ሳይንስና ሥነ ቴክኒክ፤ ለኃይል ምንጭና አጠቃላይ ዕድገት፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 30.03.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ሳይንስና ሥነ ቴክኒክ፤ ለኃይል ምንጭና አጠቃላይ ዕድገት፣

በኢንዱስትሪ የገሠገሡት ፤ በነዳጅ ዘይት ሀብትና በሌሎች ጥሬ ሀብቶች የታወቁት ፣ ምንም ዓይነት ማዕድን የሌላቸው አገሮችም ቢሆኑ፣ ለዕድገት ማንቀሳቀሻ ሞተር አድርገው የሚመለከቱት ሳይንስንና ሥነ ቴክኒክን ነው።

default

በነዳጅ ዘይት ሀብት የከበረችው ንዑሷ ቓጣር፣ እ ጎ አ በ 1995 ዓ ም ያቋቋማችው ድርጅት ከሰኔ 20 -22 ,2003 ዓ ም፣ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሚባል ዓለም አቀፍ የሳይንስ ጋዜጠኞች ጉባዔ(World Conference of Science Journalists 2011)(WSCJ 2011)ዶሃ ላይ ያዘጋጃል። ጉባዔውን ፤ የዐረብ ሳይንስ ጋዜጠኞች ማኅበር፣ የዩናይትድ እስቴትስ ብሔራዊ የደራስያን ማኅበር፣ እንዲሁም በፋርሱ ባህረ-ሰላጤ አካባቢ የሚገኙ ባለሃብቶች ናቸው።

ጤናይስጥልኝ እንደምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን፣ ዓለም አቀፍ የሳይንስ ጋዜጠኞች ጉባዔ፣ እንዲሁም ሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ ለኃይል ምንጭና አጠቃላይ ዕድገት በሚሉ አርእስት የተጠናቀረውን ቅንብር እናሰማለን።

ጉባዔው በመጀመሪያ በካይሮ ፣ ግብፅ ነበረ እንዲካሄድ የታሰበው። ይሁንና በግብፅ በተከሠተው የህዝብ አመጽና አገሪቱም ገና በለውጥ ሂደት ላይ በመሆኗ ጉባዔውን ሌላይቱ የዐረብ አገር ቓጣር ለማሠናዳት ተዘጋጅታለች። የዚሁ የቓጣር፣ የትምህርት የሳይንስና ልማት በጎ አድራጎት ድርጅት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፋቲ ሳዑድ እንዳሉት፤ የሳይንስ ምርምርን ሂደት በቀጣይነት ማራመድና አዳዲስ የምርምር ክንዋኔዎችን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ መምከር ከድርጅታቸው ዐበይት ትኩረቶች መካከል አንዱ ነው።

ዓለም አቀፍ የሳይንስ ጋዜጠኞች ጉባዔ፣ ሲካሄድ ዘንድሮ ማለትም የሰኔው 7ኛ ይሆናል ማለት ነው። በዘንድሮው ጉባዔ 800 ያህል የሳይንስ ጋዜጠኞች፤ ማለትም ፤ ከፕረስ፤ ራዲዮ ቴሌቭዥንና ኢንተርኔት ክፍል የተውጣጡ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። በተጠቀሰው ጉባዔ፣ የአየር ንብረት ለውጥን የመሳሰሉ ዐበይት ጉዳዮች ትኩረት ሳይደረግባቸው አይቀርም።

ጉባዔው በሚካሄድበት ወቅት፣ «የሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ ማዕከላትን« የዩኒቨርስቲ ግቢዎችን ፤ የምርምር ተቋማትን፤ አብያተ-ሙከራዎችን ና የመሳሰሉትን የመጎብኘትና ሐሳብ የመለዋወጥ መርኀ-ግብር መዘርጋቱም ተመልክቷል።

በዶሃ ፤ ቓጣር የሚገኘው የሀገሪቱ የትምህርት የሳይንስና ልማት በጎ አድራጎት ድርጅት፣ ዓላማው ማኅበረሰባዊ ልማት እንዲስፋፋ ማብቃት ነው። መጠን ያለፈ የተቃጠለ አየር(CO2) ያጀበውን ኤኮኖሚ ፣ ለተፈጥሮ አካባቢ በሚበጅ ሥነ -ቴክኒክ ተመርኩዞ ማሻሻልም ሌላው ዐቢይ ዓላማው ነው። ትምህርት፣ ሳይንስና ምርምር ከዚህም ጋር ተያይዞ ማኅበራዊ ልማት ፤ አገሪቱ ልዩ ግምት የሰጠቻቸው ጉዳዮች መሆናቸውም ተጠቅሷል።

በሰሜን ምሥራቅ ጃፓን ፤ በፉኩሺማ የአቶም ኃይል ማመንጫ ጣቢያ እጅግ አሳሳቢ እክል ካጋጠመ ወዲህ የዚህ የኃይል ምንጭ ጉዳይ በሰፊው ማነጋገሩን ቀጥሏል። እርግጥ ነው የአውሮፓው ኅብረት አባል ሀገራት መንግሥታት ሁሉ፤ ስለተጠቀሰው የኃይል ምንጭ ተመሳሳይ አቋም የላቸውም ። ለዚህም ነው የአቶም ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቻቸውን በበጎ ፈቃድ ብቻ ሊያስምረምሩ እንደሚችሉ የተስማሙት። ጀርመን፣ በቅርቡ ፣ ከ 17ቱ የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታሮቿ መካከል 7 ቱን ለጊዜው ለ 3 ወር እንዲዘጉ ማድረጓ የሚታወስ ነው። በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ 17 ከመቶ የኃይል ምንጭ የምታገኘው ከታዳሽ የኃይል ምንጭ ነው። ብዙዎች ጀርመን መቶ በመቶ በታዳሽ የኃይል ምንጮች መገልገል ትችላለች ሲሉ አያዛልቅም በማለት የሚያስጠነቅቁ ደግሞ አልታጡም። ባለፉት 10 ዓመታት ፤ ጀርመን በፀሐይ ፣ በነፋስ ፤ በውሃ ኃይል እንዲሁም በአዝርእት፣ ዕጽዋትና ፍግ መጠቀሙን ይበልጥ ገፍታበታለች። በነፋስ ኃይል ፤ በአሁኑ ጊዜ 27 ጊጋዋት ጉልበት በማመንጨት እንዲሁም በዛ ያሉ የኃይል ምንጮችን ፣ድንጋይ ከሰል፣ የተፈጥሮ ጋዝና የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታሮችን የሚያስንቅ አቅም አለ። እ ጎ አ በ 2020፣ 30 ከመቶ ያህል የኃይል ምንጭ ከታዳሽ የኃይል ምንጮች ሊገኝ እንደሚችል ተነግሯል።

እጅግ ዘመናዊ በሆነ ሥነ-ቴክኒክ በመጠቀም ፤ አሁን 27 ጊጋዋት የሚያመነጩትን በነፋስ ኃይል የሚሽከረከሩ ኃይል አመንጪ ግዙፍ ፉሪቶችን በአዳዲስ በመተካት አሁን የሚገኘውን የኃይል ምንጭ በ 4 እጥፍ ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ታውቋል።

የጀርመን ፌደራል የታዳሽ ኃይል ምንጮች ጉዳይ ድርጅት ፕሬዚዳንት ዲትማር ሹዑትዝ እንደገለጡት፣ የተጠቀሰውን የኃይል ምንጭ መጠን ለማስገኘት፣ እ ጎ አ እስከ 2020 ዓ ድረስ፣ 150 ቢሊዮን ዩውሮ ወጪ ይጠይቃል። በአሁኑ ጊዜ 370,000 ያህል ሰዎች በታዳሽ የኃይል ምንጭ ድርጅቶች ውስጥ ይሰራሉ። ወደፊት ይኸው የኃይል ምንጭ ዘርፍ ለ 500,000 ሰዎች ሥራ እንደሚያስገኝ ተስፋ ይደረጋል።

የያዝነው ዘመን 2011 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የሥነ-ቅመማ መታሰቢያ ዘመን መሆኑን ከዚህ ቀደም በዚህ ክፍለ-ጊዜ በተደጋጋሚ የጠቀስን ይመስለኛል። ከሥነ-ቅመማ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያውያን ምሁራን ዘንድ ፣ ከአዲሱ 2011 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መባቻ ወዲህ ምን በመደረግ ላይ እንደሆነ በማይንትዝ ዩኒቨርስቲ፣ የሚገኙትን ኑክልየር ነክ የሥነ ቅመማ ምሁር ዶ/ር ጌዴዎን ጌታሁንን ጠይቄ ነበር።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ