ስለስደተኞች የአዉሮጳ እና የቱርክ ጉባኤ | ዓለም | DW | 08.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ስለስደተኞች የአዉሮጳ እና የቱርክ ጉባኤ

የአዉሮጳ ኅብረት ስደተኞችን አስመልክቶ ከቱርክ ጋር ትናንት ያካሄደዉ ጉባኤ አዎንታዊ ዉጤት ማስገኘቱን የኅብረቱ መሪዎች እየገለፁ ነዉ። ቱርክ አዉሮጳን ጭንቅ ዉስጥ የከተተዉ የስደተኞችን ጎርፍ ለመገደብ ኅብረቱ ሊሰጣት ያቀደዉን የገንዘብ እርዳታ በእጥፍ እንዲበሌላ በኩል ያሳድግ፤ ጠይቃለች።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:50
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:50 ደቂቃ

የአዉሮጳ እና የቱርክ ጉባኤ

የተመ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR በበኩሉ ኅብረቱ አዉሮጳ ዉስጥ የበረከተዉን የስደተኛ ቁጥር ለመቀነስ ጥገኝነት ፈላጊዎቹን ሰብስቦ እስከመመለስ የሚደርስ ዉል ከአንካራ ጋር በቅርቡ ለመፈራረም ማቀዱን ተቃዉሞታል።

የአዉሮጳ ኅብረት መሪዎች ትናንት ማምሻዉን ከቱርክ ባለቀ ሰዓት በቀረበላቸዉ ሃሳብ ላይ ለመነጋገር ተሰብስበዉ ነበር። አንካራ ስደተኞችን ከግሪክ ወደግዛቷ ለመመለስ ለምታደርገዉ ትብብር ኅብረቱ ሊሰጣት ያቀደዉ የገንዘብ እርዳታ ከ3 ወደ 6 ቢሊዮን እንዲጨምር ጠይቃለች። ቀደም ሲል ኅብረቱ ቱርክ ዉስጥ የሚገኙ የሶርያ ስደተኞችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል 3 ቢሊየን ዩሮ ለመስጠት መዘጋጀቱን አመልክቶ ነበር። ከዚህም ሌላ ቱርክ በሕገወጥ መንገድ ወደግሪክ የገቡ ስደተኞችን በሙሉ ወደራሷ ግዛት ለጊዜዉና በሰብዓዊነት ልትመልስ፤ በለዉጡም ከግሪክ በምትመልሰዉ ስደተኛ ቁጥር በግዛቷ የሚገኙ ሶርያዉያንን ወደኅብረቱ አባል ሃገራት እንዲያሻግር ጠይቃለች። ይህም እንደአንካራ እምነት በሕገወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎች ህይወታቸዉ ለአደጋ የሚጋለጠዉን ጥገኝነት ፈላጊዎች ያድናል። የአዉሮጳ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዝደንት ማርቲን ሹልስ እንደሚሉት ይህ ተግባራዊ ከሆነ «በሰዉ ነፍስ አትራፊዎች» ላሉዋቸዉ ደላሎች ከፍተኛ ክስረት ነዉ።

Bildergalerie Flüchtlingskinder Situation in Griechenland

የሶርያ ስደተኞች ግሪክ ዉስጥ

ግን ደግሞ ቱርክ ባቀረበችዉ ሃሳብ የኅብረቱ አባል ሃገራት ሙሉ በሙሉ የመስማማታቸዉ ነገር ገና አልለየለትም። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ግን ጥሩ ርምጃ ተሄዷል ይላሉ።

«ትናንት የቀረበዉን ሰነድ በተመለከተ እጅግ ጠቃሚ ርምጃ ተራምደናል ብዬ አምናለሁ። ግልፅ የሆነ ግብ ለማስቀመጥ ቀሪዉን ዝርዝር ዉሳኔ በሚቀጥለዉ ሳምንት የምንመለከተዉ ይሆናል። መሠረታዊዉ ነገር እዚህ ጋር መግለፅ ካስፈለገ ከቱርክ ጋር የሚኖረን ትብብር ትናንት በዶሴዉ ላይ በግልፅ ሰፍሯል። ያንንም ተቀብለናል፤ እናም ሕገወጥ ስደትን በጋራ የመዋጋት ርምጃዉን በአፅንኦት ተተቀብለነዋል።»

ባለፈዉ ጎርጎርዮሳዊ ዓመት ብቻ ከአንድ ሚሊየን የሚበልጡ ስደተኞች እና ጥገኝነት ፈላጊዎች አዉሮጳ ገብተዋል። ካለፈዉ ጥር ወር ወዲህ ብቻ 135 ሺህ የሚሆኑ መጥተዋል። አብዛኞቹ ከጦርነት የሚሸሹት ሶርያዉያን ሲሆኑ ቀሪዎቹ ከአፍሪቃ እና ከመካከለኛዉ ምሥራቅ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ የተሰደዱ ናቸዉ።

ቱርክ ብቻዋን 2,5 ሚሊየን የሶርያ ስደተኞችን አስጠግታለች። አብዛኞቹ እዚያ ለወደፊት ኑሮቸዉ ይህ ነዉ የሚሉት ነገር በማጣታቸዉ ወደአዉሮጳ ሃገራት ለመሻገር ይሞክራሉ። ይሻገራሉም። ይህን የስደተኞች ፍሰት ለመግታት የአዉሮጳ ኅብረት ለቱርክ 3 ቢሊዮን ዩሮ ርዳታ ለመስጠት ተዘጋጅቷል። በዚህ አንካራ ለስደተኞቹ መጠለያም ሆነ ትምህርት ቤቶችን መገንባት እንድትችል ነዉ የታሰበዉ። አብዛኞቹ ስደተኞች ከቱርክ መንግስት ምንም ዓይነት ድጋፍ አያገኙም፤ በዚህም ምክንያት ለመኖር ያገኙትን በርካሽ ክፍያ ሠርተዉ ለማደር ተገደዋል። የቱርክ መንግሥት ሶርያዉያን ስደተኞች ከሀገሬዉ ሕዝብ ጋር ተዋህደዉ እንዲኖሩ ለማድረግ እንደሚጥር ይናገራል። ሥራ የመሥራት ፈቃድን እንደሚሰጥም ተናግሯል በተግባር ግን ገና አልተገለጸም እየተባለ ነዉ። የ20ዓመቱ ሶርያዊ ኦማር ኢስታንቡል በአንድ ጫማ ፋብሪካ ዉስጥ ከሁለት መቶ ዩሮ ያነሰ ደሞዝ በወር እየተከፈለዉ ይሠራል።

Griechenland Mazedonien Flüchtlinge bei Idomeni

ግሪክ ሜቄዴኖያ ድንበር

«እሁድ ቅዳሜን ጨምሮ ሳምንቱን ሙሉ ነዉ የምንሠራዉ። በሳምንቱ መጨረሻ መጥተን እንድንሠራ ያስገድዱናል ግን ደግሞ አይከፈለንም።»

ይላል። ለአብዛኞቹ በእድሜ ከፍ ላሉ ስደተኞች የሥራ ዕድል የለም፤ ልጆቻቸዉም ትምህርት ቤት አይሄዱም። ብዙዎቹ ጊዜያቸዉን በመተከዝ እንደሚገፉ ይናገራሉ። ቱርካዊዉ የስደተኞች ጉዳይ ተመራማሪ ሙራት ኤርዶኻን ይዞታዉ በዚህ ይቀጥላል የሚል ስጋት አላቸዉ።

« እጅግ በጣም ጥቂት ሶርያዉያን ስደተኞች ብቻ ከሚሰጠዉ መሥራት ፈቃድ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። አብዛኞቹ ሕገወጥ በሆነ መንገድ መሥራታቸዉን መቀጠላቸዉ አይቀርም። ትንንሽና መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኩባንያዎች እንዲህ ካለዉ የሥራ ገበያ ይጠቀማሉ። ለእነሱ ይህ ርካሽ የሠራተኛ ጉልበት ነዉ።»

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች