ስለኬንያ ምርጫ የኢትዮጵያውያን ታዛቢዎች አስተያየት
ኬንያ ባሳለፍነው ማክሰኞ ባከናወነችው ብሔራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃለማሪያም ደሳለኝ እና የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ ሌሎች ፖለቲከኞች እና የሲቪክ ተቋማት ተወካዮች በታዛቢነት ተሳትፈው ነበር፡፡
ዶይቼ ቬለ በምርጫው በታዛቢነት ከተሳተፉት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና የኢትየጶጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር (ኢሰመኮ) ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ትዝብታቸውን ተጋርቷል፡፡ እኚህ ሁለቱም ታዛቢዎች ዋና መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ባደረገው የሲቪል ተቋም አመቻችነትና ጋባዥነት ነበር በዓለማቀፍ የምርጫ ታዛቢነት የተሳተፉት፡፡
የኦፌኮው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ የደቡብ አፍሪካው የሲቪክ ተቋም በስምንት ቡድኖች ካሰማራቸው 40 ታዛቢዎች አንዱ ሆነው ነበር በአራት ቡድን በሞምባሳ የምርጫ ክልል የተሰማሩት፡፡ ፕሮፌሰር መረራ እንደሚሉት በዚያው እሳቸው በታዘቡበት የምርጫ ጣቢያ እና ሌላው ኪሱሙ በሚባል ግዛት የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት መሪው ራይላ ኦዲንጋ ሲመሩ እንደ ሪፍት ቫሊ ባሉ ግዛት ደግሞ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዊሊያም ሩቶ በለስ ሳይቀናቸው እንዳልቀረ አመልክተዋል፡፡
የኢሰመኮ ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለም ከአራት ቡድናቸው ጋር በመሆን በአራት የምርጫ ክልሎች ነበር ሂደቱን የታዘቡት፡፡ ናይሮቢ፣ ኪሱሙ፣ ሞምባሳ እና ኤልዶሬ ምርጫውን ከታዘቡባቸው አከባቢዎች ናቸው፡፡ ስድስት አይነት ምርጫዎች ከአገር መሪነት እስከ የአከባቢ ምክር ቤት አባልነት በተከናወነበት በባለፈው ማክሰኞው ምርጫ ፕሬዝዳንታዊ ፉክክሩ ልዩ ትኩረት መሳቡንም አንስተውልናል፡፡ ቀዝቀዝ ያለ የተመዝጋቢዎች ተሳትፎ ታይቶበታል የተባለው የኬንያው ምርጫ ከተመዘገቡት 22 ሚሊየን መራጮች ገደማ ከ60 በመቶ ያልበለጡ ብቻ ወጥተው መምረጣቸው ነው የሚነገረው፡፡
እንደ ዶ/ር ዳኒኤል ትዝብት በእለተ ምርጫው በነበረው ሂደት ግን ነጻ እና ፍጹም ሰላማዊ የመራጮች ተሳትፎ ተስተውሏል፡፡ በኬንያ ውስጥ በሁለት የምርጫ ዘመን የተገደበው የፕሬዝዳንትነት ስልጣን መከበሩ እና እስካሁን ሶስት ፕሬዝዳንቶች ስልጣናቸውን ለአሸናፊው በሰላም ማስረከባቸውም ለአፍሪካም ጭምር መልካም ልምድ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ፕሮፌሰር መረራ በፊናቸው የታዘቡትን ሲያጋሩን፡ መራጮች የተለየ አማራጭ ብለው ያሰቡት ተወዳዳሪዎች በምርጫው መሳተፋቸው ተሳትፎያቸውን ለማቀዘቀዙ ምክኒያት ሳይሆን እንዳልቀረ ነግረውናል፡፡ የኬንያ ተቀናቃኝ ፓርቲ ዋነኛው ሰው ራይዳ ኦዲንጋ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የሚያውቁ ሲሆን በተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ይደገፋሉ፡፡ ዊሊያም ሩቶም ቢሆኑ የአሁኑ ምክትል ፕሬዝዳንት እንደመሆናቸው ኬንያውያን ከአሁኑ ምርጫ ብዙም ለውጥ ላይጠብቁ እንደሚችሉ ፕሬፌሰር መረራ ትዝብታቸውን አጋርተውናል፡፡
በማክሰኞው የኬኒያው ምርጫ ኬንያውያኑ መርጠው ከፍተኛ ተወዳዳሪነት ካሳዩት ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የኬንያ የተቃውሞ ፖለቲካ ዋነኛ ሰው ራይላ ኦዲንጋ፤ ማናቸው 5ኛው ፕሬዝዳንት ይሆናል የሚለውን አሁንም እየተጠባበቁ ነው፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
እሸቴ በቀለ