ሳምንታዊዉ ስፖርት | ስፖርት | DW | 08.08.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ሳምንታዊዉ ስፖርት

በሳምንቱ ማብቂያ ላይ የተከናወኑ ዓበይት የእግር ኳስ፣ የቴኒስ፣ የቢስክሌት እና የዋና ውድድሮች ውጤትን አሰባስበናል። ዋነኛ ትኩረታችንም በጀርመን ቡንደስ ሊጋና በእንግሊዙ የማህበረሰቡ ዋንጫ ላይ ይሆናል። አንዳንድ የዝውውርና መሰል እግር ኳስ ነክ ዜናዎችንም አካተናል።

default

የባየርን ሙኒክ ግብ ጠባቂ ማኑኤል ኖይማን

እግር ኳስ፥

ትናንት በእንግሊዝ በተካሄደው የማህበረሰቡ ዋንጫ ውድድር ሁለቱ ማንቸስተሮች ተጋጥመው፤ ዩናይትድ ሲቲን በባከነ ሠዓት 3 ለ 2 በሆነ ጠባብ ልዩነት ማሸነፉ ታውቋል። የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ መሰል ባለቀ ሠዓት የሚከሰት ሽንፈት ካሁን በኋላ አይገጥመንም ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል። ዝርዝሩን ከጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ አስገራሚ ውጤት በኋላ ይዘንላችሁ እንቀርባለን።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ፍልሚያ ሃያላኑ ባየርን ሙኒክና ባየር ሊቨርኩሰን ያልተጠበቀ የሽንፈት ፅዋ ተጎነጩ። በቡንደስ ሊጋው የመጀመሪያ ዙር የመክፈቻ ውድድር ትናንት በሜዳው ቦሪሲያ ሞንሼን ግላድባህን ያስተናገደው የአውሮፓው ሃያል ቡድን ባየር ሙኒክ ሽንፈትን ተከናንቧል። ባየርን የመግቢያ ቲኬት ተሽጦ ባለቀበትና 69 000 ተመልካቾችን ባስተናገደውና አሊያንስ አሬና በተሰኘ ሜዳው ፊት የተረታው 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ነው። ነገሩን የበለጠ አስገራሚ ያደረገው ደግሞ በ35 ሚሊዮን ዩሮ የተገዙት የብሔራዊ ቡድኑ ግብ ጠባቂ ማኑኤል ኖየርና ተከላካዩ ጄሮሜ ቦዋቴንግ በፈጠሩት ስህተት ባየርን የመሸነፉ ጉዳይ ነው። በ62ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት የተለጋችውን ኳስ ነፃ ለማውጣት ግብ ጠባቂውና ተከላካዩ በፈጠሩት ግራ መጋባት በትውልድ ብራዚላዊ የሆነው የቤልጂጉ አጥቂ ኢጎር ዴ ካማራጎ ከመረብ አሳርፏታል። በዚያም ግላድባኸር በባየር ሙንሽን ሜዳ ከ17 ዓመታት ወዲህ አሸናፊ ሊሆን በቅቷል።

ትናንት ምንም እንኳን ባየር ሙኒክ ሮበንና ሪበሪን ሳያሰልፍ ወደ ሜዳ የገባ ቢሆንም ተቀናቃኙ እንግዳ ቡድን ቦሩሲያ ሞንሽንግላድባህ ገና ከመነሻው የመረጠው መከላከልን ነበር። የሞንሽንግላድባህ ጠንካራ ግብ ጠባቂ ማርክ አንድሬ ቴርስቴገን የትናንቱን ድል አስመልክቶ ሲናገር።

«አንድ ሆነን መታየት ነበር የፈለግነው። እንደማስበው ያንን ዛሬ አከናውነናል። እያንዳንዱ ተጫዋች ታግሏል፣ ተሟሙቷል። እናም ምናልባት ውጤቱ በወኔ ከመጫወት የመነጨ ነው። እኔ ትኩረት ሰጥቼ ልናገር የምፈልገው በቡድን የተሻለ እንድንጫወት ተጠይቀን እንደነበርና ያንንም መተግበራችንን ነው። ኳሷን በመቆጣጠሩ ደረጃ አላሰብንበትም፤ ይሁንና ግን ባገኘኸው አጋጣሚ ጎል ካገኘህም ያም ይቆጠርልሀል»

Bundesliga 1. Spieltag 2011/2012 FSV Mainz 05 - Bayer Leverkusen

የሌቨርኩሰኑ ሳሚ አላጉዊ

ከዚያው ከቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ፍልሚያ ሳንወጣ፤ ትናንት ሌላኛው ሃያል ባየር ሌቨርኩሰን በማይንስ 2 ለ ባዶ በሆነ ውጤት ተቀጥቷል። የባለፈውን ዙር ውድድር ዶርትሙንድን ተከትሎ በሁለተኛነት ያጠናቀቀው ሌቨርኩሰን ዘንድሮ ገና ከመነሻው ዕድል የጠመመችበት ይመስላል። 32 443 ተመልካቾችን ባስተናገደው የማይንስ ሜዳ የተጓዘው ሌቨርኩሰን የመጀመሪያ ግብ የተቆጠረበት በ32ኛው ደቂቃ ላይ በሳሚ አላጉዊ ነበር። የሌቨርኩሰን ግብ ጠባቂ የተላከለትን ኳስ ወደ ጎን አወጣለሁ ሲል ኳሷን በማልኮስኮሱ በቅርብ የነበረው ሳሚ አላጉዊ በፍጥነት ደርሶ ከመረብ ቀላቅሏታል። ከረፍት መልስ መደበኛው ሁለተኛው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 4 ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ በኦመር ቶፕራክ ራሱ ላይ በተቆጠረበት ሁለተኛ ግብ ሌቨርኩሰን በሽንፈት ከሜዳው ተሰናብቷል። ከአሸናፊው ቡድን ማይንስ ወደ ሌቨርኩሰን የተዘዋወረው አንድሬ ሹውርለ የሌቨርኩሰንን ሽንፈት ሲያብራራ፥

«ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ እስከመጨረሻው በቀላሉ ጥሩ አልተጫወትንም፤ እናም የመጀመሪያ ጨዋታውን ማይንስ ውስጥ ተሸንፈናል። ዛሬ የተረዳነው ያንን ነው። በግጥሚያው ማጥቃት ላይ አላተኮርንም፤ ማጥቃት ላይ ካላተኮርክ ደግሞ ያው ግልፅ ነው መሸነፍ ይኖራል»

ቅዳሜ ለት በተከናወኑ የቡንደስ ሊጋ ግጥሚያዎች ብሬመን ካይዘርስላውተርንን፤ እንዲሁም ሀኖቨር ሆፈንሀይምን 2 ለ ባዶ ሲያሰናብቱ፣ ሽቱት ጋርት ሻልካን 3ለ ምንም አሸንፏል። በተመሳሳይ ውጤት ዎልፍስቡርግ የቦን ከተማ አጎራባች የሆነውን የኮሎኝ ከተማ ቡድን ኮሎኝን ረትቷል። አውግስቡርግና ፍራይቡርግ 2 ለ2 አቻ ሲለያዩ፣ ኑረንበርግ ቤርሊንን 1 ለ ምንም አሸንፏል።

ከዛው ከእግር ኳስ ሳንወጣ አሁን የምንሸጋገረው ወደ እንግሊዝ ይሆናል። በእንግሊዝ የኮሚኒቲ ሺልድ ውድድር ፍፁም ባለቀ ሰዓት ትናንት ማንቸስተር ዩናይትድ ማንቸስተር ሲቲን 3 ለ 2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የማህበረሰቡን ዋንጫ ለ4ኛ ግዜ ሊያነሳ በቅቷል። ትናንት ለማንቸስተር የቁርጥ ቀን ልጅ በመሆን መላ ማን ዩናይትዶችን ያስቦረቀው ናኒ ነበር። ሁለቱ የአንድ ከተማ ቡድኖች ሁለት እኩል ሆነው ወደ ፍፃሜው ቢጠጉም በባከነ ሰዓት በማሸነፍ ታሪከኛ የሆኑት ማን ዩናይትዶች መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በተጨመረው ጥቂት ደቂቃ ነበር ለድል የበቁት።

በመጀመሪያው አጋማሽ የማንቸስተር ሲቲዎቹ ጆሌዎን ሌስኮትና ኤዲን ድዜኮ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ማን ዩናይትድን ሲመሩ ቆይቶ ነበር። በኋላ ላይ ግን ክሪስ ስማሊንግና ናኒ በተከታታይ አግብተው ዩናይትዶችን ከጉድ አውጥተዋቸዋል። የፕሬሚየር ሊጉ የዘንድሮ አሸናፊ ማን ዩናይትድ በዓምስት ተከታታይ ዓመታት ዘንድሮም ለአራተኛ ግዜ የማህበረሰቡን ዋንጫ በመብላት ሃያልነቱን አስመስክሯል። «አጨዋወታችንን በተመለከተ ሙሉ በሙሉ በጣም ጥሩ አያያዝ እንደነበረን እርግጠኛ ነበርኩ» ሲሉ አሰልጣኙ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል። « ኳሱን የተቆጣጠርነው እኛ እንደሆንን እየተሰማኝ በመጀመሪያው አጋማሽ 2 ለ ባዶ መመራታችንን ማመን አልቻልኩም ነበር። ይሁንና ግን ለተጫዋቾቼ ምስጋና ይግባቸውና ብዙም ሳይረበሹ ኳስ በመጫወት የሚገባንን ውጤት አስገኝተዋል» ሲሉም አክለዋል የማን ዩናይትዱ የረጅም ዘመን አሰልጣኝ።

ማን ዩናይትድ አዲስ ያስፈረማቸውን ግብ ጠባቂው ዳቪድ ዴ ጊያንና የክንፍ ተጫዋቹን አሽሌ ያንግን በትናንቱ ግጥሚያ አሰልፎ ነበር። በአንፃሩ ማንቸስተር ሲቲ በቅርቡ ያስፈረመውን ሰርጂዮ አጉዌሮን በተጠባባቂ ወንበር ላይ አስቀምጦ ነበር የዋለው። ዣቪየር ሄርናንዴዝ በጉዳት ለማን ዩናይትድ ሳይሰለፍ ቀርቷል። የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማንቺኒ ቡድናቸው ከእንግዲህ ባለቀ ሠዓት ለሚከሰት የሽንፈት ሰለባ እንደማይደረግ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫቸው አስታውቀዋል።

በተያያዘ ዜና ማንቸስተር ሲቲ ተቀናቃኙ ማን ዩናይትድ አይኑን የጣለበትን የኢንተር ሚላኑ አማካይ ለመጥለፍ ከፍተኛ ገንዘብ አሰናድቷል የሚባለውን ዜና የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ አሉባልታ ሲሉ አጣጥለውታል። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ግን ሲቲዎች የኢንተር ሚላኑ ስኔይደርን ከማን ዩናይትድ ተሻምተው ለመውሰድ 30 ሚሊዮን ፓውንድ አዘጋጅተዋል።

ሌላ ዝውውር ነክ ዜና እንደሚጠቁመው ለሆነ፤ ዲዲየር ድሮግባና አፍሪቃዊያን የቡድን ጓዶቹ ቸልሲ ውስጥ ፈተና እንደሚጠብቃቸው ታውቋል። የ33 ዓመቱ አዲሱ የቸልሲ አሰልጣኝ አንድሬ ቪላስ ቦዋስ በእድሜ አቻቸው የሆነው ዲዲየር ድሮግባን ጨምሮ ሁሉም ተጫዋቾች በቡድኑ ለመቆየት ብቃታቸውን ማስመስከር አለባቸው ብለዋል። የ33 ዓመቱ ድሮግባ «ይሄ የአሰልጣኙ ምርጫ ነው። ሆኖም ግን ለኔ በቆይታዬ ሁሉ የሆነው እንደዚህ ነው። እድሜዬ አሁን 33 በመሆኑ ከቡድኑ አንጋፋው ተጫዋች እኔ ነኝ። የሆነ ለየት ያለ ሊመስል ይችላል፤ ግን በዛ አልጨነቅም። መጫወት ከተገባኝ እጫወታለሁ» ሲል ከቸልሲ ጋር የገባው ውል ሊቋረጥ ጥቂት ወራት የቀሩት ድሮግባ ገልጿል። ለፖርቹጋላዊው አዲሱ የቸልሲ አሰልጣኝ ከድሮግባ ባሻገር አፍሪቃውያኑ ሳሎሞን ካሉ፣ ጆን ኦቢ ሚኬል እና ሚካኤል ኤሲያን ማንነታቸውን ሊያሳዩ ግድ ነው በቡድኑ ለመቆየት።

አሁን አጠር አጠር አድርገን አንዳንድ የዝውውር ዜናዎችን እና ሌሎች ስፖርታዊ ክንውኖችን እናስደምጣችኋለን። ሪያል ማድሪድ ድንቅ የእግር ኳስ ተሰጥዖ ባለቤቱን የ19 ዓመቱ ብራዚሊያዊ ወጣት ተጫዋች ሊያስፈርም ከጫፍ መድረሱ ትናንት ተገለፀ። የ19 ዓመቱ ወጣት አጥቂ ኔይማር ቡድኑ ሳንቶስ የኮፓ ሊበርታዶሬስ አሸናፊ ከሆነ በኋላ ወይ ወደ እንግሊዙ ቸልሲ አለያም ወደ ስፔኑ ማድሪድ ሊያቀና ዝንደሚችል እየተነገረ ነበር። አሁን ግን ማድሪድ ከሳንቶስ ቡድን ጋር ከስምምነት መድረሱ ተነግሯል።

የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ተጫዋች ቤኒ ማካርቲ አፍሪቃውያን ተጫዋቾች በአውሮፓ ቡድኖች በደል ይደርስባቸዋል ሲል ትናንት ለሰንደይ ታይምስ ጋዜጣ ገለጸ። የ33 ዓመቱ ማካርቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውፍረት ችግር እንደተጠቃ ይታወቃል። ማካርቲ ከአያክስ አምስተርዳም ውጪ በተጫወትኩባቸው ዌስት ሀም፣ ብላክበርን፣ ሴልታቪጎና ፖርቶ ቡድኖች ውስጥ አፍሪቃውያን ተጫዋቾች ይጠቃሉ ትንኮሳም ይደርስባቸዋል ብሏል። ማካርቲ ባሁኑ ወቅት ከዌስት ሀም ተሰናብቶ የደቡብ አፍሪቃው ኦርላንዶ ፓይሬትስን ተቀላቅሏል።

Tennis Wimbledon Novak Djokovic Petra Kvitova NO FLASH

ሰርቢያዊው ኖቫክ ድዮኮቪች በስተቀኝ

ቴኒስ፥

ታዋቂዋ የሜዳ ቴኒስ ጀግና ቬኑስ ዊሊያምስ በሮጀር ካፕ ውድድር እንደማትሰለፍ ዛሬ ገለፀች። በህመምም ምክንያት በቶሮንቶው ውድድር እንደማትሰለፍ የገለፀችው ቬኑስ በሁኔታው በጫም ተበሳጭቼያለሁ ብላለች። ሀኪሞቿን ትናንት ካናገረች በኋላ ሻል እንዳላትም ጠቁማለች።

በወንዶች የሜዳ ቴኒስ ውድድር ደግሞ ሰርቢያዊው ኖቫክ ድዮኮቪች ከአስሩ ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተወዳዳሪዎች ተርታ የአንደኝነቱን ደረጃ አስጠበቀ። ስፔናዊው ራፋኤል ናዳል ሁለተኛ ደረጃ ሲሰጠው፣ የስዊሱ ተወላጅ ሮጀር ፌደረር ሶስተኛ ለመሆን በቅቷል። ደረጃውን የሰጠው በእንግሊዘኛ ምህፃሩ ATP የተሰኘው የቴኒስ ባለሙያዎች ማኅበር መሆኑ ታውቋል።

ብስኪሌት፣

አውስትራሊያዊው ቢስኪሌተኛ ሲሞን ጌራን ትናንት የዴንማርኩን ውድድር በአንደኛነት አጠናቀቀ። ለስድስት ተከታታይ ዙሮች በተከናወነው አጠቃላይ ውድድር ግን 24ኛ ደረጃን ነው ያገኘው። በጥቅል የዙሮቹ አሸናፊ የሆነው ሆላንዳዊው ቴዎ ቦስ ነው።

ዋና፥

ለሶስት ጊዜያት የዓለም የዋና ውድድር አሸናፊ የሆነችው የ16 ዓመቷ ታዳጊ ሚሲ ፍራንክሊን ቅዳሜ ለት ፈጣን በሆነ ሁኔታ የ100 ሜትር የነፃ ቀዘፋ ውድድር አሸናፊ ሆነች። አሜሪካዊቷ ወጣት የ100 ሜትሩን ዋና ያገባደደችው 53.63 በሆነ ሰከንድ ነበር ። ይህ ውጤቷ ባለፈው በቻይና ሻንጋይ በተደረገው ውድድር የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሊያስደርግ የሚችልል ውጤት መሆኑም ተጠቁሟል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic