«ሴቢት»፣ የኮምፒዩተር ትርዒት፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 07.03.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

«ሴቢት»፣ የኮምፒዩተር ትርዒት፣

በጀርመንኛው አህጽሮት «ሴ ቢ ት » በመባል የሚታወቀው፣ የዘንድሮው ፣ የሃኖፈር ዓለም አቀፍ የቢሮና የመረጃ ሥነ ቴክኒክ ማዕከል፣ እ ጎ አ መጋቢት 12 ቀን 1986 ዓ ም በሰሜን ጀርመን ከተማ፣ በሃኖፈር ከተጀመረ ወዲህ፣ ከጊዜ ወደጊዜ፤

የሥነ ቴክኒኩን  ፣ የኢንዱስትሪውን፣ የኤኮኖሚውንና  የንግዱን  ማኅበረሰብ ይበልጥ እያማለለ መምጣቱ  የሚታበል አልሆነም።  በዚህ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ትርዒት ዘንድሮ ማለትም እ ጎ አ በ 2012 ዓ ም፤ ምን አዲስ ነገር ይሆን ለትርዒት የቀረበው? የዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን፣ መነሻና መድረሻ  «  ሴ ቢ ት» ይሆናል። አብራችሁን ቆዩ።

በዓለም ዙሪያ፣ በብዙ አካባቢዎች፤ከኤኮኖሚ ድቀት ሙሉ በሙሉ ለማገገም ገና ብርቱ ጥረት በመደረግ ላይ ቢሆንም፣ በዓለም ውስጥ ከታወቁት የመረጃ ቴክኖሎጂ ትርዒት አቅራቢዎች መካከል አንዱ የጀርመኑ የሓኖፈር ዐውደ ርእይ፣  በዚህ  ዘርፍ፣  ንግዱ ሊደራ እንደሚችል ጠንከር ያለ ግምት ነው ያለው።

ከትናንት በስቲያ ማታ ፣  የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ትርዒቱን መርቀው የከፈቱት ሲሆን፤  ከትናንት አንስቶ እስከ ቅዳሜ ለህዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል። ሜርክል፤ ስለ «ሴቢት» ጠቀሜታ ሲናገሩ እንዲህ ነበረ ያሉት።

«Cebit ፣ ዓይናችን እያዬ ዓለም በምን ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ያስረዳናል። በብዙ ዘርፎች በጥሩ አቋም ላይ እንገኛለን። በመረጃና በመገናኛ ሥነ ቴክኒክ ረገድ ግን በሚገባ ልናሻሽለው የምንችለው ነገር አለ።» 

ከ 70 አገሮች የተውጣጡ ከ 4,000 በላይ ትርዒት አቅራቢዎች ናቸው ትናንት በይፋ ተመርቆ ተከፍቶ እስከ ቅዳሜ በሚዘልቀው ዓለም-አቀፍ ትርዒት ላይ በመሳተፍ  የሚገኙት።  Cloud Computer Technology(የመረጃ ቴክኖሎጂ ሰነዶች ማከማቻ ሥርዓት የተዘረጋበት ማለት ነው፤)ይህ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያዝበትና የሚጠበቅበት አያያዝ፤  ዐቢይ ትኩረት እንደሚሰጠው ነው ከወዲሁ የተገለጠው። ትርዒቱ፤ በይፋ በተከፈተበት ሥነ ሥርዓት ላይ፣ የ «ጉግል ዋና ኀላፊ ኤሪክ ሽሚት፤ ኢንተርኔት ዓለምን በመለወጡ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳበረከተ ጠቅሰው፤ የኢንተርኔት ሰነዶችን በሳንሱር ለመቆጣጠር  የሚደረግ ማንኛውንም ሙከራ እንደማይቀበሉት ነው ያስታወቁት። የኢንተርኔቱ ድረ ገጽ እንዲሁ የኮምፒዩተር መረብ አይደለም፤ እንዲያውም ፤ የዓለም አቀፍ ንቃተ-ኅሊና ነው ማለት ይቻላል  ብለዋል። የመረጃ ልውውጥን በቁጥጥር ሥር አውላለሁ ብሎ መነሣሣት፤ የሚከሽፍ ጉዳይ ነው። ከ ጉግል ሌላ፤ ታዋቂው የረቂቅ ሥነ ቴክኒክ ውጤቶች ባለቤት IBM እና SAMSUNG  ለትርዓቱ ታጥቀው ተነስተዋል።  ማይክሮሶፍት በፊናው፤ አዲሱን መስኮት 8 የተሰኘውን ሶፍትዌር ለማስተዋወቅ እየሞከረ ነው። ሰ ቢት ፣ የፊታችን ቅዳሜ ፣ ትርዒቱ እስኪደመደም ድረስ ከአምናው 339,000 ህዝብ የላቀ ተመላካች ሳይገኝ እንደማይቀር ነው አዘጋጂዎቹ የሚያሰላስሉት። በዘንድሮው  የ ሴ ቢ ት ትርዒት፤ የተመልካቾችን ቀልብ ከሳቡት መካከል በ 26ኛው  አዳራሽ የሚታየው በሳቴላይት መሪነት የሚንቀሳቀሱ አውቶሞቢሎች የሚታዩበትና የአሽከርካሪው ልዩ የአጅ ስልክ ናቸው። ጉዳዩ ከዚህ ቀደም በዚህ ዝግጅት እንዳቀረብነው፤ ያለ አሽከርካሪ፤ ትርምስ በበዛበት ጎዳናም ቢሆን፣ ያለአደጋ የሚሽከረከሩ መኪናዎችን ነው የሚመለከተው። ሠርቶ ያቀረበው፤ የጀርመኑ ፍራውን ሆፈር የምርምር ተቋም ሲሆን በተለይ የዚሁ እጅግ ዘመናዊ ሥነ-ቴክኒክ ክፍል ኀላፊ Jens Zech እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ።

«ለምሳሌ እዚህ ላይ  2 የተሽከርካሪ መብራቶች አሉ። እንዲሠራ መመሪያ ሲሰጣቸው  ጎዳናውንና የተሽከርካሪዎችን እንቅሥቃሤ  በመገምገም እንዴት መሠማራት እንደሚቻልና ተፈጥሮን በማይበክል ኃይል በመጠቀም፣ ከአንድ ቦታ ተነስቶ ብዙ ተሽከርካሪዎች በሚንቀሳቀሱበት ጎዳናም ቢሆን እፈለጉት ቦታ መድረስ እንደሚቻል ያስረዳል።»

በዘንድሮው ትርዒት የሚያስደንቀው ተጨማሪ ጉዳይ፣  የወደፊት ተሽከርካሪዎች የተባሉት አውቶሞቢሎች፤ ማቆሚያ ቦታ በሚጣበብበት ጊዜ፤ እንደሚሸበሸብ ልብስ አጥረው ሳይገጩና ሳይገጩ፤ ቦታ ማብቃቃት የሚችሉ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፤ ቢሮ በር ድርስ ከተፍ ብለው በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት  ባለቤቱን አሣፍረው ወደፈለገው ቦታ የሚወስዱ ናቸው። 2,10 ሜትር ርዝማኔ ያላቸው ተሽከርካሪዎች በመቆሚያ ቦታ ለሥፍራ ቁጠባ 50 ሴንቲሜትር ድረስ ሰብሰብ ማለት ይችላሉ።

ሌላው (M-to-M) ከአንድ ማሺን ወደ ማሺን በተለያዩ የመኪና ዓይነቶች የመገናኛ አገልግሎት መፍጠር  መቻሉ ነው። የአጅ ስልክ ውስጥ እንደሚያገልግል SIM-Card

ዓይነት ማለት ነው። እናም  ከመኪና ውስጥ በኢንተርኔት መጠቀም ብቻ ሳይሆን የአስቸኳይ ሁኔታ ጥሪ በማስተላለፍ የሚፈልገውንዓይነት እርዳታማግኘት ይቻላል ማለት ነው። በጀርመን የ ቮዳፎን  ቃል አቀባይ ፓውስ ጌርላህ---

«ወደፊት የ «ጉግል»ም ሆነ የቮዳፎን አውቶሞቢሎች አይደለም የሚሠሩት።  እንበል የ BMW ሆኖ፤፣ አዳዲስ  አገልግሎቶች ብቻ ነው የሚኖሩት።ተመራማሪዎች እንደሚገምቱት M-to-M  በተሰኘው የአውቶማቲክ አገልግሎት ክፍል በ 2012 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ብቻ 9 ቢሊዮን ዩውሮ ትርፍ ሳይገኝ  አይቀርም።  

የዘንድሮው ፤ የ «ሴቢት» ልዩ እንግዳም ሆነች ተጋባዥ ሀገር ብራዚል ስትሆን፤ ፕሬዚዳንትዋ  ወ/ሮ ዲልማ ሩሴፍ ፣ በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ ከመራኂተ መንግሥት 

አንጌላ ሜርክል ጋር ተገኝተው ነበር።

ብራዚል በግል ኮምፒዩተሮች በመጠቀም ከዓለም የ 3ኛነቱን ቦታ የያዘች ሀገር ናት። የመረጃ ቴክኖሎጂው ዘርፍ በሚመጡት 12 ወራት  6 ከመቶ ያህል ዕድገት እንደሚያሳይ ነው የሚገመተው።

ምንም እንኳ ዘንድሮ ካምናው በቁጥር የላቀ ጎብኚ እንደሚገኝ ይገመት እንጂ፤ እ ጎ አ በ 2001 ከተደረሰበት ክብረወሰን ጋር ሊቀራረብ የሚችል የህዝብ ጉብኝት በሃኖፈር ይከናወናል ተብሎ አይጠበቅም። ያኔ  850,000 ህዝብ ነበረ የጎበኘው። ተሳታፊዎቹ ኩባንያዎችም ከ 8,000 በላይ ነበሩ ። ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ቁጥሩ የቀነሰው፤ በርሊን፤ ላስ ቬጋስ ባርሴሎና ና የመሳሰሉ ከተሞች ብርቱ ተፎካካሪዎች በመሆናቸው ነው።

በአምናው  የ ሴ ቢት ትርዒት፣ «ቶቢ» የሚባለው በእስዊድን ኩባንያ የተሠራው፤ በዓለም ውስጥ  የመጀመሪያው ፣ ዓይንን በማሽከርከር የሚሠራው «ላፕ ቶፕ»ቀርቦበት ብርቅ-ድንቅ!  ተብሎ እንደነበረ የሚታወስ ነው።

የጀርመን ቴሌኮም፤ ልዩ ጥራት ባለው ተንቀሳቀሽ ስልክ Long Term Evolution (LTE)በተሰኘው ሥነ-ቴክኒክ፣ በፍጥነት ከእጅ ስልክ  የተለያየ መረጃን ለማግኘት፤ በ «አይፓድ» እና በመሳሰለው ለሚሠራበት፣  በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መድቧል። ይኸው ሥነ ቴክኒክ ውድ የመረጃ ማስተላለፊያ ገመድ ሳይዘረጋ ፣ ለገጠር ኑዋሪዎች እንዲጠቀሙ ማድረግ ይቻላል።  ፣ ቮዳፎን፣ 02፣ እና የጀርመን ቴሌኮም፣ ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር አንስቶ፣ ያለገመድ በ LTE  ደንበኞች ፣ በኢንተርኔት ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን ማሠራጫ መሥመሮች አሽሽለው መሥራቱን ተያይዘውታል።

እንዳምናው ዘንድሮም ላቅ ያለ ትኩረት የተደረገበት  « ክላውድ ኮምፒዩቲንግ»  ነው። ክላውድ ኮምፒዩቲንግ፤ አንድ ደንበኛ፤ በቢሮም ሆነ በመኖሪያ ቤቱ፣ ያለ ሶፍትዌርም ሆነ የኮምፒተር ሞተር(ፕሮሰሰር) በድረ-ገጽ  የሚጠቀምበት ፤ የሚገለገልበት አሠራር ነው። 

ይኸው፣ ለቢሮና ለቤት የሚጠቅመው  የኢንተርኔት አገልግሎት ፣  የንግዱ ዓለም በቁጠባ የተቀላጠፈ ሥራ ማከናወን የሚችልበትን ብልሃት  ነው። መሆኑም  ነው የሚነገረው። ተጠቃሚዎች፤  በያመቱ  ለ «ክላውድ ኮምፒዩቲንግ»፣ 1,6 ቢሊዮን ዩውሮ(2,2 ቢልዮን ዶላር ) እንደሚያውጡ ነው የሚገመተው። ከንግድ ደንበኞች ጋር ፣ ይኸው የአገልግሎት ዘርፍ ዘንድሮ ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ 3,5 ቢሊዮን ዩውሮ ገቢ እንደሚያገኝ የሚጠበቅ  ሲሆን፤ ከሆነ ፣ ካምናው የ 55 ከመቶ ዕድገት  ያሳያል ማለት ነው። « ክላውድ ኮምፒዩቲንግ» አንድ ደንበኛ፤ በቢሮም ሆነ በመኖሪያ ቤቱ፣ ያለ ሶፍትዌር፣ በድረ-ገጽ  የሚጠቀምበት ፤ የሚገለገልበት አሠራር ነው። 

በዚህ  የ «ክላውድ ኮምፒዩቲንግ» መርኀ ግብር ይበልጥ ያተኮረው እውቁ የሶፍትዌር ኩብንያ ማይክሮሶፍት ነው። «ዊንደውስ» እና «ማይክሮሶፍት  ኦፊስ» ኩባንያው እንደ ወተት ሰጪ ላሞች ፣ በአመዛኙ  ገንዘብ  በገፍ የሚያልብባቸው የገቢ ምንጮቹ ናቸው።  ማይክሮሶፍት ከዚህ ሌላ፤ ድምፁን አጥፍቶ፤ በድረ-ገጽ፤  በተለይም በ « ክላውድ»  ላይ አትኮሮ መቆየቱ ን በጀርመን የማይክሮሶፍት ቅርንጫፍ ኀላፊ ፣ ራልፍ ሃውፕተር ያስረዳሉ። ክላውድ ኮምፒዩቲንግ ይላሉ ራልፍ ሃውፕተር፣ የኢንተርኔት የአገልግሎት ዓይነት ሂደትን  የለዋወጠ ነው። ይህ ደግሞ ለኤኮኖሚው ልዩ ማነቃቂያ ኅይል  የሚሆን ነው። «ክላውድ ኮምፒዩቲንግ፣»  በኅብረተሰቡም በኩል ለውጥ የሚያንፀባርቅ ነው። የክላውድ ኮምፒዩቲንግ አገልግሎት፣ ከህዝብ ብዛት ጋር ተያይዘው በሚከሠቱ ማኅበራዊ ችግሮች፤የጤና አጠባበቅ፣  አስተዳደርና በመሳሰሉት ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ አሠራሩም ይበልጥ ግልጽነትንና ፍጥነትን የሚያካትት ነው። ማይክሮሶፍት የጀርመን ቅርንጫፍ፣ በክላውድ ሥነ ቴክኒክ በመመርኮዝ፤ እያንዳንዳቸው የፈጠራ ሥራንና ውጤትን የሚሹ  30 ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ቃል ከመግባቱም፤ በአውሮፓ ፣ ጀርመንን   በክላውድ ኮምፒዩቲንግ ረገድ መሪ ሀገር ለማድረግ ከመጣር እንደማይቦዝን ራልፍ ሃውፕተር አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ፣ ጀርመናውያን በሥነ ቴክኒክ በተለይም በመገናኛ ዘርፎች የሚደረገውን ሁሉንም ዓይነት አሠራር የሚደግፉ አይደሉም። ለምሳሌ ያህል ጉግል በጀርመን ሀገር የተለያዩ ከተሞችን ጉዳናዎች በተንቀሳቃሽ ምስል ለመቅረጽ ያደረገውን ሙከራ የተቃወሙ ጀርመናውያን  ጥቂቶች አልነበሩም። ክላውድ ኮምፒዩቲንግን በተመለከተ ፣ አብዛኞቹ መሪ ኩባንያዎች፤ በጀርመን መሠረት ያላቸው አይደሉም። መሪዎቹ፤ IBM, Amazon, Google,Microsoft  እና  Salesforce.com  ናቸው። 

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ

 • ቀን 07.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14GYX
 • ቀን 07.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14GYX