ስለ የአፍሪቃ ነፃ የንግድ ቀጠና የአኅጉሪቱ ሥራ አስፈፃሚዎች ምን ይላሉ? | ኤኮኖሚ | DW | 27.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

ስለ የአፍሪቃ ነፃ የንግድ ቀጠና የአኅጉሪቱ ሥራ አስፈፃሚዎች ምን ይላሉ?

የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ተግባራዊ ለመሆን አንድ አገር ብቻ ይጠብቃል። ቀጠናውን ለመመስረት ስምምነታቸውን በፊርማ ካረጋገጡ አገሮች መካከል 21ዱ በየአገሮቻቸው ምክር ቤት አቅርበው አፅድቀዋል። ኤርትራ፣ ታንዛኒያ እና ናይጄሪያ ግን ቸልተኛ ሆነዋል። 2.1 ቢሊዮን ሸማቾች ይኖሩታል የተባለው ነፃ የንግድ ቀጠና ግን ጥያቄዎች አላጡትም

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:27

ስለ የአፍሪቃ ነፃ የንግድ ቀጠና የአኅጉሪቱ ሥራ አስፈፃሚዎች ምን ይላሉ?

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ያጸደቀው የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለመግባት የአንድ አገር ውሳኔ ብቻ ይጠብቃል። ስምምነቱን 52 አገሮች ሲፈርሙ 21 በየአገሮቻቸው ምክር ቤት አጽድቀዋል። ኤርትራ፣ ናይጄሪያ እና ታንዛኒያ ጉዳዩን ወደ የምክር ቤቶቻቸው ማቅረብ ቀርቶ ሰነዱን ለመፈረም እንኳ ዳተኛ ሆነዋል።

ይኸ ውል 55ቱን አፍሪካውን አገሮች በአንድ ለማገበያየት ተስፋ ተጥሎበታል። የአፍሪካ ኅብረት መረጃ እንደሚጠቁመው ከአጠቃላይ የአኅጉሪቱ ግብይት 15% በመቶ ብቻ እስር በርስ በአገሮች መካከል ይደረጋል። ይኸ የአውሮጳ፣ እስያ፣ ሰሜን አሜሪካ እና ላቲን አሜሪካ አገራት ካላቸው የርስ በርስ ግብይት ያነሰ ነው።

እንደ ታቀደው ከተሳካ አጠቃላይ አመታዊ የምርት መጠናቸው 3.4 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ 1.2 ቢሊዮን ሸማቾች ይኖሩታል። ለአኅጉሪቱ ዜጎች ከአንዱ አገር ወደ ሌላው በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ያጎናፅፋል።  ይኸ ሁሉ ግን በበርካታ ጥብቅ ድርድሮች የሚወሰን በተለይ በመሪዎች ተስፋ የተጣለበት ውጥን ነው። የምጣኑ ሐብት ተንታኞች እና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች በስምምነቱ አስፈላጊነት ቢስማሙም ተግባራዊነቱ ላይ በርካታ ጥያቄዎች አሏቸው።

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ በኪጋሊ በተካሔደው የአፍሪካ ሥራ አስፈፃሚዎች የውይይት መድረክ የተሳተፉት ናይጄሪያዊው አብዱልሰመድ ራቢዩ ምንም እንኳ አገራቸው የአፍሪካ አኅጉራዊ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ለመፈረም ዳተኛ ብትሆንም ለፋይዳው ግን ጥርጣሬ የላቸውም።

ከአባታቸው በወረሱት ሐብት  ያቋቋሙት የግል ኩባንያ  ስኳር፣ ብረታ ብረት እና ሩዝ ለናይጄሪያ ከዓለም ገበያ በማቅረብ ይታወቃል። መቀመጫውና በሌጎስ ከተማ ያደረገው እና በዋና ሥራ አስፈፃሚነት የሚመሩት ቡዋ ግሩፕ በወደብ አስተዳደር፣ ዱቄት እና የምግብ ዘይት ማምረት፤ ነዳጅ እና ጋዝ ንግድ የተሰማራ ኩባንያ ነው። የአፍሪካን በተለይም የምዕራቡን ገበያ ጠንቅቀው የሚያውቁት አብዱልሰመድ ራቢዩ ታዲያ ነፃ የንግድ ቀጠና ተግባራዊነት በአገራቸው የተነሳበት ጥያቄ ችላ ሊባል እንደማይገባ ተናግረዋል።

አብዱልሰመድ ራቢዩ "የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና አሁን ባለው መዋቅር ስምምነቱ ያልፈረመችው ናይጄሪያን መሰል አንዳንድ አገሮችን ተጠቃሚ አያደርግም። ይኸ አንድም አገሪቱ ካላት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ጋር ይገናኛል። የአገሪቱ ገበያ ከውጭ በምትሸምተው ላይ ጥገኛ መሆኑ ሌላው ጉዳይ ነው። ናይጄሪያ ጉዳዩን የሚመረምር ኮሚቴ አዋቅራለች። ካልፈረመችባቸው ምክንያቶች አንዱ በቀጣናው አገሮች መካከል ወጥ የቀረጥ ሥርዓት ለመፍጠር፣ የታክስ ክፍያዎች ለማስቀረት እና የአባል አገራቱን ምርቶች ለመጠበቅ   በምዕራብ አፍሪካ የኤኮኖሚ ማኅበረብ ስምምነት ሥር የተፈረመ ውል አለ። አንዳንድ አባል አገራት ሥራ ላይ ከዋለ ጥቂት ጊዜ ያስቆጠረውን ይኸን ስምምነት እያከበሩ አይደለም። በናይጄሪያ ያመረቱትን በቤኒን መሸጥ ያልሆነላቸው ኩባንያዎች አሉ። ቡርኪና ፋሶ፣ ቤኒን፣ ኒጀር እና ቻድ የዚህ ስምምነት ፈራሚ ቢሆኑም እኛ በናይጄሪያ ያመረትንውን ስሚንቶ በእነሱ ገበያ መሸጥ አንችልም። በናይጄሪያ ከሚያስሳበን ጉዳይ አንዱ በክፍለ አኅጉሩ የተፈረመው ስምምነት ካልተከበረ ግዙፉ የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና እንዴት ሊሰራ ይችላል የሚለው ጉዳይ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ ባሻገር ናይጄሪያ ሌሎች አገሮች ቻይናን ከመሰሉ አገሮች በሚሸምቱት ሸቀጥ ገበያዬን ይጎዳሉ የሚል ሥጋት ጭምር አላት። "ናይጄሪያ ከ200 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አላት። በርካታ ሸቀጦች ከሌሎች አገሮች ትሸምታለች። ድንበሮቻችንን በዚህ ስምምነት ክፍት ስናደርግ ሌሎች አገሮች ከቻይና የሚሸምቱትን ሸቀጥ በናይጄሪያ ላለማራገፋቸው ምን ማረጋገጫ አለን?" ሲሉ ይጠይቃሉ በኪጋሊው የውይይት መድረክ የተሳተፉት አብዱልሰመድ ራቢዩ። 

ናይጄሪያውያኑ ፖለቲከኞች እና ነጋዴዎች ከተጫናቸው ሥጋት ባሻገር ባለሙያዎች የሚያነሷቸው የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ፈተናዎች በርካታ ናቸው።ቀዳሚው በአፍሪካ አገሮች መካከል የሚታየው የምጣኔ ሐብት ልዩነት ነው። ከአፍሪካ አጠቃላይ የምርት መጠን 50 በመቶውን የተቆጣጠሩት ግብፅ፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው። ስድስቱ የአፍሪካ ሉዓላዊ የደሴት አገሮች ከአኅጉሪቱ አጠቃላይ የምርት መጠን ያላቸው ድርሻ ግን 1 በመቶ ብቻ ነው። እንደ ደቡብ ሱዳን ያሉ አገሮች ያላቸው መሠረት ልማት ከደቡብ አፍሪካ ቀርቶ ከጎረቤት ኢትዮጵያ አይወዳደርም። አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች የዜጎቻቸውን የስራ ፍላጎት የተሸከመው ኋላ ቀሩ ግብርና ነው። አነስተኛ የእርሻ ባለቤቶች ከግዙፍ እና ውስብስብ የግብርና ሥራዎች ጋር መወዳደር የመቻላቸው ነገር አጠራጣሪ ነው። አፍሪካውያን ሸማቾች ርካሽ ምርቶች መፈለጋቸው አነስተኛ አምራቾች ከውጪ አገራት በሚገቡ ሸቀጦች ሊደቆሱ ይችላሉ የሚል ሥጋት ደቅኗል።

የግብጹ ቢሊየነር ናጉይብ ኦንሲ ሳዊሪስ የአፍሪካ አኅጉራዊ የንግድ ቀጠና ተግባራዊነት እንደ እርሳቸው ላሉ የግል ባለወረቶች የሚፈጥረው ዕድል አልጠፋቸውም። የናጠጡት ግብፃዊ በኪጋሊው የአፍሪካ ሥራ አስፈፃሚዎች የውይይት መድረክ አኅጉራዊው ነፃ የንግድ ቀጣና መሬት ወርዶ ተግባራዊ ሲሆን እንደ እርሳቸው ያሉ ባለወረቶች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ጠቃቅሰው ነበር።

ሳዊሪስ "ፈተናዎቹ የሚመጡት ተግባራዊ ሲደረግ ነው። መንግሥታት አንዳች ስምምነት ፈርመው ሥራ ለመስራት ስንጀምር እና ቢሮክራቶች ተግባራዊ ማድረግ  ሲጀምሩ ችግሩ ይፈጠራል። መንግሥታት ለስራ ስንቀርባቸው ትርፍ አጋብሰን የምንጠፋ ይመስላቸዋል። ሥራ ፈጣሪዎች ውጥናቸው መጥፎ ነው የሚል ጥርጣሬ አላቸው። ነገር ግን የሥራ ፈጣሪው ውጥን መጥፎ አይደለም። እርግጥ ነው ማትረፍ ይፈልጋሉ ነገር ግን በሚሰሩበት አገር ሥራ እና ሐብት ይፈጥራሉ። እንደ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ያሉ መንገዱን ሊጠርጉ ይገባል። እኔ ለምሳሌ በማዕድን ፍለጋ፣ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ በባንኮች እና የቴሌኮም ኩባንያዎች ተሰማርቻለሁ። እዚህ አገር መጥቼ በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለመሰማራት ብፈልግ ለገዢዎች ብድር የሚያቀርብ ተቋም የለም። የገነባኋቸውን መኖሪያ ቤቶች እንዴት ልሸጥ ነው? ለእንዲህ አይነት ችግሮች መፍትሔ የሚፈጥር መንገድ ቢገኝ፤ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ይኸን ቢያመቻች የሚያስፈልገኝ መጥቼ ቤቶቹን መገንባት እና መሸጥ ብቻ ይሆናል። በቃ ወደ ሥራ ገባሁ ማለት ነው" ብለዋል። 

በኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሐብት ፕሮፌሰሩ ካርሎስ ሎፔዝ ሕንድ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ጀርመን በአፍሪካ ባላቸው መዋዕለ-ንዋይ ከፈጠሩት የሥራ ዕድል ይልቅ የደቡብ አፍሪካ እና ሞሮኮ እንደሚልቅ ተናግረዋል። የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኤኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ የነበሩት ካርሎስ ይኸን ምሳሌ ያቀረቡት የአኅጉሪቱ አገሮች የርስ በርስ የንግድ ልውውጥ የሚኖረውን ፋይዳ ሲያስረዱ ነው።

ካርሎስ ሎፔዝ"በአፍሪካ አገሮች መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ በመሠረታዊነት እሴት በተጨመረባቸው ምርቶች ላይ ነው። አኅጉሪቱ ከአፍሪካ ውጪ የምታደርገው ግብይት ግን ሸቀጥ ላይ የተንጠለጠለ ነው። ይኸ እሴት ላይ ያተኮረ ሊሆን ይገባል። ይኸ የሚሆን አስፈላጊው መዋዕለ ንዋይ ተግባራዊ ሲሆን ነው። አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠናውን መተግበር ስለሚኖረው ፈተና አንድ ምሳሌ ላቅርብ። በአንዳንድ የአፍሪካ ድንበሮች ሰነዶች ለማስጨረስ እስከ 700 ሰዓታት ይፈጃል። የገቢ እና ወጪ ንግድ ሰነዶች ለማሰራት ባ,ንዳንድ አገሮች በቀን እስከ 2 ሺሕ 500 ዶላር ይጠይቃል።  ይህ ተቀባይነት የለውም። የንግድ ልውውን መልክ የማስያዝ ችግሮች አሉብን። ነገር ግን የመሰረተ ልማት ችግርም አለ። ከአንድ የአፍሪካ አገር ወደ ሌላው ምርቶች ለመላክ ያለው ፈተና እጅግ አስከፊ ነው። አንድ ምርት ከዚህ ሞምባሳ ከመላክ ይልቅ ከሞምባሳ ቻይና መላክ ርካሽ ነው። ይኸ ፈፅሞ ሊቀጥል አይገባም" ሲሉ ለተሰብሳቢዎች ተናግረዋል። 

አፍሪካ የቤት ሥራዋን በአግባቡ ካጠናቀቀች ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት እነዚህ ሁሉ እንከኖች መፍትሔ ያገኛሉ። እስካሁን በንግድ ድንጋጌዎች እና በሸቀጦች ላይ የተደረሱ ስምምነቶች ቢኖሩም ጥብቅ ድርድር የሚጠይቁ ሥራዎች ግን ይቀራሉ። የቅጂ መብት ባለቤትነት፣ አንድ ምርት የተመረተበትን አገር የመለየት እና የየአገራቱን ታክስ ማጣጣም መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች ናቸው። ፕሮፌሰር ካርሎስ ሎፔዝ በሁለት አመታት ድርድር ከስምምነት ተደርሶ በአመት ውስጥ የተፈረመውን  አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ከሌሎች ተመሳሳይ ሒደቶች ሲያወዳድሩት በጥሩ መንገድ ላይ እንደሚገኝ እምነታቸው ነው። ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት እንደ አውሮጳ ኅብረት ያሉ ለመሰረቱት ወጥ ገበያ ድርድር እና ውይይት በአማካኝ እስከ አስር አመታት ወስደዋል።

የርዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ አፍሪካውያኑ ነጋዴዎችም ሆኑ ፖለቲከኞች ነፃ የንግድ ቀጣናውን ስኬታማ የማድረጉ ሥራ በራሳቸው ጫንቃ ላይ የወደቀ መሆኑን ጠቅሰው ኮፍጠን ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።

"ሰዎች የአፍሪካ አኅጉራዊ የንግድ ቀጠና በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል ካላደረጉት በቀር በራሱ ለችግሮች መፍትሔ አያመጣም። ከዚህ ቀደም የነበሩ ክፍለ አኅጉራዊ የንግድ ስምምነቶች ላይ ጫና ያሳደረ ጉዳይ ሁሉ በዚህም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ከዚህ ቀደም የነበሩ ስላልተሳኩ ይኸኛውም ውጤት አይኖረውም የሚል ነገር አይሰራም። አንዳች ስምምነት ላይ ደርሰን በራሴ ውጤት እንዲያመጣ መጠበቅ አይኖርብንም። ጥረት ይጠይቃል። ሰዎች ጥቅማቸውን ለማግኘት መስራት የሚገባቸውን መስራት ይኖርባቸዋል። ጥያቄ የማይነሳበት ነገር ሌሎች ክፍለ አኅጉራዊ ስምምነቶችም ይሁኑ የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና የሚኖራቸው ፋይዳ ነው። ምንም ሰው ትክክለኛው መንገድ ይኸ አይደለም አላለም። ለአኅጉራችን ልማት ጥቅም ዕድሉን ማሳደግ ካስፈለገ እውነቱን ለመናገር ብቸኛው መንገድ ይኸው ነው። ስለዚህ እንዲሰራ ልናደርገው ይገባል"

ከ70 በላይ ከሚሆኑ አገራት የተውጣጡ ከ1800 በላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በተሳተፉበት የአፍሪካ ሥራ አስፈፃሚዎች የውይይት መድረክ ኢትዮጵያን ወክለው የተገኙት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ናቸው። ፕሬዝዳንቷ እንደ ርዋንዳው አቻቸው ሁሉ አፍሪካ የርስ በርስ የንግድ ልውውጧን ከማጠናከር ውጪ አማራጭ የላትም ሲሉ ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነች። በታሪካችን በበርካታ ኤኮኖሚያዊ ቡድኖች ውስጥ ተሳትፈናል። ነገር ግን በአንዳንድ ዘርፎች  ተሳትፎ ብናደርግም ሙሉ በሙሉ አልነበረም። አንዳንድ ስምምነቶችን ማክበር ፈታኝ ነበር። ነገር ግን ከመዋሐድ ውጪ አማራጭ እንደሌለን ተረድተናል። ይህ በአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ረገድ ብቻ አይደለም። ከቅርብ ጎረቤቶቻችን በተለይም ከኤርትራ ጋር ያለንን ግንኙነት ለማሻሻል የወሰድንው እርምጃ በቀጠናው የተሻለ ውህደት እንደሚፈጥር ያሳያል። ትልቅ፣ የተረጋጋ ቀጠና እንዲኖረን ያግዛል። ስለዚህ አኅጉራዊ የኤኮኖሚ ውኅደት ለመፍጠር ወዳቀድንው መሰረታዊ መርኆ ከማምራት የተለየ አማራጭ ያለን አይመስለኝም"

ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ እና ኤርትራ መቼ አኅጉራዊውን ነፃ የንግድ ቀጣና እንደሚቀላቀሉ የታወቀ ነገር የለም። ቢያንስ ናይጄሪያ ጉዳዩን የሚመረምር ኮሚቴ በፕሬዝዳንቱ አማካኝነት አቋቁማለች። የአፍሪካ ሥራ አስፈፃሚዎች የውይይት መድረክ ፕሬዝዳንት አሚር ቤን ያሕመድ እንዳሉት ግን ፖለቲከኞቹ ዕቅዳቸውን ለማሳካት የግሉን ዘርፍ ቸል ሊሉት አይገባም።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic