ሳዑዲ የሚኖሩ የስልጤ ብሔረሰብ ሽምግልና | ባህል | DW | 16.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ሳዑዲ የሚኖሩ የስልጤ ብሔረሰብ ሽምግልና

በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ ከተማ የሚኖሩ የስልጤ ብሄረሰብ አባላት ያቋቋሙት የሀገር ሽማግሌዎች ምክር ቤት በብሄረሰቡ መካከል የሚከሰቱ ችግሮችን በመፍታት እርቅና ሰላም እያወረደ ነው ፡፡ የዕለቱ የባህል አምዳችን ባህል ባህር ተሻግሮ በሰው ሀገር ላይ የተከታይ ህዝቦቹንም ሆነ የተወለወጆቹን ማህበራዊ ፍትህ ለማስፈን የሚጫወተውን ሚና እንቃኛለን፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:37

የስልጤ ብሔረሰብ ሽምግልና

 

የሽማግሌዎች ምክር ቤቱ  በወረዳ ፣ በዞን እና በበላይ ጠባቂ ሽማግሌዎች የተዋቀረ ነው ፡፡ በሪያድ የሚኖረው አብዛኛው የስልጤ ብሄረሰብ አባል ዘመናዊ የሚባለው የፍትህ ስርዓት አንድም በቀላሉ ተደራሽ ባለመሆኑ ሁለትም   ከውስብስብነቱ አንጻር ባህላዊውን የዳኝነት ስርዓት መርጧል፡፡ በተለይ በገንዘብ መካድም ሆነ በትዳር መካከል በሚደርሱባቸው በደሎች የተማረሩ ሴቶች ባህላዊው የሽምግልና ስርዓት ፍትህ እያስገኘላቸው መሆኑን የሽምግልና ምክር ቤት አባላቱ ይናገራሉ፡፡

የስልጤ ዞን በመእከላዊው ኢትዮጵያ በደቡብ ክልል ይገኛል ፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያም በርካታ የብሄረሰቡ አባላት ይኖራሉ፡፡ ብሄረሰቡ ባብዛኛው በንግድ ስራ ነው የሚተዳደረው፡፡ አኗኗራቸውም የተቀራረበ፤ እርስ በርስ የሚያስተሳስሯቸው ድርና ማጎች፣ እቁብና እድሮች የጠበቁ ናቸው፡፡ የሪያድ ስልጤዎች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር በሚያጋጥሟቸው የእለት ግጭቶችንም ሆነ ገንዘብ ነክ የሆኑ አለመግባባቶችን በባህላቸው መሰረት እያከሙ እና እየፈወሱ ናቸው፡፡

በሪያድ የሚኖሩ ስልጤዎች ከየተወለዱባቸው  ስምንቱም ወረዳዎች ነዋሪነታቸው እዚሁ ሪያድ የሆነ አምስት አምስት የሀገር ሽማግሌዎች መርጠው 45 የሽማግሌዎች ምክር ቤት ሰይመዋል ፡፡ ክሶችም ሆኑ ሌሎች አቤቱታዎች  መጀመሪያ በወረዳ ደረጃ በተዋቀሩት አምስት ሽማግሌዎች ይታያሉ፤ አብዛኞቹም ጉዳዮች በዚሁ ደረጃ እልባት ያገኛሉ ፡፡ በወረዳ ደረጃ እልባት ያላገኙት ደግሞ 45 ሽማግሌዎች በሚሰየሙበት የዞን ምክር ቤት ይታያሉ፡፡ በ45 የሽማግሌዎች ምክር ቤት መፍትሄ ያለገኙ ጉዳዮች ወደ አምስቱ የብሄረሰቡ የበላይ ጠባቂ ሽማግሌዎች ይመራሉ፡፡ ተከሳሾችም ሆኑ ተበዳዮች ይግባኝ ማለት ከፈለጉም ለበላይ ጠባቂ ሽማግሌዎቹ ነው የሚያቀርቡት፡፡ ኢማም ዑመር ዑስማን ወይንም በስፋት በሚታወቁበት አቡ ፉአድ አንጋፋ ሽማግሌ፣ የጉባዔው መስራችም ፣የበላይ ጠባቂው ምክር ቤትም አባል ናቸው፡፡ባህላዊውን የሽምግልና ስርዓት ባህር አሻግረው እዚህ ሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ ማምጣቱ ለምን አስፈለገ፤

ችግር ብልሀትን ይፈጥራል ይባላል ፡፡ ያሉት የፍትህ ተቋማት የኛ ህብረተሰብ ሙሉ በሙሉ ሊጠቀምባቸው አይችልም፡፡ ሲበደል የተለያየ ቦታ ሄዶ አቤቱታ የማቅረብ አቅም የለውም፡፡ በዚህም የተነሳ ይበደላል፡፡ በተለይ ሴቶች በአደራ ያስቀመጡትን ገንዘብ ይበሏቸዋል፡፡

ጉዳዮች በተለያየ መንገድ ወደ ሽምግልናው ጉባዔ ይመጣሉ፡፡ በቀጥታ በከሳሽ አማካኝነት ከሚመጡ ክሶች በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ኤምባሲም ወደ ሽምግልና ጉባዔው የሚመሩ።አቤቱታዎች ያጋጥማሉ ፡፡ የሽማግሌዎቹ ጉባዔ ራሱም ወደ ጉዳዮች የሄደባቸው ጊዜዎች አሉ።  አበጋዝ አንዋር ሻፊ የሽምግልናው ጉባዔ ሊቀመንበር ናቸው፡፡

እንደ ጉዳዩ ውስብስብነት ከ3-4 ቀጠሮ የሚፈጅ አለ። በተለይ በቅርቡ በስራ ቦታ ላይ በኦሮሞ ብሄረሰብ አባላት እና በስልጤዎች ዘንድ በተነሳ ጠብ ከኦሮሞዎቹ ወገን የተወሰኑ ይጎዳሉ ፡፡ የሳዑዲ ፖሊስ በጉዳዩ ገብቶ የተጎዱት ወደ ሀኪም ቤት ጉዳት አድራሾቹም ወደ እስር ቤት  ይወሰዳሉ ፡፡ በድርጊቱ የተቆጡት ኦሮሞዎች በሪያድ የሚገኙ ስልጤዎችንም ሆነ የንግድ ተቋሞቻቸውን ለማጥቃት ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የሽምግልና ጉባኤው ሊቀመንበር አበጋዝ አንዋር ሻፊ ከኦሮሞዎቹ ጋር የተነሳው ጠብ ሽማግሌ ባይገባበት ኖሮ አደጋው የከፋ ይሆን እንደነበር ይገልጻሉ፡፡

በስልጤ ዞን የዳሎቻ ወረዳ ተወላጆች በሆኑ የሪያድ ነዋሪዎች መካከል በፌስ ቡክ ላይ ተፈጸመ በተባለ የስም ማጥፋት ተግባር ከፍተኛ ጸብ ተነስቶ ጉዳዩም በሳዑዲ የደህንነት መስሪ ቤት ዘንድ ተይዞ እያለ ተበዳይ ነን በሚሉ ቤተሰቦችና በዳይ በተባሉት ቤተሰቦች መካከል ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ጦሱም ከሪያድ አልፎ ሀገር ቤት ዳሎቻ ወረዳ ላይ ተጻራሪ ቤተሰቦች  ለጠብ በሚጋበዙበት ሰዓት አሁንም የሽማግሌዎች ጉባዔ ቀን ከሌት በስረ ነገሩ ላይ በመምከር ውሳኔ በማስተላለፍ በሪያድም ሆነ በሀገር ቤት የተፈጠረውን ችግር እልባት ሰጥተዋል ፤ አጥፊዎችም ካሳ እንዲከፍሉ አድርገው እርቀ ሰላም አውርደዋል፡፡ አበጋዝ አንዋር ሻፊ። የሽምግልና ጉባዔው ከተቋቋመ ወዲህ ለውጥ አለ ወይ ኢማም ዑመር ዑስማን ለሽምግልናው ጉባዔ ጥሪ መልካም ምላሽ የማይሰጥ፣ ለውሳኔዎችም አልገዛ ያለ በዳይነቱ የተረጋገጠና በእምቢተኛነቱ የጸና ግለሰብ ጉዳዩ ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ፣ ለስልጤ ዞን ጽህፈት ቤት እና ሀገር ቤት ላሉ ቤተ ሰቦቹ በዳይነቱም ሆነ እምቢተኛነቱ ተገልጾ ይተላለፋል ፡፡ በእምቢተኛነቱ የጸናም ከብሄረሰቡ ሽማግሌዎች ውግዘትና  እርግማን ይጠብቀዋል፡፡ ይህንን የሚፈቅድ ማንም የብሄረሰቡ አባል እንደማይኖር አብዛኞቹ ይስማማሉ፡፡

በሪያድ የስልጤ ብሄረሰብ ባህላዊ የሽምግልና ጉባዔ ከተቋቋመ ጀምሮ ለበርካታ ችግሮች እልባት ከመስጠቱም በላይ በመኖሩ ብቻ ለተጎጂዎች ታላቅ ተስፋ ለጉልበተኞች እና ለህገ ወጦች ደግሞ ማስፈራሪያና አደብ ማስገዣ ሆኗል፡፡ እኔ በታደምኩበት አንድ የሽምግልና ምሽት ከረጅም ሙግትና ክርክር በኋላ ፍርድ ሲሰጥ አስተውያለሁ ፡፡

የሽምግልና ጉባዔው አባላት ህዝባቸውን ከማገልገላቸው በላይ የሚያረካቸው ምንም ነገር እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ የቤተሰባቸውን ጊዜ ገንዘባቸውንም ሆነ ማንነታቸውን ሰውተው ለማምጣት የሚተጉት ፍትህ ሰፍኖ ማየታቸው የዚህም ሂደት አካል በመሆናቸው በገንዘብ የማይተመን እርካታ እና ደስታን እንደሚያገኙ ግን ይናገራሉ ፡፡ እርካታው ከዚህም በላይ ታላቅ መንፈሳዊ ፋይዳ አለው፡፡አቶ ሙዘሚል ሼክ አደም የሽምግልና ጉባዔው ምክትል ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ፍትህ ፈልገው ወደ ሽምግልናው ጉባዔ አቤቱታቸውን ካሰሙት መካከል የተወሰኑትን አነጋግሬያለሁ የሽምግልናው ጉባዔ ባይኖር ሊደርስባቸው የሚችለውን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ስነ ልቦናዊ ቀውስ አስከፊ ይሆን እንደነበር ይስማማሉ፡፡

ባህል ተበዳይን ሲክስ፣ ስብራትን ሲጠግን ባየሁበት በዚሁ ጉባዔ ከሳሽም ተከሳሽም ምርቃት አገኝተዋል ከሳሽም ጽናቱን ፈጣሪ እንዲያላብሰው ፤ ተከሳሽም እዳውን ባግባቡ ለመክፈል እና የሽማግሌዎችን ቃል እንዲያከብር አላህ ይረዳው ዘንድ ከፍተኛ ዱአ ተደርጎላቸዋል፡፡ የክስ ሂደቱም ሆነ ውሳኔዎቹ በዳይን ከመቅጣት እና ተበዳይን ከመካስ በዘለለ ጠብን ከልብ ውስጥ በማድረቅ በቀልን የማያስፋፉ ውሳኔዎችን ለመታዘብ ችያለሁ ፡፡ ዘመናዊ የሚባለው የፍትህ ስርዓት በቀላሉ የማይጠግናቸው ወይንም እንደተሰበሩ የሚተዋቸው ማህበራዊ ግንኙነቶች በባህላዊው የፍትህ ስርዓት ሙሉ በሙሉ ወይንም አብዛኛውን ጊዜ የሚጠገኑበት ጊዜ ያመዝናል፡፡ ዘመናዊው የፍትህ ስርዓት አጥፊን ከመቅጣት ባለፈ ለሚኖረው ቀጣይ ማህበራዊ ግንኙነት ይህ ነው የሚባል መፍትሄ ሲያስቀምጥ አይስተዋልም ፡፡ ባህላዊው የፍትህ ስርዓት ግን ቂምን ከልብ ማድረቅን ጨምሮ የተዋቀረ ስርዓት ነው፡፡ 

ስለሺ ሽብሩ

ኂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic