ስለ ኦሮሚያው ተቃውሞ የሂዩመን ራይትስ ዋች ዘገባ | ኢትዮጵያ | DW | 16.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ስለ ኦሮሚያው ተቃውሞ የሂዩመን ራይትስ ዋች ዘገባ

የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች በዚህ ዓመት በተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች የተካሄደውን ተቃውሞ ለማፈን በወሰዱት እርምጃ ከ400 በላይ ተቃዋሚዎች መገደላቸው እና ከ10 ሺህዎች በላይ ደግሞ መታሠራቸውን ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂዩመን ራይትስ ዋች ዛሬ ባወጣው ዘገባ አስታወቀ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:32

የሂዩመን ራይትስ ዋች ዘገባ

ድርጅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት በወቅቱ በተፈፀመው ግድያ የዘፈቀደ እሥር እና ሌሎች በደሎች ላይ በአስቸኳይ ተዓማኒና ገልለተኛ ምርመራ እንዲያካሂድም ጠይቋል። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጉዳዮች ተመራማሪ ፊሊክስ ሆርን የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች ይህን መሰሉን እርምጃ እንዲያወግዙም ጥሪ አቅርበዋል። ዛሬ ይፋ የተደረገው የሂዩመን ራይትስ ዋች ባለ 61 ገጽ ዘገባ ካለፈው ኅዳር አንስቶ እስከ ግንቦት በአዲስ አበባ እና በኦሮምያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ላይ በኦሮሚያ የተለያዩ ክልሎች የተነሳውን ተቃውሞ ለማክሸፍ መንግሥት የወሰደው እርምጃ መጠነ ሰፊ እና አላስፈላጊ እንደነበር ገልጿል። ዘገባው መንግሥት በወቅቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ገዳይ ኃይል መጠቀሙን ያብራራል። በመቶዎች ለሚቆጠር ጊዜ በተካሄዱት በርካታ ተቃውሞዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች ተቃዋሚዎችን ለመበተን ጥቂት ማስጠንቀቂያ ብቻ በመስጠት ወይም ያለምንም ማስጠንቀቂያ መተኮሳቸው እና በየሰልፎቹ ላይ ከተካፈሉት መካከል አንድ ወይም ከዚያ በላይ ተቃዋሚዎች ይገደሉ እንደነበር ገልጿል። የሂዩመን ራይትስ ዋች የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጉዳዮች ተመራማሪ ፊሊክስ ሆርን ድርጅታቸው በደል የደረሰባቸውን፣ የዓይን ምስክሮችና ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩ ሰዎችን በመጠየቅ ደረስኩበት ያለውን ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
«ወደ 400 እንደሚሆኑ የተገመቱ ሰዎች እንደተገደሉ ከ10 ሺህ በላይ የሚቆጠሩ እንደታሠሩ ከመካከላቸውም አብዛኛዎቹ በኋላ እንደተፈቱ ሆኖም አሁንም በርካቶች በእሥር ላይ እንዳሉ ደርሰንበታል። ስለዚህ ተቃውሞውን ለማክሸፍ

Menschenrechte Logo human rights watch

የተወሰደው እርምጃ በኦሮምያ በቅርብ ዓመታት ያልተለመደ ነበር።»
በዘገባው ከተገደሉት መካከል ከ300 በላይ የሚሆኑት በስም መለየታቸውና የአንዳንዶቹንም ፎቶ እንዳለ ተገልጿል። እንደዘገባው ከተገደሉት አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ሲሆኑ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ሕጻናትም ይገኙበታል። የፌደራል ፖሊስና ጦር ሠራዊትም በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን መምህራንን ሙዚቀኞችን ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን የጤና ባለሞያዎችን እንዲሁም ለሚሸሹ ተማሪዎች እገዛ ያደርጉ የነበሩ እና ከለላ የሰጧቸውን ሰዎችን ማሠሩም በዘገባው ተብራርቷል። ከታሠሩት አብዛኛዎቹ የተፈቱ ሲሆን ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ደግሞ ክስ ሳይመሰረትባቸው አሁንም በእስር ላይ እንዳሉ እና ከሕግ አማካሪም ሆነ ከቤተሰብ አባላት ጋር እንደማይገናኙም የሂዩመን ራይትስ ዋች ዘገባ ያስረዳል። የኢትዮጵያ የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ስለዚሁ ጉዳይ ያቀረበውን ዘገባ የኢትዮጵያ ፓርላማ ማጽደቁን በዚሁ ዘገባ መሠረትም በኦሮምያው ተቃውሞ ወቅት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 173 መሆኑን ከመካከላቸውም 28ቱ የፀጥታ ኃይሎች ናቸው ማለታቸውን አሶስየትድ ፕሬስ ዘግቧል። መንግሥት ተመጣጣኝ

Karte Äthiopien englisch

ያልሆነ ኃይል አልተጠቀመም ሲሉም ማስተባበላቸው ተገልጿል። ሆኖም ሆርን በወቅቱ የተፈጸሙት ግድያዎችም ሆነ ሌሎች በደሎች በገለልተኛ ወገን አልተጣሩም ይላሉ።
«የፀጥታ ኃይሎች በኅዳር ወር የተጀመረው ተቃውሞ በቀጠለበት ጊዜ በሙሉ ከፍተኛ መጠን ያለው ገዳይ ኃይል ተጠቅመዋል። በወቅቱ ስለተፈፀሙት በደሎች እስካሁን ድረስ ተዓማኒና ገለልተኛ ምርመራ አልተደረገም። በድርጊቱ ተጠያቂ የሆኑትን የመያዝ ሙከራም አልተደረገም።»
በዚሁ ዘገባ በተቃዋሚዎች አመፅ፣ በውጭ ዜጎች የተያዙ እርሻዎች መውደማቸው የመንግሥት ሕንፃዎች እና ንብረቶች መዘረፋቸውን እና መውደማቸው ተጠቅሷል። ይሁንና ከኅዳር ወዲህ ከተካሄዱት ከ500 በላይ ተቃውሞዎች ሂዩመን ራይትስ ዋች ምርመራ ካካሄደባቸው ከ62 ቱ አብዛኛዎቹ ሰላማዊ እንደነበሩ ገልጿል። ድርጅቱ ደረሱ ስለተባሉት በደሎች ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ያገኘው መረጃ ምን ይሆን?
«በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ መንግሥት ራሱን እንዲከላከል ዕድል ለመስጠት ሞክረናል። ሆኖም እንዳለመታደል ሆኖ ስለነዚህ ክሶች ለሂዩመን ራይትስ ዋች በይፋ ለመናገር ፈቃደኛ አልሆኑም። »
ሂዩመን ራይትስ ዋች ለኦሮሚያ ተቃውሞ የኢትዮጵያ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ላይ ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ከእስካሁኑ የበለጠ ጠንካራ ምላሽ እንዲሰጥ፣ እነዚህን ከባድ በደሎችም የተመ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት መመልከት እንደሚገባው አሳስቧል። ሆርን ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ይዞታ እንዲሻሻል የሚጠይቅበትን መንገድ እንዲቀይር ጠይቀዋል።
«የአውሮጳ ፓርላማን ጨምሮ የኢትዮጵያ ወዳጅ ከሆኑ ወገኖች ጠንካራ መግለጫዎች ሰምተናል። ሆኖም ይህ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻል ለረዥም ጊዜ ሲጠቀሙበት የቆዩት ዝምተኛ ዲፕሎማሲ ነው። የኢትዮጵያ ወዳጆች የዝምታ ዲፕሎማሲ ሲከተሉ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ይዞታ እየተባባሰ ነው የሄደው። ስለዚህ እንደ እነዚህ ዓይነት በደሎች በጥብቅ ሊወገዙ የሚገባበት ጊዜ አሁን ነው።»

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic