሪ ከዋክብት ፤ ፕላኔቶች ፤ ጨረቃዎችና ስለመሳሰሉት በአጠቃላይ ስለፍጥረተ ዓለም ምሥጢር ለማወቅ ከሚመራመሩት አንዱ ፣ የአውሮፓው የኑክልየር ምርምር ድርጅት ( CERN ባለፈው ወር ማለቂያ ገደማ የተመሠረተበትን 60 ዓመት ያከበረ ሲሆን፣ በመጪው ዓመትም ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያስታወቀው።

ከአውሮፓና ከሌሎችም ክፍላተ ዓለም የተውጣጡ የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ጠበብት፣ በዚያ ድርጅት ውስጥ የሚመራመሩ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም እጅግ ግዙፉን በፍጥነት በሚሽከረከረው አቶም ጨፍላቂ መሣሪያ (LHC)ረዳትነት በመጀመሪያ ስለተገኘው ውጤት ከዚህ ቀደም በዚህ ዝግጅት ማውሳታችን የሚታወስ ነው። በአውሮፓው የኑክልየር ምርምር ድርጅት ( CERN) ቀጣዩ ርምጃ ይበልጥ አጓጊ ሳይሆን አይቀርም ነው የሚባለው።

የአቶምን ቅንጣት ሥረ - መሠረት ለማወቅ በሚደረገው የምርምር ሩጫ ፣ በቀጣዩ ምን ይሆን የሚጠበቀው? ፈልጎ ለማግኘት ጥረት ስለሚደረግበት ነገር ፣ በሚመጣው ጊዜ ምን እንደሚፈለግ ካሁኑ መጠቆምም ሆነ መተንበይ ይችላሉ? ለድርጅቱ የሥራ መሪ ለጀርመናዊው ፣ ሮልፍ ዲተር ሆየር የቀረበ ጥያቄ ነበር።

« በአቶም ቅንጣት ክፋይ ፤ ወይም በሂግስ የአቶም ቅንጣት በኩል ስለሚታየው ፍጥረተ ዓለም ግንዛቤ ለመጨበጥ ችለናል። አሁን ስለፍጥረተ ዓለም 5 ከመቶው ምን እንደሆነ መግለጽም ሆነ ማብራራት እንችላለን። 95 ከመቶው ግን ከሞላ ጎደል ምን እንደሆነ አናውቅም ወይም ምን እንደሆነ ሐሳቡም የለንም።እንደሚመስለኝ እዚህ ላይ ሰፊ እመርታ ማድረግ የሚጠበቅብን ነው የሚሆነው።

Planet Pluto ist ein Planetino

ተፈጥሮ ብሩሕ ገጿን ካሳየችን ምናልባት በሚመጡት ጥቂት ዓመታት፤ ጽልመት ስለዋጠው ፍጥረተ ዓለም ማወቅ የምንጀምርበት መስኮት ይከፈት ይሆናል። መቼ? አላውቅም»።

LHC እ ጎ አ እስከ 2035 ይሠራል ከዚያ በኋላ ምን ይመጣል? ምን ይደረጋል? ለሚለው ጥያቄ ሮልፍ ዲተር ሆየር እንዲህ ብለዋል።

«ለዚህ መልስ ለመስጠት LHC ውና ሌሎች አውታሮች፣ እንደቴሌስኮፕ የመሳሰለው ለምሳሌ ያህል ውጤት ሲያሳዩ ወደምን እያመራን እንደሁ መናገር እንችላለን። የተተከሉት አውታሮቻችን የሚሠሩበት ጊዜም ሆነ ዘመን ረዘም ያለ ቢሆንም ፣ ስለአዳዲስ አውታሮች ካሁኑ መነጋገር መጀመር አለብን። ስለ LHC ለመጀመሪያ ጊዜ የተነገረው ከ 30 ዓመት በፊት ፤ እ ጎ አ በ 1984 ነበር። መናገሩ ምንም የሚያስከፍለው ዋጋ የለም። ማጥናት ነው። ግን ማጥናት ካልተጀመረ በኋላ ምንም አይኖረንም። ስለሆነም ካሁኑ ማሰብ ፤ ማሰላሰል ይኖርብናል። ከእስካሁኑ የላቀ ክብ የሆነ አውታር ወይስ በአግድሞሹ የሚተከል አውታር ነው የሚያስፈልገን ---ወይስ ደግሞ---»

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic