ስለካንሰር በቂ ግንዛቤ | ጤና እና አካባቢ | DW | 02.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ስለካንሰር በቂ ግንዛቤ

ስለካንሠር ቀደም ሲል በብዙዎች ዘንድ የነበረዉ ግንዛቤ አሁን መለወጡ በይፋ የታየበት ጉባኤ ነበር ባለፈዉ ሳምንት አዲስ አበባ ላይ የተካሄደዉ የካንሠር ዓቀም አቀፍ ጉባኤ። ኢትዮጵያ ዉስጥ በየዓመቱ ከ60 የሚበልጡ ሰዎች በአዳዲስ የካንሠር አይነቶች እንደሚያዙ ይፋ ሆኗል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:40

በአዲስ አበባ የተካሄደዉ የካንሰር ጉባኤ

የጡት እና የማሕጸን ጫፍ ካንሠር ኢትዮጵያ ዉስጥ በአሁኑ ጊዜ የብዙዎች ሴቶች ወገኖቻችንን ሕይወት ለአደጋ ያጋለጡ የጤና እክሎች መሆናቸዉ መነገር ከተጀመረ ሰነበተ። ይፋ የወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱትም በዓመት ከ60 ሺህ ከሚበልጡት የካንሠር ታማሚዎች አብዛኞቹ ሴቶች ናቸዉ። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የካንሰር መከላከል እና መቆጣጠር የብሔራዊ አማካሪ ዶክተር ኩሙዝ አብደላ ከዚህ በፊት ከሚታወቀዉ በበለጠ ሴቶችን የሚያጠቃዉ ካንሠር የሚያደርሰዉ ጉዳት ከፍ ብሎ መገኘቱን ይናገራሉ፤
ቀደም ብለዉ ካንሠርና እሱን መሰል የማይተላለፉ በሽታዎች ትኩረት አግኝተዉ የመከላከሉ መፍትሄ እንዲወሰድ ይህ የጤና ችግር ኅብረተሰቡ ዉስጥ የሚያስከትለዉን ጫና የተገነዘቡ ግለቦችን ድርጅቶች ሲወተዉቱ ቆይተዋል። ወይዘሮ ጽጌረዳ ታፈሰ በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የፕሮግራም እና የኮሙኒኬሽን አማካሪ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት የካንሠር ሕመም የመንግሥት ትኩረት ስቦ እንደቆየ ነዉ የሚናገሩት።
አጋጣሚዉም በካንሠር ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ግንባር ፈጥረዉ የተቀናጀ ሥራ እንዲሠሩ እንዲሁም መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠዉ ጫና ለመፍጠር ይረዳል።


ካንሰር ላይ ትኩረቱን ያደረገዉ ይህ ጉባኤ በዋና ከተማዋ መካሄዱም ጥሪያቸዉ ጆሮ እንዳገኘ እንደሚያመላክት ነዉ አቶ ዘላለም መንግሥቱ በማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ የካንሠር ሶሳይቲ የፕሮግራም ኃላፊ የገለጹልን።
የዘርፉ ባለሙያዎች ቀድሞ በሚደረግ ምርመራ የካንሠር ህመም ከተደረሰበት በሕክምና በሽታዉ የሚያደርሰዉን ጉዳት ለመቀነስ ብሎም ለመዳን እንደሚቻል ይናገራሉ። የሕክምና አገልግሎቱ በአግባቡ በተደራጀባቸዉ የምዕራቡ ዓለም ሃገራት ቅድመ ምርመራ ለማድረግ ከማበረታታት አልፎ አንዳንዴም በጤና መድሕን ዋስትናዎች አማካኝነት ግፊትም ይደረጋል። ኢትዮጵያ ዉስጥ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የካንሠር ሕክምናን የሚሰጠዉ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ነዉ። ለካንሠር በሽታ ትኩረት መሰጠቱ አንድ ነገር ሆኖ ሰዎች ዘግይቶ ለሕክምና ሲኬድ የሚከተለዉን ዉስብስብ የጤና እክል ብሎም ህልፈተ ሕይወት ለመቀነስ መርዳቱን ተገንዝበዉ፤ ምርመራዉን ማድረግ ቢሹ አቅሙ ምን ያህል ነዉ?


ዶክተር ኩሙዝ እንደገለጹት በአምስት የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ዉስጥ የተጀመረዉ የካንሠር ማዕከላት ግንባታ በቀጣይ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ይጠናቀቃል። ለምርመራ እና ሕክምና የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችም ግዢ ተፈጽሞ በወራት ጊዜ ዉስጥ ወደሀገር እንደሚገቡ ይጠበቃል። ግንዛቤን ከመፍጠር አኳያም ለመገናኛ ብዙሃን ሥልጠና መሰጠቱ ታዉቋል። አፍሪቃ ዉስጥ የጡት፤ የማሕጸን ጫፍ እና የፕሮስቴት ካንሰር የሚያደርሱትን ጉዳት እናስቁም በሚል ርዕስ በተካሄደዉ ጉባኤ ላይም በተለይ በበሽታዉ የሚደርሰዉን ጉዳት እስከ 40 በመቶ መግታት አልሞ ነዉ የተጠናቀቀዉ። በተጨማሪም ይህን ለማሳካት በሕክምናዉ ረገድ ያለዉን የአቅም ዉሱንነት ለማሻሻል የሁሉም ትኩረት እንደሚያስፈልገዉ አፅንኦት ተሰጥቷል።
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic