ስለ አዲስ አመት ዕቅድ ሳይንስ ምን ይላል?
ረቡዕ፣ መስከረም 1 2017አዲስ ዓመት አዲስ ጅምር ነው። አዲሱ ዓመት ሲጀምር በሕይወታችን ውስጥ ለውጦችን ማድረግ እንዳለብን ይሰማናል። በአዲስ መንገድ መጀመር፣ አዲስ ነገር ማድረግ እና ከአሮጌ ልምዶች እና ችግሮች መሰናበት እንፈልጋለን።ለዚህም በአዲስ አመት አዳዲስ እቅዶችን እና አዲስ መፍትሄዎችን ማዘጋጀትም እንጀምራለን።
ከዚህ አንፃር አሮጌ አመት ተሸኝቶአዲስ ዓመት ሲተካ አዳዲስ ዕቅዶችን መንደፍ በተለያዬ የዘመን አቆጣጠር አዲስ ዓመትን በሚያከብሩ ሁሉ የተለመደ ነገር ነው። ሰዎች ክብደታቸውን ለመቀነስ፣ ጤናማ አመጋገብ ዘዴን ለመከተል ፣ ገንዘብ ለመቆጠብ፣ መፃህፍትን ለማንበብ፣ ከሱስ ለመውጣት ወዘተ እቅድ ያወጣሉ።
ህይወትን ከመመርመር የአእምሮ ተግባር ጋር ይያያዛል
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሥነ-አዕምሮ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ እንዲሁም የሪኔሳንት/Renascent/ የአዕምሮ ጤና እና የሱስ ማገገሚያ ማዕከል መስራች የሆኑት ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ ጉዳዩ ከእእምሮ ጋር ይያያዛል ይላሉ።«እንግዲህ አዲስ ማለት የመጀመሪያ ነው።ለሚጀመረው አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ነው።ስለዚህ ሰዎች ቆም ብለው ያለፉትን አንድ አመት ውስጥ ያሉትን ቀናት በህይወታቸው ምን ምን እንዳለፈ በመመርመር በተለይ ደግሞ ሰዎች የአዲስ ዓመት ዕቅድ ሲያቅዱ ጉድለቶቻቸው ላይ ነው የሚያተኩሩት።እና ሃሳቡ እንግዲህ አዲስ የሚለው አዲስ ጅማሮን መሻሻልን ይመኛሉ።እንግዲህ ይህ የሰው ተፈጥሮ ነው። ሰው ሁል ጊዜ አዲስ ነገር ይፈልጋል። ህይወቱን ማሻሻል ይፈልጋል ጤናውን ማሻሻል ይፈልጋል።እነዚህ እነዚህ ነገሮች እንግዲህ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ በአዲሱ አመr ሰዎች የጎደላቸውን ነገር በተሻለ ሁኔታ ለማሟላት የሚከተሉት ነው።እንግዲህ ይህ አንዳንድ ጽሁፎችንም እንዳየሁት ለበርካታ አመታት ሰዎች ይህንን ተግባር ሲፈጽሙት ቆይተዋል።እንግዲህ ከዚያው ጋር ተያይዞ ማህበራዊ መሰረትም አለው።ነገር ግን ከአእምሮ ጋር የሚያያዘው ደግሞ ሰልፍ ሪፍሌክሽን የምንለው ራስን የማየት ህይወትን የመመርመር የማዳመጥ ይህ ተሳክቶልኛል ይህ ጎሎኛል የሚለውን ስለሚያካትት ቀጥታ ከአእምሮ ጋር ይያያዛል።» በማለት ፕሮፌሰር ሰለሞን አብራርተዋል።
የአዲስ ዓመት ዕቅድ ታሪካዊ አመጣጥ
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ4,000 ዓመታት በፊት የጥንቶቹ ባቢሎናውያን የአዲስ ዓመት ዕቅድ እና ውሳኔዎችን በማድረግ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች እንደነበሩ ይነገራል። ለእነርሱ አዲሱ አመት የሚጀምረው በመጋቢት አጋማሽ ላይ ሰብላቸው ከተዘራ በኋላ ሲሆን፤ የአዲስ አመት ክብረ በዓላትን በዚሁ ወቅት ያከብራሉ። በተመሳሳይም በጁሊየስ ቄሳር የግዛት ዘመን የጥንቶቹ ሮማውያን በተምሳሌታዊ መንገድ ያለፈውን ዓመት ወደ ኋላ እና ወደ ፊት ይመለከታል ብለው ለሚያምኑት ለግሪኩ አምላክ ጃኑስ ክብር ሲሉ ጥር 1 ቀን አዲሱን ዓመት ያከብራሉ። አዲሱን ዓመት ለማክበር ሮማውያን መስዋዕቶችን በማቅረብ ለሚመጣው አመት መልካም ስራዎችን ለመስራት ቃል ይገባሉ።
ሰዎች በአዲስ ዓመት ለምን ያቅዳሉ?
ኢትዮጵያውያንም መስከረም 1 ቀንን በዘመን መለወጫነት ለዘመናት እያከበሩት ይገኛሉ። በዚህ ሁኔታ በዓለም ዙሪያ ያሉ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአዲስ ዓመትን ከአዲስ ዕቅድ እና ተስፋ ጋር ያከብራሉ። ይህም ተመራማሪዎች እንደሚሉት የሰው ልጆች ለመለወጥ ያለውን ዓለማቀፋዊ ፍላጎት ያሳያል።እንደ ፕሮፌሰር ሰለሞን ለውጥ ደግሞ ራስን ከማየት ይጀምራል።ራስን ማየት ወይም ስለ ራስ ማሰላሰል/Self-reflection/ ግለሰቦች ራሳቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዲረዱ እና በሕይወታቸው ውስጥ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያደርጉ የሚረዳ ጠቃሚ የአእምሮ ተግባር ነው።አዲሱ አመት ደግሞ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ያለፈውን አመት ለማሰላሰል ፣ ግቦችን ለመንደፍ እና እነሱን የሚያሳካ እቅድ ለማውጣት የተመቼ ።መሆኑን ፕሮፌሰር ሰለሞን ገልፀዋል። «ሰዎች አዲሱን ዓመት የአዲስ ህይወት ጅማሬ፣ የአዲስ ልምምድ ጅማሬ አድርገው ይወስዱታል ሁለተኛ ደግሞ ጉድለቶቻቸውን የማስተካከል የማረም ጅማሬም አድርገው ስለሚወስዱት ካለንደሩም ለምሳሌ መስከረም አንድ አንደኛው ወር 2017 ይላል የኛ ካሌንደር።ስለዚህ የ2017 የመጀመሪያው ቀን ነው ማለት ነው። እና በአመቱ ጅማሬ ይህንን አከናውናለሁ ይህን አስተካክላለሁ ይህን እጨምራለሁ የሚለው ነገር የዕቅድ መጀመሪያ ነው።ብሎ መውሰድ ይቻላል። ከግለሰብ አንፃር ህይወታቸውን ይመረምራሉ ከዚያ ደግሞ በአመቱ ምን አሳካለሁ ምን አገኛለሁ ወዴት እደርሳለሁ የሚለውን ማሰብ በውስጣችን ያለ ተፈጥሮ ነው ብዙሃኑ ጋ ማለት ነው።ብዙም ትዝ የማይላቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ።ግን ቀላል ቁጥር የሌለው ሰው አዲስ ዓመት ሲመጣ አመቱን እንዴት ነው የማሳልፈው? ምንድ ነው የማከናው ነው?መቀየር ያለብኝ፣ ማስተካከል ያለብኝ፣ መጨመር ያለብኝ የሚለውን ነገር ለማሰብ እድል የሚሰጥ ነገር ነው።»በማለት ገልፀዋል።
40 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች በአዲስ ዓመት ያቅዳሉ
የማህበራዊ ሥነልቡና ባለሙያዎች እንደሚሉት የአዲስ ዓመት ውሳኔዎችን እንዲወስኑ ሰዎችን ከሚያበረታታቸው ነገሮች አንዱ እንደ አዲስ በመጀመር፣ከዚህ በፊት ያልተሳኩ ግቦችን ወደ ጎን በመተው እንደገና ለመሞከር ዕድል በመስጠቱ ነው።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሰዎች በዚህ ተነሳስተው የለመዱትን ነገር ለማቆም ወይም አዲስ ልምምድ ለመጀመር የሚወስኑት በዚሁ በአዲስ ዓመት ነው። ፕሮፌሰር ሰለሞንም እሳቸው በሚሰሩበት የሱስ ማገገሚያ ማዕከል ይህንን ልብ ብለዋል።
ነገር ግን ብዙውን ጊዜ እነዚህ ዕቅዶች የመሳካት ዕድላቸው ዝቅተኛ መሆኑ ይነገራል። እንደ «ሳይኮሎጂ ቱዴይ» የአዲስ ዓመት ውሳኔ ካደረጉ ሰዎች መካከል ከ10 በመቶ ያነሱት በትክክል ይሳካላቸዋል። ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ውሳኔውን ማድረግ ለምን እንደመረጡ እንኳን ማስታወስ አይችሉም።
ሌላው በስታቲስታ የተደረገ ጥናት፣ በ2018 የአዲስ ዓመት ውሳኔዎችን ካደረጉት ሰዎች ውስጥ አራት በመቶው ብቻ ዕቅዳቸውን አጥብቀው እንደያዙ ተናግረዋል። ለዚህም ከምክንያቶቹ አንዱ ብዙ ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች ወደ ህይወታችን መግባታቸው ነው። በተለይ ዘመኑ የዲጅታል ቴክኖሎጅ በመሆኑ ደግሞ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እና ቴክኖሎጂ በአሁኑ ወቅት የአዲስ ዓመት ዕቅድን ለማሳካት የበለጠ ከባድ ያደርጉታል።የሰው ልጅ አእምሮ በባህሪው ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮችን የመፈለግ አዝማሚያ አለው። የሚሉት ፕሮፌሰር ሰለሞን ለእቅዳችን ስኬትም ሆነ ውድቀት ግን አጠቃቀማችን ይወስነዋል ይላሉ።.«የሰው ልጅ ቴክኖሎጅ እና ፈጠራ ላይ የሚሰማራው ችግሮችን ለመፍታት ነው።ስለዚህ ቴክኖሎጅ በበጎ መልኩ ካየነው ህይወታችንን የሚያቀል የምንፈልገውን ነገር ያለድካም እንድናገኝ የሚያደርግ ነው ።ለምሳሌ እያንዳንዱ ሰው እጁ ላይ ስልክ አለው።በያዘው ስልክ ብዙ አይነት ስራ መስራት ይችላል።ህይወቱን የሚያቀሉ ነገሮችን።ከነዚህ አንዱ የባህሪ ለውጥን የሚያግዙ ብዙ አይነት «አፕሊኬሽኖች» አሉ።እነዚያን መጠቀም ይችላል።ህይወቱንም ወደ ተሻለ መንገድ ሊመራ ይችላል።ስለዚህ ቴክኖሎጅ ዋነኛ አላማው የሰውን ልጅ ወደ ኃላ መጎተት እና ማሰናከል ሳይሆን ማገዝ እና የህይወት ጥራትን መጨመር ነው ብዬ ነው የማምነው።እና እንዳጠቃቀማችን ነው።ብዙ »አፕሊኬሽኖች» አሉ ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣አመጋገብን ለመከታተል የሚረዳ እንቅልፍን ለመከታተል የሚረዳ፣የስራ አፈፃጸም ብቃታችንን የሚከታተል።»ብለዋል።
የአዲስ ዓመት እቅድን ለማሳካት መደረግ ያለባቸው ተግባራት
ተመራማሪዎች ውሳኔዎችን ለማስቀጠል ተጨባጭ ግቦችን ማውጣት አስፈላጊ ነው ይላሉ።ያም ሆኖ መጥፎ ልማዶችን በመተው፣አዳዲስ ጠቃሚ ልማዶችን መለማመድ ቀላል አይለም።ምክንያቱም ልማዶች የተወሳሰቡ እና ከሰዎች ባህሪ ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ናቸው።በመሆኑም ከዕቅድ ባሻገር የባለሙያ እገዛ ይጠይቃል።ሲሉ ያስረዳሉ።
እንደ ፕሮፌሰር ሰለሞን ህይወትን በዕቅድ መምራት ተገቢ በመሆኑ የሰው ልጅ አዲስ ዓመትን መጠበቅ የለበትም። ያም ሆኖ ከነ ጉድለቱም ቢሆን በአዲስ አመትም ቢሆን ማቀዱ ካለማቀድ የተሻለ መሆኑን ገልፀዋል።በአጠቃላይ የአዲስ ዓመት ዕቅድን ለማሳካት ለምን እንዳቀዱ ምክንያቱን በደንብ ማወቅ፣ ቀላል እና በተወሰነ ጉዳይ ላይ ማተኮር፣ወደ ተግባር ሊለወጥ የሚችል ማድረግ፣ ዕቅድን በተለያዩ ጌዜዎች በትንሽ በትንሹ መከፋፈል፣ውድቀትን አለመፍራት፣ባይሳካም እንደገና መሞከር እና ተስፋ ቆርጦ አለማቋረጥ፣ እና ትግስት ወሳኝ ነገሮች ናቸው።ሊለውጡት የሚፈልጉትን ነገር አጥብቆ መፈለግም ሌላው ጉዳይ መሆኑን ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ
ፀሐይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ