ሳምንታዊ የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 15.08.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ሳምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ትናንት እና ከትናንት በስትያ በእንግሊዝ በተከናወኑ የፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ከዋነኞቹ ቡድኖች መካከል ማን ዩናይትድ ድል ቀንቶት አምሽቷል። የሁልግዜም ተቀናቃኞቹ ቸልሲ፣ አርሰናልና ሊቨርፑል ግን የድል ስካር እንዳማራቸው መቅረቱ ታወቀ።

default

ድል የቀናቸው ሻልካዎች

ዱባይ ውስጥ ማራዶና ሲያሰለጥን ቁጭ ብሎ ለመመልከት የሚመጣው ተመልካች ቁጥር ማየሉ ተነገረ። ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ግዜ በዓለም አቀፍ ጁዶ ውድድር ላይ ተፋላሚዎችን ልታሰልፍ መሆኑ ተገለፀ። አሜሪካዊቷ ሴሬና ዊሊያምስና ሰርቢያዊው ጆኮቪች በሜዳ ቴኒስ ውድድር አሁንም ሃያልነታቸውን አስመሰከሩ። ሌሎች ስፖርት ነክ አጫጭር ዘገባዎችንም አካተናል፤ ዝርዝሩን እንደየቅደም ተከተሉ ከቀጣዩ የጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ትንታኔ በኋላ ይዘንላችሁ እንቀርባለን።

እግር ኳስ

ትናንት እና ከትናንት በስትያ በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ዘጠኝ የእግር ኳስ ፍልሚያዎች ተከናውነዋል። ታዲያ እንደ ሻልካ የሰመረለት፣ ጮቤ የረገጠ ቡድን ሊገኝ አልቻለም። አብዛኛዎቹ ውድድሮች በጠባብ ልዩነትና ነጥብ በመጋራት ሲጠናቀቁ፤ ሻልካ ኮሎኝን ከትናንት በስትያ እንዳይሆኑ አድርጎ ነው የሸኘው። አምስት ግቦችን አስታቅፎ ኮሎኝን አንገት አስደፍቷል። ለመፅናኛ እንዲሆን ግን የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ተሰላፊው የኮሎኙ ፖዶልስኪ ሻልካ ላይ አንድ ግብ ሊያስቆጥር ችሏል። ለሻልካ ሆልትቢ እና ራውል አንድ አንድ ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፉ፤ የዕለቱ ጀግና ሆኖ ያመሸው ክላስ ያን ሁንቴላር ሀትሪክ ለመስራት በቅቷል።

ባለፈው ሳምንት የመጀመሪያውን ውድድር በቦሪሲያ ሞንሼን ግላድባህ በደጋፊው ፊት 1 ለባዶ የተቀጣው ሃያሉ ባየር ሙኒክ፤ ቅዳሜ ለት የግብ ዕዳውን በዎልፍስቡርግ ላይ ሊያካክስ ችሏል። መደበኛው ሠዓት ተገባዶ በተጨመረው የባከነ ደቂቃ ላይ ነበር ሉዊዝ ጉስታቮ ከመረብ ባሳረፋት ግብ ሙኒክ ዎልፍስቡርግን 1 ለዜሮ ሊያሸንፍ የቻለው። ጨዋታው እንደተገባደደ ጉስታቮ ለጋዜጠኞች በሰጠው ቃለ መጠይቅ እንዲህ ሲል ደስታውን ገልጿል፥

«ትንሽ ከበድ ያለ ነበር፤ ሆኖም ግን ቡድናችን አሸንፏል። እስከመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ተፋልመናል፤ እናም ግቡ የዛ ውጤት ይመስለኛል።»

የተሸናፊው ዎልፍስቡርግ አሰልጣኝ ፌሊክስ ማጋዝ፤ ባየር ሙኒክ አሸናፊ ሊሆን የቻለው በዳኛ ስህተት ነው ሲሉ ሞግተዋል። ለዚያ ማረጋገጫ ደግሞ የተቀረፀው ቪዲዮ በድጋሚ ይታይልኝ ማለታቸውም ታውቋል።

የባለፈው ዙር ዋንጫ ባለቤት ቦሩሲያ ዶርትሙንድም ቅዳሜ ለት የሽንፈትን ፅዋ ከተጎነጩት ተርታ ሊሰለፍ ግድ ሆኖበት ነበር። የሆፈንሀይሙ ሳሊሆቪች ጨዋታው በተጀመረ በ9ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ድርትሙንዶች የሽንፈትን ዜማ እያንጎራጎሩ ወደ ቤታቸው አቅንተዋል። የተሸናፊው ቦሩሲያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ ዩርገን ክሎፐ፥

« ተበሳጭቻለሁ። በእርግጥ መጀመሪያ ላይ ጫና ተፈጥሮብን ነበር፤ ኋላ ላይ ግን በጣም ጥሩ ተጫውተናል። ዛሬ በግልፅ በርካታ የግብ ዕድሎች አምልጠውናል። ሆፈንሀይም አደገኛ ሆኖ ነው የቆየው ምንም ጥያቄ የለውም። እንሸነፋለን ብሎ ያሰበ አልነበረም።»

በቅዳሜው ግጥሚያ ማይንዝ ፍራይቡርግን እንዲሁም ሀኖቨር ኑረምበርግን በተመሳሳይ 2 ለ1 በሆነ ውጤት ሊያሸንፉ ችለዋል። ሀምቡርግና ሄርታ ቤርሊን 2 ለ2 አቻ ሲለያዩ፤ ቦሩሲያ ሞንሽን ግላድባህና ሽቱትጋርትም 1ለ 1 አቻ ወጥተው ነጥብ ተጋርተዋል። ትናንት ካይዘርላውተርንም እንደዚሁ ከአውስቡርግ ጋር በአቻ 1ለ 1 ተለያይቶዋል። ባየር ሌቨርኩሰን ብሬመንን 1 ለ ባዶ በመርታት 3 ነጥብ ይዞ ለመውጣት ችሏል።

በዚህም መሰረት ማይንዝና ሀኖቨር በ6 ነጥብ በመሪነቱ ተርታ ሲሰለፉ፤ ሽቱትጋርትና ቦሩሲያ ሞንሽን ግላድባህ በ2 ነጥብ ዝቅ ብለው ይከተሏቸዋል። ዎልፍስቡርግ፣ ሻልካ፣ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ፣ ብሬመን፣ ሆፈንሀይም፣ ኑረምበርግ፣ ባየር ሙኒክና ባየር ሌቨርኩሰን እያንዳንዳቸው 3 ሶስት ነጥብ ይዘው ከ5ኛ እስከ 12ኛ ተርታ ላይ ይገኛሉ። ፍራይቡርግ፣ ሄርታ ቤርሊን፣ ሀምቡርግና ካይዘርላውተርን አንድ አንድ ነጥብ ያላቸው ሲሆን፣ በግብ ይለያያሉ። በሁለቱ ግጥሚያዎች ምንም ነጥብ ያልያዘው ብቸኛው ቡድን ኮሎኝ ነው።

ከዛው ከእግር ኳስ ሳንወጣ አሁን የምንሸጋገረው ወደ እንግሊዝ ይሆናል። በእንግሊዝ የፕሬሚየር ሊግ ፍልሚያ ትናንት እና ከትናንት በስትያ 7 ጨዋታዎች ተከናውነው ነበር። እንደቦልተን ግን በግብ የተንበሸበሸ የለም። ቦልተን ዊጋንን 4 ለ1 ቀጥቶ ሸኝቷል። ብላክበርን በዎልቭስ 2ለ 1 ተሸንፏል። ፉልሀም ከአስቶን ቪላ እንዲሁም ኒውካስል ከአርሴናል ያለምንም ግብ ባዶ ለባዶ ተለያይተዋል። ከማንቸስተር ዩናይትድ በስተቀር ዋነኞቹ ቡድኖች አልተሳካላቸውም። ልክ እንደመድፈኞቹ ሁሉ ቸልሲና ሊቨርፑልም ነጥብ ተጋርተው ነው የወጡት። ትናንት ቸልሲ ከስቶክ ጋር ዜሮ ለዜሮ ሲለያይ፤ ሊቨርፑል ከትናንት በስትያ ከሰንደርላንድ ጋር 1 ለ1 ነጥብ ተጋርቷል። ማን ዩናይትድ ትናንት ዌስት ብሮምዊች አልቢዮን 2 ለ 1 ረትቷል።

ለማን ዩናይትድ በ13ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያዋን ግብ ያስቆጠረው ግልፍተኛው ግን ደግሞ አደገኛው አጥቂ ዋይኒ ሮኒ ነበር። ሮኒ ከአሽሌ ያንግ የተላከለትን ኳስ ተቀብሎ በጋብሪየል ታማስ እግሮች መሀል በማሾለክ መሬት ለመሬት የመታት ኳስ ከመረብ ቀላቅላለች። ሆኖም ግን በ 37ኛው ደቂቃ ላይ የዩናይትዶችን ደስታ ያጨለመ የተቀናቃኞቻቸውን ሀሴት ግን የጨመረ ክስተት ተፈጠረ። በ18.3 ሚሊዮን ፓውንድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ የተገዛው ግብ ጠባቂ ዴ ጊያ በሻን ሎንግ የተመታችውን ደካማ ኳስ ሊያድን አልተቻለውም። ግቡ ለዌስት ብሮሚች እንደስጦታ ነበር የተቆጠረው። እናም ማንቸስተር ዩናይትድ የመጀመሪያውን አጋማሽ በአቻ እረፍት ሊወጣ ችሏል። ከረፍት መልስ ግን አሽሌ ያንግ ግብ ጠባቂው ዴ ጊያን ከሀፍረት ታድጎታል። አሽሌ ከግራ በኩል በፍጥነት ገብቶ የመታትን ኳስ የዌስት ብሮሚቹ ስቴቨን ራይድ ጨርፎ በገዛ መረቡ ላይ ግብ አስቆጥሯል። በዚያም ማን ዩናይትድ 2 ለ 1 ሊያሸንፍ ችሏል። በእርግጥ ሩኒ ለናኒ ያቀበለውን ያለቀለት ኳስ ናኒ ከግብ ጠባቂው ብዙም ሳይርቅ ከማዕዘን ውጭ ያጓናት ኳስ ማንቸስተሮችን ለበለጠ ድል የምታበቃ ነበረች።

በሌላ ውድድር ሊቨርፑል 50 ሚሊዮን ፓውንድ አውጥቶ ካስፈረማቸው 5 አዳዲስ ተጫዋቾቹ አራቱን ቢያሰልፍም ድል ሳይቀናው ቀርቷል። የ 5 ጊዜያት የአውሮፓ ባለድሉ ሊቨርፑል አሰልጣኝ ኬኒ ዳግሊሽ ተጨዋቹቾ እስኪላመዱ ድረስ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም ሲሉ ደጋፊዎቻቸው እንዲታገሱ ጠይቀዋል። «ለመጀመሪያ ጊዜ አንፊልድ ላይ ወጥቶ መጫወት እንዲህ ቀላል አይምሰላችሁ። በተለይ ትናንት ለፈረመው ለጆሴ» ሲሉ ቅዳሜ ለት ገልፀዋል። ሊቨርፑል ቡድኑን ለማጠናከር በዚህ ዓመት ብቻ 100 ሚሊዮን ፓውንድ ማውጣቱ ተገልጿል። ለሊቨርፑል በ12ኛው ደቂቃ ላይ ሱዋሬዝ፣ ለሰንደርላንድ ደግሞ ላርሰን በ57ው ደቂቃ ላይ ግቦችን በማስቆጠር ቡድኖቻቸው ነጥብ ተጋርተው እንዲወጡ አስችለዋል። ቸልሲ በፈርናንዶ ቶሬዝም በዲዲየር ድሮግባም ግብ ማስቆጠር ተስኖት ሲወጣ፤ አርሰናልም ከአንድ ቀን በፊት የቸልሲ ዕጣ ነበር የገጠመው። የቶትንሀምና የኤቨርተን ጨዋታ ለደህንነት ሲባል ለሌላ ግዜ መዛወሩ ተገልጿል። ምክንያት፤ ለንደንና አካባቢዋ ላይ የተከሰተው የሰሞኑ ረብሻ። ዛሬ ልክ መደበኛው ስርጭታችን ሲገባደድ ደግሞ የማንቸስተር ሲቲና የስዋንሲ ግጥሚያ ይጀምራል።

Asiatische Stars in der Bundesliga Flash-Galerie

አሁን ዓለም አቀፍ ስፖርት ነክ ዜናዎችን አጠር አጠር አድርገን እናሰማለን። ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር ሩብ ፍፃሜው ላይ ተዳርሷል። ሚክሲኮ ኮሎምቢያን 3 ለ1፣ ፈረንሳይ ናይጀሪያን 3 ለ2 አሸንፈዋል። እንዲሁም ብራዚል ስፔንን በፍፁም ቅጣት ምት መለያ 4 ለ2 ስትረታ፤ ፖርቹጋልም አርጀንቲናን በዚያው በፍፁም ቅጣት ምት መለያ 5 ለ4 አሸንፋለች።

አርጀንቲናውያን ደጋፊዎች ሀዘን ሲውጣቸው ዱባይ ውስጥ አርጀንቲናዊውን የኳስ እንቁ ለመመልከት የሚመጡ ታዳሚያን ቁጥር ተበራክቷል። የ50 ዓመቱን ማራዶና ለመመልከት። ማራዶና የዱባዩን አል ዋስል ቡድን ለማሰልጠን የ2 ዓመታት ውል ፈርሙ ስከሳምንት በፊት ስራ መጀመሩ ታውቋል። ታዲያ ማራዶና በሚያሰለጥንበት ሜዳ በርካታ ደጋፎቹ ምስሉ የታተመባቸውን ካናቴራዎች ለብሰው መለማመጃ ቦታውን አጣበውታል። ያም በመሆኑ ቡድኑ ተጨማሪ መቀመጫዎችን ለማሰራት መገደዱ ተነግሯል። ማራዶና የዱባይን ሀይለኛ ሙቀት ለማስታገስ ሜዳው ላይ ተጋድሞ በፍጥነት ቀዝቃዛ ውሃ አምጡልኝ ሲልም ተደምጧል።

አትሌቲክስ

በ100 ሜትር ፈጣን ውድድር ሶስተኛው ፈጣን አትሌት ጃማይካዊው ስቴቭ ሙሊንግስ ሀይል ሰጪ ንጥር መጠቀሙን ወኪሉ አስታወቁ። የ28 ዓመቱ ወጣት አትሌት ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ድርጊት ለ2 ዓመታት ከስፖርት ታግዶ እንደነበር ይታወቃል። እናም አሁን የዕድሜ ልክ ከስፖርት አውድ የመታገድ ዕጣ ሊገጥመው እንደሚችልም እየተገለፀ ነው።

በሌላ ዜና ደግሞ የቀድሞው የ100 ሜትር ሩጫ አሸናፊ አሜሪካዊው ማይክ ሮጀር ተመሳሳይ ክስ ደርሶበታል። የሮጀር ወኪል ለዜና አውታሮች እንደገለፀው ከሆነ ማይክ ሬድ ቡል የተባለውን መጠጥ የጠጣ መስሎት ሌላ ሀይል ሰጪ መጠጥ መጠቀሙ ነው ስህተቱ ብሏል።

ጁዶ

በዓለም አቀፉ የጁዶ ፍልሚያ ውድድር ላይ ሁለት ተወዳዳሪዎች ኢትዮጵያን ወክለው ሊሰለፉ እንደሆነ ተገለጸ። ፈረንሳይ ላይ ከነገ ሳምንት በሚጀምረው ውድድር የሚሳተፉት የ19 ዓመቷ ቆንጂት ጉሌቻና የ31 ዓመቱ ሰይፉ መኮንን መሆናቸውም ታውቋል። መቀመጫቸውን ጀርመን ካደረጉት የኢትዮጵያ ጁዶና ጁ ጂትሱ ማኅበር ፕሬዚዳንት ትናንት በተላከልን መግለጫ ሁለቱ ተወዳዳሪዎች የመጓጓዣና በፈረንሳይ ቆይታቸው የመኝታ እንዲሁም የምግብ ወጪያቸውን የሚችልላቸው ዓለም አቀፉ የጁዶ ፌዴሬሽን እንደሆነ ተጠቅሷል። ውድድሩ ለ6 ቀናት ቀጥሎ የፊታችን እሁድ ይጠናቀቃል።

ሜዳ ቴኒስ

ታዋቂዋ ሴሬና ዊሊያምስ ትናንት 6ለ4 እና 6ለ2 በሆነ ልዩነት ሳማንታ ስቶሱርን አሸነፈች። የ29 ዓመቷ ሴሬና በዓለም የስፖርተኞች ደረጃ 80ኛ ላይ ስትገን በሰሞኑ ውጤቷ ወደ 31ኛ ደረጃ እንደምትሸጋገር ይጠበቃል። በሜዳ ቱንስ ውድድር ግን አሁንም በዓለም አንደኛ እንደሆነች ነው። በወንዶች የሜዳ ቴኒስ ውድድር ደግሞ ሰርቢያዊው ጆኮቪች በተደጋጋሚ ማሸነፉን እንደቀጠለ ነው። ትናንት ማርዲ ፊሽን 6ለ2 3ለ6 እና 6ለ4 ሊያሸንፍ ችሏል። የ24 ዓመቱ ጆኮቪች በሜዳ ቴኒስ ውድድር አንደኛነቱን ሊነጠቅ አልቻለም።

ኦሎምፒክ

ቱርክ የ2020 ኦሎምሊክን ለማዘጋጀት እንደምትወዳደር ጠቅላይ ሚንስትሯ ሬሴፕ ታዪፕ ኤዶዋን ገለፁ። ቱርክ ለዚህ ዓላማዋ ስትል ዋና ከተማዋ ኢስታንቡል ውስጥ 75 000 ተመልካቾችን የሚያስተናግድ ስታዲየም ከ10 ዓመታት በፊት ገ።ንብታ መጨረሷ ይታወቃል። በ2020 ከካታሯ ዶሃ ጋር በቅንጅት ኦሎምፒክን ለማዘጋጀት ከኢስታንቡል በተጨማሪ ሮም፣ ቶኪዮና ማድሪድም ለመወዳደር ተርታ ውስጥ ገብተዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic