ሳዑዲ አረቢያ 47 ሰዎችን በሞት ቀጣች | ዓለም | DW | 02.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሳዑዲ አረቢያ 47 ሰዎችን በሞት ቀጣች

ሳዑዲ አረቢያ ታዋቂ የሺዓ እስልምና የሃይማኖት አባትን ጨምሮ 47 ሰዎችን በሞት ቀጣች። ድርጊቱ ቁጣ ቀስቅሷል። በሞት ከተቀጡት 47 ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ከዐሥር ዓመት በፊት አል-ቃዒዳ በፈጸመው ጥቃት የተከሰሱ የሱኒ እስልምና ተከታዮች ናቸው ተብሏል። ኒምር አል-ኒምራንን ጨምሮ አራቱ የሺዓ እስልምና እምነት ተከታዮች ናቸው።

አራቱ የሺዓ እስልምና እምነት ተከታዮቹ በሞት የተቀጡት የፖሊስ መኮንን በመግደል ነው ስትል ሳዑዲ አረቢያ ገልጣለች። የሞት ፍርዱ በአስራ ሁለት የሳዑዲ አረቢያ ግዛቶች በእሩምታ ተኩስ እና ተከሳሾችን በመቅላት ተግባራዊ መደረጉን ሬውተርስ ዘግቧል። አገሪቱ ተግባራዊ ያደረገችው የሞት ቅጣት እኩልነትን ፍለጋ በሱኒ ጽንፈኞችም ይሁን አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የሺዓ እስልምና ተከታዮች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በትዕግስት እንዳማታልፍ ለማሳየት ቢሆንም በቀጣናው በሁለቱ የእስልምና ዘውጎች መካከል ያለውን ቁርሾ እንዳባባሰው ሬውተርስ ዘግቧል። በሳዑዲ አረቢያ ምስራቃዊ ግዛት ቃቲፍ በተሰኘ አካባቢ በርካታ የሺዓ እስልምና ተከታዮች በኒምር አል-ኒምራን መገደል ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸውን የዐይን እማኝ ለሬውተርስ ተናግረዋል። የሳዑዲ አረቢያ ተቀናቃኝ የሆነችው ኢራን እና አጋሮቿ የሞት ቅጣቱን አምርረው ሲያወግዙ የአገሪቱ ፖሊስ የሺዓ እስልምና ተከታዮች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ተቃውሞ ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ስጋት የጸጥታ ጥበቃውን አጠናክሯል። ኢራን ሳዑዲ አረቢያ የወሰደችው ርምጃ ዋጋ ያስከፍላታል ስትል ዝታለች። ለኢራን መንግስት ቅርበት ያላቸው አህመድ ኻታሚ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የሳዑዲ አረቢያ ንጉሳዊ ቤተሰብ «ከታሪክ ገጾች ይፋቃል» ሲሉ ተናግረዋል። የሊባኖሱ ሒዝቦላህ የሞት ቅጣቱን «ግድያ» ሲለው በርካታ የኢራቅ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከኢራን ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎችም ሳዑዲ አረቢያን አውግዘዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሳዑዲ አረቢያ በኒምር አል-ኒምራን ላይ ተግባራዊ ያደረገችው የሞት ቅጣት ንጉሳዊው አስተዳደር «ተቃዋሚዎቹን በሙሉ ለማጥፋት» የሚያደርገው ጥረት አካል ነው ሲል ተችቷል። በጀርመን ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አንድ ስማቸው እንዲገለጥ ያልፈለጉ ባለሥልጣን የሃይማኖት አባቱ ሼክ ኒምር አል-ኒምራን ላይ የተፈጸመው የሞት ቅጣት እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል። ባለሥልጣኑ በዚህ ንግግራቸው እንዲህ አይነት ድርጊት በጀርመን ኢ-ሰብአዊ የሆነ የቅጣት አይነት ተደርጎ እንደሚታይ ዳግም አረጋግጠዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ