ሴት ተማሪዎችን የሚደግፉት አውሮፓውያን ተማሪዎች | ወጣቶች | DW | 06.09.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

ሴት ተማሪዎችን የሚደግፉት አውሮፓውያን ተማሪዎች

ፕሮጀክት-ኢ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ሴቶች ተምረው ጥሩ ቦታ እንዲደርሱ የትምህርት እና የተለያየ ድጋፍ የሚጠጥ ማሕበር ነው። የማሕበሩ አባላት ደግሞ አውሮጳ የሚኖሩ በጎ ፍቃደኛ ተማሪዎች ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ የዛሬው የወጣቶች ዓለም እንግዳችን አድርገናቸዋል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:02

ሴት ተማሪዎችን የሚደግፉት አውሮፓውያን ተማሪዎች

ፕሮጀክት-ኢ (Project-E) መንግሥታዊ ያልሆነ የአውሮፓውያን ተማሪዎች ማሕበር ነው። ማሕበሩ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ወላጆቻቸውን ያጡ  ሴት ተማሪዎች ተምረው ራሳቸውን እንዲችሉ የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎች ይሰጣል።  ማሪያነ ሲደ ይህንን ማሕበር በቅርቡ ከተቀላቀሉ ወጣቶች አንዷ ናት። «ከ አምስት አመት ገደማ በፊት ነው የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተማሪ እያለሁ ስለ ፕሮጀክት-ኢ ያወኩት።  በወቅቱ ከትምህርቴ ጋር የሚገናኝ ነገር ስፈልግ ወዲያው ሀሳቡ የመጣልኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር። ያኔ ነው ስለ ፕሮጀክት-ኢ ጉግል ላይ ያነበብኩት። እና በትምህርት እና በሥራ መካከል ክፍተት ሳገኝ  በርግጥም ፕሮጀክት-ኢ ትዝ አለኝ። ከዛም በጎ ፍቃደኞች እንደሚፈልጉ አነበብኩ እና አመለከትኩኝ።  ከዛን ጊዜም አንስቶ የማሕበሩ አባል ነኝ።  አሁን የርዳታ ገንዘብ ማሰባሰብ ላይ እሰራለሁ።»የ28 ዓመቷ ጀርመን- ኢትዮጵያዊት በአሁኑ ሰዓት በኔዘርላንድስ ማስትሪሽት ከተማ በሚገኝ አንድ  ዩንቨርስቲ ውስጥ የሰው ኃብት ልማት እና የመንግሥት አስተዳደር ምርምር ጥናት ላይ ለ2ተኛ ዲግሪዋ ትማራለች። 

ሌላው የዚህ ፕሮጀክት አባል ሞሪትዝ ኮልበ ይባላል። ፕሮጀክት ኢን  የተቀላቀለው የከፍተኛ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመልቀቂያ ፈተና ከወሰደ በኋላ ነው። በወቅቱ በአፍሪቃ ቀንድ የሚገኙ ሀገራት የልማት ትብብር ስራዎችን እያፈላለገ ነበር።« ስለ ድርጅቱ ኢንተርኔት ላይ ካነበብኩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሄድኩኝ። እዛም በፕሮጀክት ኢ  ውስጥ ለአምስት ወር አገለገልኩ። ስራውን እና ሀገሩን በጣም ወደድኩት። ስለሆነም ትምህርቴን በዮንቨርስቲ ለመከታተል ስመለስ አውሮፓ የሚገኘውን የፕሮጀክት ኢ ቡድን ተቀላቀልኩ እና በህዝብ ግንኙነት አገለግል ጀመር። በመጨረሻም አንድ የሊቀመንበር ቦታ ሲለቀቅ ለምርጫ የቀረበልኝን ጥያቄ ተቀብዬ ተመረጥኩኝ። አሁን በሊቀመንበርነት ለፕሮጀክት ኢ ሳገለግል ሁለት አመት ተኩል ሆነኝ።»

Äthiopien PROJECT-E (Privat)

ማሪያነ ሲደ ከተማሪዎች ጋር

የ 24 ዓመቱ ጀርመናዊ ወጣት ሞሪትዝ ያለፉትን አምስት አመታት በበጎ ፍቃደኝነት ለዚህ ማሕበር አገልግሏል። እሱም በጀርመን ሀይድልበርግ ከተማ የጀመረውን የዮንቨርስቲ ትምህርት ሲያጠናቅቅ ወደ አፍሪቃ ሄዶ መሥራት ይፈልጋል። ከአህጉሩ ጋር ይበልጥ ያስተዋወቀው ይኼው የበጎ ፍቃደኛ ሥራው ነው።«ከፕሮጀክት ኢ የምወደው ነገር በሁለት ቡድን ተከፍለናል። በአንድ በኩል አውሮፓ ያለነው አለን በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ  ውስጥ አሉ። ኢትዮጵያ ያለው ፕሮጀክት የሆቴል ሙያ ማሰልጠኛውን የሚያስተዳድሩ 14 ሠራተኞች አሉት። በዚያም ዕድሜያቸው ከ 18 እስከ 25 ያሉ ሴት ተማሪዎች ይሰለጥናሉ።  አውሮፓ ያለው የፕሮጀክቱ የበጎ ፍቃደኞች ቡድን ደግሞ  የህዝብ ግንኙነት፣ የርዳታ ገንዘብ ማሰባሰብ፣ የፋይናንስ እና የአስተዳደር ሥራዎች ላይ ያተኩራል።»

ማሪያነ ገንዘብ ከሚያሰባስቡት ቡድን ውስጥ ናት። ወጣቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፕሮጀክት-ኢ ለማገልገል ወደ ኢትዮጵያ የተጓዘችው ባለፈው ግንቦት ወር ነው። በነበራት የአንድ ወር ቆይታም ሌሎች የማሕበሩ የሥራ ድርሻዎች ላይ ተሳትፋለች።« ፕሮጀክት ኢ በአሁኑ ሰዓት ሙሉ ሰዓት ለሚሰለጥኑት ተማሪዎች ሁለት አይነት ደረጃዎች ነው ያሉት። ወደፊት ደግሞ ፕሮጀክት ኢ ከዚህ የበለጠ ሴቶችን ማሰልጠን የሚችልበት ሦስተኛ ደረጃ ላይ እየሠራ ይገኛል። በፊትም የሥራ ልምዱ ስለነበረኝ እኔም ይህን እውን ማድረግ የሚቻልበት መንገድ ላይ እሳተፍ ነበር። አልፎ አልፎ ደግሞ መምህራኑን በማገዝ እንግሊዘኛ እና ፈረንሳይኛ አስተምሬያለሁ። በመዝናኛ ጊዜያቸው ደግሞ  ዮጋ ስፖርት፤ የባሌት ዳንስ ፤ እንዲሁም ከልጃገረዶቹ ጋር ኬክ እንጋግር ነበር። ልጆቹ ኬክ የመጋገር ልምድ ስላልነበራቸውም ጥሩ እና ደስ የሚል ጊዜ ነበር። »

Äthiopien PROJECT-E

ተማሪዎች ኬክ ሲጋግሩ

ሞሪትዝን እና ማሪያነን እንዲህ የሳበው እና ያሳተፈው ፕሮጀክት ኢ ከተመሰረተ 12 ዓመቱ ነው። መስራቾቱ ደግሞ ኦስትሪያውያን ወንድማማቾች ናቸው።« የፕሮጀክት ኢ መስራቹ ቬንዝል ቫልድሽታይን በወቅቱ የከፍተኛ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመልቀቂያ ፈተና ከወሰደ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የልጆች ማሳደጊያ ውስጥ የሥራ ልምምድ አድርጎ ነበር። እና የታዘበው ነገር የልጆች ማሳደጊያውን ለቀው በ 17 እና 18 ዓመታቸው የሚወጡት ልጃ ገረዶች የሥራ ዕድል እንደሌላቸው ፤ ከወንዶች ጋር ሲነፃፀርም ደግሞ  ጥሩ የሚባል የሥራ ስልጠናም እንደማያገኙ ነው ። ከዛም ከወንድሞቹ ጋር ሆነው በምን መንገድ ይህን ማሻሻል እንደሚቻል ተማከሩ። ያኔም ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም አዲስ አበባ ውስጥ የሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ መገንባት የሚል ሀሳብ መጣላቸው። ይህም ኮሌጅ በነፃ ወጣቶቹን ሴት ተማሪዎች የሚያሰለጥን እና የኢትዮጵያንም የሥራ ገበያ ከግምት ያስገባ እንዲሆን ወሰኑ።»

ሞሪትዝ እንደገለፀልን ወንድማማቾቹ የመሠረቱት ፕሮጀክት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ሄዷል። እኢአ በ2014 ዓ ም የሆቴል ሙያ ማሰልጠኛው ኮሌጅ ሊመሰረት ችሏል። ዛሬ በማሰልጠኛ ኮሌጁ ዕድሜያቸው ከ 18 እስከ 25 ያሉ እስከ 70 ሴት ተማሪዎች በየዓመቱ ሙያዊ ስልጠናቸውን ያጠናቅቃሉ። ሥራም ያገኛሉ። ስልጠናው በሁለት የተከፈለ ሲሆን ረዥሙ አንድ ዓመት ተኩል አጭሩ ደግሞ የቤት አያያዝ ሥራ ሲሆን ከሦስት ወር እስከ አራት ወር ይፈጃል። ተማሪዎቹም በስልጠና ጊዜያቸው የሚያስፈልጋቸው ማንኛውንም ወጪ የሚሸፍነው ፕሮጀክት ኢ ነው። ፕሮጀክት ኢ አውሮፓ ውስጥ 26 አባላት አሉት። ለመሆኑ ሌሎች በዚህ ፕሮጀክት ለመሳተፍ የሚፈልጉ ወጣቶች ምን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል?

Äthiopien PROJECT-E (Privat)

ሞሪትዝ ኮልበ

« ኢትዮጵያ ባለው የፕሮጀልት ኢ ውስጥ ለማገልገል በጎ ፍቃደኞቹ ፣ በንግድ ወይም በአስተዳደር ሥራ ልምድ ያላቸው ቢሆን ይመረጣል። ምግብ ቤት ወይም ሆቴል ውስጥ ልምድ ያላቸው ከሆኑ ያላቸውን  ልምድ ለሌሎች ሊያካፍሉ ይችላሉ። ሌላው አስፈላጊ ነገር ሴቶች ፆታን በተመለከተ  ያላቸው አስተሳሰብ  ማሻሻል እንዲችሉ ማገዝ የሚችል ቢሆን ጥሩ ነው።»ይላል ሞሪትዝ።  ይህ ማሪያነ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበራት የበጎ ፈቃደኝነት ሥራ የታዘበችው ነው። « ወጣቶቹን ልጆች በራሳቸው እንዲተማመኑ ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ታዝቤያለሁ። ማኅበረሰቡ ዘንድ ሴቶች ራሳቸን ትንሽ የበታች ሲያደርጉ ይስተዋላል። እና የባሌት ዳንስ ስንደንስ ራሳቸውን ትንሽ ለቀቅ አድርገው ፈታ ሲሉ አይቻለሁ። እዛ ከሚገኙት ሠራተኞች ጋር የነበረን ቆይታም ጥሩ ነበር። ግማሽ ኢትዮጵያዊ በመሆኔም ወዲያው እንደ ኢትዮጵያዊ አድርገው ነው የተቀበሉኝ። ከኔ ጋር እንግሊዘኛ እየተነጋገሩ መለማመድ እየቻሉ፤ በአንፃሩ እኔንም ባህሉን እና ቋንቋውን ለማስተማር ሲጥሩ ነበር ።»

የበጎ ፍቃደኝነት ሥራ ምንም እንኳን ያለ ገንዘብ ክፍያ ሌሎችን መርዳት ወይም ማገልገል ቢሆንም በጎ ፍቃደኞቹም ከሌሎች የሚያገኙት ጥቅም አለ። ማሪያነስ ከዚህ ሥራዋ ለራሷ ምን ጠቃሚ ነገር አገኘችበት? « በግሌ በውስጤ ያለኝን ባህል እና ማንነቴን እንዳውቅ እና የበለጠ እንድመረምር ረድቶኛል።  በተለይ ችላ የተባለው የኢትዮጵያዊነት ጎኔን ማለት ነው!  ምክንያቱም ጀርመን ውስጥ ስለሆነ ያደኩት የአማርኛ ቋንቋን በደንብ አልተማርኩም። ሌላው ልቤ ውስጥ የቀረው ሴቶችን ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረጉ ሥራ ነው። አሁን ደግሞ ከመቼውም በላይ ከኢትዮጵያ ጋር ባህላዊ ትስስሬ ጎልቶ ስለታየኝ በዚህ ዘርፍ ላይ የበለጠ መሥራት እፈልጋለሁ።»

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic