ሳይንስና ሥነ ቴክኒክ በ2013 | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 26.12.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ሳይንስና ሥነ ቴክኒክ በ2013

በምድራችን የሚኖረው ህዝብ ብዛት ከ 7 ቢሊዮን ቢበልጥ እንጂ እንደማያንስ የታወቀ ሆኖ ሳለ ፣ ላሁኑና ለመጪውም ዘመን ፤ በዝች ምድር የሰዎችን ህልውና እንዴት አስተማማኝ ማድረግ ይቻላል ? ለሚለው ጥያቄ መልሱ የሚያከራክርም የሚያነታርክም ሊሆን ይችላል?

ለሚለው ጥያቄ መልሱ የሚያከራክርም የሚያነታርክም ሊሆን ይችላል? የምድራችንን የተፈጥሮ ሃብት በቅጡ በመጠቀም፤ ፕላኔታችንንም ከአየር ውሃና አፈር ብክለት በመከላከል በዘላቂነት ጠቀሜታ እንድትሰጥ ከመረበራብ ይልቅ፤ በተለይ ኃያላኑ መንግሥታት ፤ ለራሳቸው አሳላጭ የኤኮኖሚ ዕድገት እንጂ፣ ባጠቃላይ ለዓለም ግዝብ ጠቀሜታ እምብዛም ደንታ ያላቸው አልመሰሉም።

የክዌቶውን የአየር ንብረት ጥበቃ ውል ፣ በዚያው መጠንም ሆነ በተሻለ ውል ለመተካት እንኳ በወቅቱ እንዳልተቻለ የታወቀ ነው።

ያልታወቀ ነገርን ለማወቅ መጓጓት አዎንታዊ የሰው ባህርይ ቢሆንም፣ ስለ ምድራችንም ሆነ ፕላኔታችን ምሥጢራት ጠንቅቆ ሳያውቅ፣ በሽታን ረሃብን ሳያጠፋ ፣ የሩቁን ካልደረስኩበት ብሎ፣ ሥፍር ቁጥር የሌለው ሀብት ማባከኑ የሚያነጋጋር ጉዳይ ነው።

ከ 50 ዓመታት ገደማ በፊት፤ ሁለት ኃያላን መንግሥታት ብቻ ነበሩ በኅዋ ምርምር ላይ ያተኮሩት፤ የያኔዋ ሶብየት ኅብረት(ያሁኑ ሩሲያ) እና ዩናይትድ ስቴትስ!

በአሁኑ ጊዜ፤ ቻይናና ህንድ ራሳቸውን አጠናክረው ውድድሩ ውስጥ ገብተውበታል፤ የአውሮፓው ኅብረት፣ ጃፓንና የመሳሰሉ አገሮችም አሉ። ካፍሪቃ ፤ ደቡብ አፍሪቃ ናይጀሪያና ኢትዮጵያ ለኅዋ ምርምር ላቅ ያለ ትኩረት ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ ባለፈው ጥቅምት በ 2,5 ሚሊዮን ዩውሮ ውጪ አዲስ የኅዋ ምርምር ጣቢያ ተመርቆ እንዲከፈት አብቅታለች፤ ይህም በምሥራቅ አፍሪቃ እጅግ ትልቁ የከዋክብት ማጥኛ ጣቢያ መሆኑ ተነግሯል። በኅዋና ሌሎች ሰማያዊ አካላት ላይ የሚደረገው ዓለም አቀፍ የምርምር ውድድር አስገራሚ እየሆነ መጥቷል።

በቅርቡ፤ ህንድ ማርስን የሚያስስ መንኮራኩር አምጥቃለች። መንኮራኩሯ ፣ በሚመጣው ዓመት በመስከረም ወር መግቢያ ገደማ ነው ማርስ የምትደርሰው።

ቻይና፣ በኅዋ ፣ እ ጎ አ እስከ 2020 የኅዋ ምርምር ጣቢያ ከማቋቋሟ በፊት በዚህ ወር ውስጥ፤ «ዩቱ » ያለቻትን መንኮራኩር በተሣካ ሁኔታ ጨረቃ ላይ ማሳረፏና ፣ መረጃ በማሰባሰብ ላይ መሆኗ ታውቋል። ቻይና ፤ የተለያዩ ሳይንሳዊ መረጃዎችን ፤ በተጨማሪም ጨረቃ ላይ ስለሚገኝ የማዕድን ዓይነትና መጠን ጭምር ነው ለማወቅ ጥረት የምታደርገው። ማርስ አንድ ዘመን፤ ህይወትን መደገፍ የሚያስችሉ ተፈላጊ ነገ ሮች ፤ ፈሳሽ ውሃ ጭምር እንደነበራት ፤ አሁንም የረጋ ውሃ እንዳላት ፤ ባፈሯና በመሳሰለው ምርምር የምታደርገው የዩናይትድ ስቴትስ መንኮራኩር (CURIOSITY) ተግባሯን በማከናወን ላይ ናት ። ማርስ ፣ አሁንም ለህይወት መሠረቶች የሆኑት ተፈላጊ ነገሮች፤ ሃይድሮጂን፤ ኦክስጂን፤ ካርበን ፣ ናይትሮጂን፤ ፎስፈረስና ድኝ አላት።

እ ጎ አ እስከ 2030 ሰውን ወደ ማርስ ለመላክ ሩሲያም ዩናይትድ ስቴትስም ሐሳቡ ቢኖራቸውም፤ በዚህ መስክ በሚደረገው ምርምር፣ ቻይና፣ በአንዳንድ ነጥቦች ሁለቱንም መንግሥታት መቅደም የምትችልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል የገመቱ አልታጡም። ዩናይትድ ስቴትስ፤ በመስከረም ወር መግቢያ ላይ 1970 ያመጠቃቸቻው VOYEGER 1 እና VOYEGER 2 የተሰኙት መንኮራኩሮቿ በረጅም ጉዞአቸው፣ ጁፒተር፤ ሳተርን ዩሬነስንና ኔፕቱን አልፈዋል። በተለይ ቮየጀር አንድ ከፀሐያዊ ጭፍሮች ድንበር አልፋ በኅዋ ያን ያህል ርቀት ለመጓዝ የመጀመሪያቱ ሰው ሠራኅሽ መንኮራኩር ለመባል በቅታለች። በፕሉቶኒየም ኃይል የምትንቀሳቀሰው ይህችው መንኮራኩር፤ እ ጎ አ በ 2025 የሚያነጉዳትን ኃይል ታጣለች። እስከዚያ ግን ወደ ከዋክብት ቀጣና ማምራቷን ትቀጥላለች።

በአንታርክቲክ የበረዶ ተራሮች በተተከለ ቴሌስኮፕ አማካኝነት፤ በኅዋ፣ ንዑሳን ኑውትሮኖች መከሠታቸው፤ በኅዋ እጅግ ግዙፍ ጽልመት የለበሱ ጉድጓዶች፣ የሚፈነዱ ትላላቅ ከዋክብት፤ እንዲሁም ጽልመታዊ ቁስ አካል (ዳርክ ማተር) ምን እንደሆነ ምሥጢሩን ላይቶ ለማወቅ አመቺ ሁኔታ ሳይፈጥር አልቀረም።

በብሪታንያው ተወላጅ ፒትር ዌር ሒግስና ቤልጂጋዊው ፍራንሷ ኦንግሌርት፣ በነባቤ ቃል ቢገለጽም ፣ ለማግኘት አስቸግሮ የኖረው ገዝፍ ያላቸው ቁስ አካላት ሁሉ መነሻው እጅቅ ኢምንት ቅንጣት፣ «ሂግስ ቦሰን» ፣ በሐምሌ ወር 200 ዓ ም ፣ በቤተ ሙከራ እውን ተብሎ ከተረጋገጠ ውዲህ ፤ ሁለቱ የፊዚክስ ሊቃውንት የዘንድሮውን የኖቤል ሽልማት ከ 15 ቀን በፊት ነበረ በእስቶክሆልም የተቀበሉት።

ለፍጥረተ ዓለም ቁስ አካል ኢምንት መሠረት ስለሚሰኘው «ሒግስ-ቦሰን» (የእግዚአብሔር ቅንጣት)ነባቤ ቃል ያሠፈሩት ፒትር ዌር ሒግስ ፤ በአውሮፓው የኑክልየር ምርምር ተቋም(European Organization for Nuclear Research) በግዙፍ አቶም ጭፍላቂ መሣሪያ Large Hadron Collider አማካኝነት ምሥጢሩ ተደረሰበት እንደተባለ ፣ የተሰማቸውን ስሜት እndዲህ ነበረ የገለጡት።
«በዚህ አስደናቂ ግኝት የተሳተፉትን ሁሉ እኔም እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ። ለእኔ፤ ይህ በእውነት በሕይወት ዘመኔ የተከሠተ ተዓምራዊ ጉዳይ ነው።»

የ CERN ዋና ሥራ አስኪያጅ ጀርመናዊው Rolf-Dieter Heuer በሐምሌ ወር 2004 ዓ ም የአቶም ኢምንት ቅንጣት (ሂግስ- ቦሰን) በቤተ ሙከራ መገኘቱ እንደተገለጠ በበኩላቸው እንዲህ ማለታቸው የሚታወስ ነው።

«እንደሚመስለኝ፤ ትልቅ ግኝት ነው። የአቶም ኢምንት ቅንጣት አግኝተናል። እንደምገምተው50 ዓመት ያህል ስንፈልገው የነበረ ነው። ይህ ስንፈልገው የነበረው፤ እጅግ ኢምንቱ የአቶም ኢምንት ቅንጣት ነው፣ አይደለም፥--እኛ ከሚፈለገው የአቶም ቅንጣት ጋር ተመሳሳይነት ያለውን ለማግኘት በቅተናል። »

በሥነ ቅመማ ፤ Martin Karplus, Michael Levitt, እና Arieh Warshel የተባሉት ተመራማሪዎች ፣ በኮምፒዩተር ሞዴል፤ እንደ ምስለ-በረራ፣ የንጥረ ነገሮችን ምሥጢራዊ ፈጣን ጉዞ በማሳየት፣ በሰውነት አካላት ውስጥ፣ ንጥረ ነገሮች እንዴት እንደሚንሸራሸሩ በማስረዳታቸው ፣ ይህ በፊናው ደግሞ መድኃኒቶችን፣ የፀሐይ ብርሃንና ሙቀት ተቀባይ ስስ ጡቦችን አሠራር ለማሻሻል የሚበጅ በመሆኑ ፤ ምርምራቸው ለሽልማት አብቅቷቸዋል።

በህክምናው ዘርፍ ደግሞ ፣ የኅዋሳትን የማጓጓዣ ሥርዓትን ፣ ከአንድ ኅዋስ ወደ ሌላው ንጥረ ነገሮች የሚመላለሱበትን መንገድ፣ በምርምራቸው በማስረዳት ነው ፤ ጄምስ ኢ ሮትማን፤ ራንዲ ደብልዩ ሼክማን፣ እና ቶማስ ሲ ሱድሆፍ ለሽልማት የበቁት።

ሳይንስ በሚያትተው ዝግመታዊ ለውጥ ረገድ ፣ በ 2013 የተካሄደ የምርምር ውጤት፤ የሰዎች ሁሉ የመጀመሪያው አባት ከ 340 ሺ ዓመታት በፊት የኖረ መሆኑን ጠቁሞአል።

ይህ ደግሞ ከ 140,000 ዓመታት አንስቶ በአፍሪቃዊ -አሜሪካዊ ሰው ጭምር የተከሠተ ነው።

በፕላኔታችን የአንደኛነቱን ደረጃ በያዘው «ማሪያነ ትሬንች» በተሰኘው በሰላማዊው ውቅያኖስ ፣ 11,000 ሜትር ጥልቀት ባለው አዘቅት ወለል ፣ ሕይወት ያላቸው ኢምንት ነፍሳት፤ ባካቴሪያዎች እንደሚገኙ ተመራማሪዎች አስታውቀዋል።

በፕላኔታችን ፣ በቅዝቃዜ ፤ ከ 0 በታች 89,2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ክብረ ወሰን በያዘው አንታርክቲክ በተለይ በበረዶ ከተሸፈነ 15 ሚሊዮን ዓመታት ያስቆጠረ ነው በተባለለት ቮስቶክ ሥር ባለ ሐይቅ የተለያዩ ንዑሳን ነፍሳት ሳይገኙ አይቀርም ተብሏል። 7 ሺ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት ባለው በጥልቁ የከርሰ ምድር ክፍልም ተመሳሳይ ነፍሳት በተለይ 19 ዓይነቶች ይገኛሉ ነው የተባለው። --- --------------(ይቀጥላል)

ተክሌ የኋላ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic