ስለ ኦሮሚያ ክልል የሰብዓዊ ቀውሶች የኢሰመኮ መግለጫ | ኢትዮጵያ | DW | 08.12.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ስለ ኦሮሚያ ክልል የሰብዓዊ ቀውሶች የኢሰመኮ መግለጫ

በኦሮሚያ ክልል ግጭት ተባብሶ በቀጠለባቸው አከባቢዎች ባለፉት ስድስት ወራት እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሊባል የሚችል በመፈጸሙ በመንግስት በኩል አፋጣኝ እና ዘላቂ ምላሽን የሚመጣ ርምጃ እንደሚያሻው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዐስታወቀ።

እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተከስቷል ተባለ

በኦሮሚያ ክልል ግጭት ተባብሶ በቀጠለባቸው አከባቢዎች ባለፉት ስድስት ወራት እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት (grave violation of human rights) ሊባል የሚችል በመፈጸሙ በመንግስት በኩል አፋጣኝ እና ዘላቂ ምላሽን የሚመጣ ርምጃ እንደሚያሻው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዐስታወቀ። ኮሚሽኑ ትናንት ባወጣው መግለጫ የተለያዩ ተዋንያን ይሳተፉበታል ባለው የኦሮሚያው የተለያዩ አከባቢዎች ግጭት፤ ንጹሃንን እያፈናቀለና ለሰፋፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየዳረገ ነው። ሥዩም ጌቱ 

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በየጊዜው በሲቪል ሰዎች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት የተከሰቱ መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውሶችን በማስመልከት ትናንት አመሻሹን ባወጣው መግለጫ፤ በክልሉ በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ፣ የአካል ጉዳት እና መፈናቀል ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሊባል የሚችል በመሆኑ መንግሥት አፋጣኝ እና ተጨባጭ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል እርምጃ እንዲወስድ የሚሻ ነው ብሏል፡፡ 

በከዚህ ቀደም ሪፖርቱ በመላ አገሪቱ በሕይወት የመኖር መብት እጅግ የከፋ አደጋ ውስጥ መውደቁን፤ በተለይም በኦሮሚያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የታጣቂ ኃይሎች እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሰላማዊ ሰዎችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለመፈናቀል፣ ለዘረፋ እና ለንብረት ውድመት እንደሚዳሪጉት መግለጹን ያስታወሰው ኮሚሽኑ፤ ያ ሪፖርት ይፋ ከተደረገበት ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. ወዲህ እስከ ተሰናባቹ ህዳር ወር ድረስም በኦሮሚያ ግጭቶችና በግጭቱ የሚደርሱ ጥቃቶች መሻሻል እንዳላሳዬ ባደረገው ክትትል ማረጋገጡን አመልክቷል። 

Infografik Karte Äthiopien AM

የኢትዮጵያ ካርታ


በተለይም በወለጋ እና የሸዋ ዞኖች፣ በሁለቱ የጉጂ እና አርሲ ዞኖች እንዲሁም በኢሉ አባቦራ እና በቡኖ በደሌ ግጭቶችና ጥቃቶቹ ተባብሰው መቀጠላቸውን ኮሚሽኑ በምርመራው አረጋግጧል፡፡

ለአብነትም በምሥራቅ ወለጋ ዞን ዴጋ፣ ሳሲጋ፣ ጊዳ አያና፣ ኪረሙ፣ ጉትን፣ ሊሙ እና ጅማ አርጆ ወረዳዎች፤ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ (አሊቦ፣ ጃርደጋ እና ጃርቴ ከተሞች)፣ አሙሩ፣ ሆሮ ቡልቅ እና ጉዱሩ ወረዳዎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች በቁጥር መጨመር ወይም የመወሳሰብ አዝማምያ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶቹን ደረጃ በበቂ ሁኔታ መመርመር እንኳ እንዳላስቻለ  ነው ኮሚሽኑ የገለፀው፡፡

ይሁንና በኮሚሽኑ ክትትል መሰረት በተለያዩ ወቅቶች በእነዚህ አካባቢዎች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች፣ እንዲሁም በመንግሥት እራሳቸውን እንዲከላከሉ በሚል የታጠቁ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከሌሎች ክልሎች ጭምር እንደመጡና በተለምዶ በአካባቢው የአማራ ታጣቂዎች የሚባሉ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ይንቀሳቀሳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማሳሰቢያ

በኮሚሽኑ የአከባቢው ክትትልና ምርመራ ዳይረክተር ኢማድ አብዱልፈታ በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩትም እነዚህ የታጠቁ ተዋንያን ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር በሚያደርጓቸው ውጊያዎች፣ በሌላ ወቅት በተናጠል በሚያደርሷቸው ጥቃቶች የተወሳሰበ ሰብዓዊ መብት ጥሰትን ይፈጽማሉ ብለዋል። 
በታጣቂ ቡድኖች ቁጥጥር ስር በዋሉ አካባቢዎች ደግሞ አፈናዎች፣ “መንግሥትን ወይም ሌላኛውን የታጣቂ ቡድን ትደግፋላችሁ ወይም የመንግሥት ኃላፊ ናችሁ ወይም መረጃ አቀብላችኋል” በሚል የሚደርሱ ግድያዎች፣ ዝርፊያዎች፣ ሌሎች ጥሰቶች፣ በግዳጅ የሚጠየቁ የገንዘብ ክፍያዎች የአካባቢዎችን ነዋሪዎችና ማኅበረሰብ ከግጭቶቹና ከጥቃቶቹ ባልተናነሰ ለስቃይ የዳረጉ መሆናቸውን ኮሚሽኑ ከተጎጂዎች አረጋግጧል።  

በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችም “ታጣቂ ቡድን ትደግፋላችሁ” በሚል ከፍርድ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ በሲቪል ሰዎች የመኖርያ ሰፈሮች አቅራቢያ የተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች፣ ሕገ ወጥና የዘፈቀደ እስሮች ይፈጸማሉም ብሏል ኢሰመኮ በመግለጫው፡፡

Äthiopien l Gebäude Ethiopian Human Rights Commission( EHRC)

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሕንጻ ዓርማ

በተለያዩ ጊዜያት ኮሚሽኑ ለመንግስት የሚያቀርባቸው ምክረ ሃሳቦች ፍትህ በማስፈን ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እንዲቻል የሚረዱ ቢሆኑም በዚህ ረገድም የመጣው ለውጥ አመርቂ አለመሆኑን ነው የኮሚሽኑ አከባቢያዊው የምርመራ ዳይሬክተሩ አቶ ኢማድ የሚገልጹት፡፡ 

የእርዳታ እና መሰረታዊ የአገልግሎት ተቋማት ተደራሽነት ግጭት በተከሰተባቸው አከባቢዎቹ አለመድረሳቸው የማህበረሰቡን እንግልት እንዳባባሰም ነው ኮሚሽኑ የገለጸው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ሆን ተብሎ ሲቪል ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ በተለይም ብሔርን እና የፖለቲካ አመለካከትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙም ኢሰመኮ በምርመራው አረጋግጧል፡፡

እንደ ኮሚሽኑ መግለጫ ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. እስከ ኅዳር ወር 2015 ዓ.ም. ግጭት በተባባሰባቸው የኦሮሚያ ክልል አከባቢዎቹ፤ መቶዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፣ ብዛታቸው የማይታወቅ ሰዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሚኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለዋል። የመንግሥት የፀጥታና የአስተዳደር አባላት ተገድለዋል፣ የመንግሥት እና የሲቪል ሰዎች ንብረቶች ተዘርፈዋል፣ መሰረታዊ አገለግሎቶችም ተቋርጠው፤ በነዚህ ባለፉት ስድስት ወራት እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በመፈጸሙ ዘላቂ ምላሽን ይሻል ብሏል ኮሚሽኑ፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ
 

Audios and videos on the topic