ስራ ፈላጊዎች ወደ ሳውዲ እንዳይሄዱ መታገዱ | ዓለም | DW | 24.10.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ስራ ፈላጊዎች ወደ ሳውዲ እንዳይሄዱ መታገዱ

የኢትዮጵያ መንግስት ቢያንስ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ስራ ፈላጊዎችን ወደ ሳውዲ አረቢያ እንዳይገቡ ማገዱን ኣስታወቀ። በዚሁ መሰረት 40 ሺሽ ያህል ቀደም ሲል የተፈቀዱ ቢዛዎችም ተሰርዘዋል።

የሳውዲ አረቢያ መንግስትም ባላፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ስራ ፈላጊዎች ወደዚያች ኣገር እንዳይገቡ ጊዜያዊ እቀባ መጣሉ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ግን እገዳው የሳውዲ መንግስት ለጣለው ዕቀባ ኣጸፋ ኣለመሆኑን ኣስታውቀዋል።

ዘውዳዊው የሳውዲ ኣራቢያ መንግስት ከኢትዮጵያ ሰራተኞችን ላለመቀበል ወይንም ቅበላውን ላልተወሰነ ጊዜ ለማገድ የወሰነው በሳውዲ አረቢያ ምንጮች መሰረት የሳውዲ ህጻናት በኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች መገደልን ኣሊያም በህግ ቐንቐ በግድያ መጠርጠርን ተከትሎ ነው። ይኸው በሳውዲ አረቢያ የኣገር ውስጥ ጉዳይ እና የስራ ሚኒስቴር የተጣለው እገዳ የግድያው ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስ ይዘልቃል ተብለዋል።
ሸሪፍ ኦስማን የተባሉ ኣንጋፋ የኢትዮጵያ ዲፒሊማት እንደሚሉት ይህ ሁሉ ሲሆን ከሳውዲ ኣረቢያ መንግስት በኩል ለኢትዮጵያ መንግስት የተገለጸ ነገር የለም። ይሁንና የኢትዮጵያው ጠ/ሚ/ር ኃ/ማ/ደሳለኝ ከቀናት በፊት ፓርላማ ቀርበው ባሰሙት ንግግር ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ኢትዮጵያን ሰራተኞች ወደ ሳውዲ አረቢያ እንዳይገቡ ማገዳቸውን ኣስታውቀዋል። በኢትዮጵያ የብዙኃን መገናኛዎች ዘገባ መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት 40 000 ያህል የቤት ሰራተኞችን ወደ ሳውዲ አረቢያ ለማስገባት የቀረቡለትን የቪዛ ጥያቄ ሰርዘዋል።


እርምጃው የሳውዲ አረቢያ መንግስት የኢትዮጵያ ሰራተኞችን ለተወሰነ ጊዜ ላለመቀበል ባለፈው ሳምንት ለጣለው እቀባ ምላሽ መሆኑን በሳውዲ አረቢያ የሰራተኞች ኣስመጪ ኮሚቴ አባላት ይናገራሉ። በኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስተር ቃል ኣቀባይ የሆኑት አንባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደሚሉት ግን የመንግስታቸው አቐም ከዚህ ጋር የተገናኘ ኣይደለም።
የሰራተኞች ኣስመጪ ኮሚቴ አባላት እንደሚሉት የኢትዮጵያ መንግስት የሳውዲ ባለስልጣናት ዕቀባውን ከመጣላቸው በፊት የተፈቀዱ ቪዛዎችን ጭምር ነው ያመከነው። እነዚህ 40 000 ያህል ቪዛዎች ደግሞ በኣስመጪው መ/ቤት መረጃ መሰረት ኣስቀድሞ ክፍያ የተፈጸመባቸውም ናቸው። እናም ይላሉ ከጂዳው የኣስመጪ ኮሚቴ ጽ/ቤት ሚ/ር ሳሊህ ሃርናዳህ የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ አቐሙ የሚጸና ከሆነ ገንዘቡን ለሳውዲ ኣሰሪዎች መልሶ መተካት ይኖርበታል። በዚህ ረገድ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስለመምከራቸው ግን የጠቀሱት ነገር የለም።
በተያያዘ ዜና የሳውዲ አረቢያ መንግስት ያወጣውን መመዘኛ ኣሙዋልተው ለተገኙ ህገ ወጥ ስደተኞች የኣገር መኖሪያ ፈቃድ ለመስጠት የተቆረጠው ቀነ ገደብ በቀጣዩ ሳምንት እንደሚያበቃ ተመልክተዋል። ይኸው የተራዘመ ቀነ ገደብ ሊያበቃ በተቃረበበት በኣሁኑ ወቅት በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኢንባሲ በቪዛ ፈላጊዎች መጨናነቁም ተሰምተዋል። አንባሳደር ዲና ሚፍቲ እንደሚሉት በእርግጥ የመንግስታቸው አቐም በዚህ ኣይነቱ ጊዛዊ ችግሮች ላይ ያተኮረ ኣይደለም።
ወትሮውንም ዜጎችን የማስተናገድ ኣቅሙ ደካማ መሆኑ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ኢምባሲ ሁለቱ መንግስታት በየፊናቸው በጣሉት የክልከላ ገደብ ጉዳዩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበታል እየተባለ ነው። የሳውዲ አረቢያ መንግስት ከህገ ወጥ ስደተኞች ኣንጻር የያዘው አቐም በእርግጥ በኣገሪቱ የሚገኙትን ሁሉንም ስደተኞች ይመለከታል። ይሁን እንጂ ምንጮች እንደሚያመለክቱት የኢትዮጵያ ስደተኞችን በእጅጉ ማስደንገጡ ኣልቀረም።
በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በደቡባዊው የኣገሪቱ ድንበር በኩል ወደ ሳውዲ አረቢያ እንደሚገቡ እና በየቀኑም ወደ ሪያድ እና ጂዳ በሚያቀኑ ጎዳናዎች ላይ በርካቶች እንደሚያዙ ዘገባዎች ያመለክታሉ። ኣምልጠው ወደ ከተሞቹ የሚገቡት ቁጥርም በዘገባዎቹ መሰረት ቀላል ኣይደለም። ከገቡ በኃላም በተለይ ሴቶች የቤት ሰራተኞች በኣሰሪዎቻቸው ከፍተኛ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ሲነገር ቆይተዋል። ለሞት የተዳረጉም እንደነበሩ ኣይዘነጋም።

ጃዕፈር አሊ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic