ሴፕ ብላተር ተመረጡ | ይዘት | DW | 01.06.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ይዘት

ሴፕ ብላተር ተመረጡ

ብላተር እንዳሉት አዘጋጁ ሃገር እንደ እስከዛሬው በ 24 የፊፋ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መወሰኑ ቀርቶ በ ፌደሬሽኑ 208 አባላት እንዲመረጥ ማድረግ ይፈልጋሉ

የዓለም ዓቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን በምህፃሩ ፊፋ አባላት ዛሬ የስዊሱን ዜጋ ሴፕ ብላተርን ለአራተኛ የሥልጣን ዘመን መረጡ ። ብላተር ለ 4ኛ ጊዜ በፕሬዝዳንትነት የተመረጡት ከ 203 አባላት የ186 ቱን ድምፅ አግኝተው ነው ። ብላተር ዛሬ ለጉባኤው ባሰሙት ንግግር እንደገና ከተመረጡ የፊፋን ስም ያጠፋውን ሙስናን ለማስቀረት የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን የሚያዘጋጀው ሀገር የሚመረጥበትን አሰራር ለመቀየር እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል ። ብላተር እንዳሉት አዘጋጁ ሃገር እንደ እስከዛሬው በ 24 የፊፋ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መወሰኑ ቀርቶ በ ፌደሬሽኑ 208 አባላት እንዲመረጥ ማድረግ ይፈልጋሉ ። የፊፋ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ን ለማስተናገድ ከሚፈልጉ ሃገራት ጉቦ እየተቀበሉ ድምፃቸውን ሸጠዋል ተብለው በቅርቡ ታግደዋል ። ብላተር ጉባኤው ሲከፈት ባሰሙት ንግግር ፊፋ በዚህ ምክንያት ለአደጋ መጋለጡን አስታውቀዋል ። « እግር ኳስ ፣ ክብር መልካም ጨዋታ እና ስነ ስርዓት የሚለው መርሁ በዚህች ዓለም ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብዪ አስብ ነበር ። ሁኔታው ግን እንደዚያ አይመስልም ። ፊፋ የፌደሬሽናችን ፅኑ ምሰሶዎች ተናግተዋል ። አደጋ ተጋርጦበታል ። »

ከፌደሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አንዳንዶቹ ከስራ መታገዳቸውን እንደ ምክንያት በማቅረብ የ የፊፋ ፕሬዝዳንት ምርጫ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ከብሪታኒያ የእግር ኳስ ማህበር በኩል የቀረበውን ሃሳብ ጉባኤው ሳይቀበለው ቀርቷል ። የፊፋ ምክትል ፕሬዝዳንት አርጀንቲናዊው ጁልዮ ግሮንዶና እንግሊዝን በማማረር ፣ የእንግሊዝን መገናኛ ብዙሀን ደግሞ ስለ ፊፋ የሀሰት ዘገባዎችን በማቅረብ በጉባኤው ፊት ወቅሰዋል ።

ሒሩት መለሠ

ነጋሽ መሐመድ