ሳላፊት የነበረችዉ ጀርመናዊት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 15.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ሳላፊት የነበረችዉ ጀርመናዊት

ወጣቶች የራሳቸዉን ሕይወት ራሳቸዉ ለመምራት በሚሞክሩበት ጊዜ አንዳንዴ ነገሮች በትክክለኛዉ መንገድ ላይሄዱ ይቻላሉ። ልክ ሽቴፊ እንደሆነችዉ ማለት ነዉ።

በማኅበራዊ መገናኛ ምታገኛቸዉን መረጃዎች ተጠቅማ የአክራሪዎችን አካሄድ ጭራሽ ወደጀርመን ለማምጣት ነበር ያቀደችዉ። የ25 ዓመቷ ወጣት ያን አካሄዷን ከለወጠች ሁለት ዓመታት ቢሆናትም አሁንም ግን ከዚያ ስሜት አልወጣችም።

«ቤተሰቦች አሉሽ፤ በጂሃዲስትነት ብትሞቺ ወደገነት ትገቢያለሽ» ይህ የእነሱን ፍልስፍና እንድትከተይ የሚሸነግሉበት ማሳመኛ ነዉ ትላለች ከሳላፊስትነት የተለወጠችዉ ወጣት ጀርመናዊ። ለስምንት ዓመታት ያህል በዚህ መስመር ዘልቃለች።

«በኢንተርኔት የሚሰራጩት ቀስቃሽ መልዕክት ያዘሉት ቪዲዮዎች ፎቶዎችና ትርጉሞች አሏቸዉ። እነሱ ናቸዉ እኔን በጣም የቀሰቀሱኝ። በአንድ ወቅት በቃ መሰደድ አለብኝ ብዬ የተነሳሁበት ጊዜ ነበር። ወደጂሃድ ማለትም ወደቅዱሱ ጦርነት መሄድ አለብኝ አልኩ። በቃ ወደጦርነት ለመሄድ በጣም ፈለኩኝ።»

የሽቴፊ የእስላማዊ ፅንፈኝነት ጉዙ እንደሌሎቹ ወጣቶች በማኅበራዊ መገናኛዎችና ኢንተርኔት ነዉ የተጀመረዉ። «ለእኔ ሁሉም ሙስሊም እኩል ነበር። በዚህ እረገድ ምንም ልዩነት አድርጌ አላዉቅም። በኢንተርኔት ጓደኝነት ወደ100 የሚሆኑ ሰዎች ነበሩኝ፤ ከእነሱ መካከልም እጅግ አክራሪዎችም ይገኛሉ።» ትላለች ሽቴፊ የኋላ ታሪኳን ስታወጋ። የ25ዓመቷ ወጣት የግለሰቦቹን ማንነት ለመጠበቅ ስትል እዉነተኛ ስማቸዉን መጠቀም አትፈልግም። ይህ የማደርገዉ ግን ስለፈራሁ አይደለም ነዉ የምትለዉ እሷ። ሽቴፊ የ15 ዓመት ታዳጊ ወጣት ሆና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለች ነዉ ስለእስልምና ያወቀችዉ።

«ያኔ ነዉ የሆነ መነሳሳት ያደረብኝ። ከዚያ በፊት ስለእስልምና የማዉቀዉ አልነበረም፣ ስለሃይማኖት ባጠቃላይ የማዉቀዉ አልነበረም። ያ ለእኔ ምንም ማስረዳት የምችለዉ ጉዳይ አልነበረም።»

የክፍል ጓደኛዋ አባት ኢማም ናቸዉ፤ እናም አንድ ቀን ወደመስጊድ ጋበዟት። ብዙም ሳትቆይ እስልምናን ተቀበለችና መፀለይ ቁርአን ማንበብ እና የእራስ ክንብንብ ማለትም ሂጃብ መልበስ ጀመረች። ዓመት በጨመረ ቁጥር ሽቴፊ ስለአዲሱ ሃይማኖቷ ይበልጥ ማወቅ ትፈልግ ጀመር። ምርምሯን ስታጠናክርም በፌስቡክ በኩል «ሚላቱ ኢብራሂም» ማለትም «የአብርሃም ማኅበረሰብ» የሚል የጂሃዲስቶች ቡድንን ታገኛለች።

«እኔ ምንነቱን አላወኩም ነበር። እዚያ ላይ የሚለጠፉ ነገሮችን ቪዲዮዎችን ሁሉ ለራሴ መቅዳት ጀመርኩ። በየጊዜዉ የሚለጠፉትን እኔም ወደራሴ ገፅ እወስዳቸዉ ጀመር።»

«በሚላቱ ኢብራሂም» መረጃዎች መሳቧንም ትቀጥላለች። በአንድ ወቅትም ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖችን ማዉገዝና ጥላቻን በፌስ ቡክ መለጠፍ ይጀምራሉ። እንደዉም ግድያም ሳይቀር ያዉጃሉ።

«በነፃነት የመወሰን እድሉ ከእንግዲህ አይኖርህም። የግንኙነት አድማሴ በጣም ጠባብ ነበር። በአንድ አቅጣጫ ብቻ ነበር ማሰብ የምችለዉ። እንደዉ ፈፅሞ ጸሎት የማያዉቀዉ የቀድሞ ባለቤቴ እንኳን በጣም ነፃ ሰዉ ነበር። በዚህ ምክንያትም እሱን ፈትቼ ወደአፍጋኒስታን ሄድኩና አንድ ሙጃሂዲን አገባሁ።»

ከዚህ በኋላም ከአብዛኛዎቹ የቀድሞ ጓደኞቿ ጋ የነበራት ግንኙነት ተበላሸ። ከወላጆቿ ጋ የነበራት ቅርርብም እንዲሁ በችግር የተሞላ ሆነ። ሲጀመር ወደእስልምና ሃይማኖት መቀየሯ ሊገባቸዉ አልቻለም። የሽቴፊ አክራሪነት ከእለት ወደዕለት እየጠነከረ ሲሄድም ጣልቃ መግባታቸዉን አቆሙ።

እንዲያም ሆኖ ካለቤተሰቦቿ ድጋፍ ራሷን ከገባችበት ለማዉጣት መንገድ ጀመረች። ለዚህም ምክንያት የሆናት ከ«ሚላቱ ኢብራሂም» ቡድን ሰባኪዎች አንዱ ራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለዉ ቡድን አባል መሆኑ የተገለፀ ግለሰብ ገነት ገብቶ ስለሚገኘዉ ጥቅምና ሙስሊም ካልሆኑ ሰዎች መጠንቀቅ እንደሚገባ የሰጣቸዉ የቅስቀሳ ትምህርት ነበር። ሽቴፊ ይህ ጥርጣሬ አሳደረብኝ ትላለች። እሷ ማወቅ የፈለገችዉ የበሰለ የሃይማኖት ትምህርት ቢሆንም በሴሚናሩ የቀረበዉ ይበልጥ ስለሞትና ፊትን በመሸፈን ራስን ስለመለወጥ የሚቀሰቅስ በመሆኑ የምትከተለዉን መስመር መጠራጠሯን ቀጠለች። ሂጃብ የምትለብስ ብትሆንም አጠቃላይ ፊቷን እንድትሸፍን የቀረበላትን ጥያቄ ባለመቀበሏ እንደዉም በፌስቡክ የእነሱን ማንነት የምትሰልል ተደርጋ ተወሰደች። ይህም የመጨረሻዬ ሆነ ትላለች።

«ያ ለእኔ የመጨረሻ ዉሳኔ ላይ እንድደርስ አደረገኝ። እስከዚህ ሄጃለሁ ከዚህ በላይ አልጓዝም የሚል። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ስልም አሰብኩ። ይህ እኔ ልከተለዉ ከፈለኩት እስልምና ሃይማኖት ጋ አብሮ አይሄድም።»

እናም ጨርሳ ከቡድኑ እስክትወጣ ሌላ ስድስት ወር ፈጀባት። አሁን ለዘብተኛ የሆነ መስመር የሚከተል ሙስሊም ማኅበረሰብ አባል ናት። ትምህርቷንም መማር ቀጥላለች። ወደፊት እሷ ያለፈችበትን ተሞክሮ ለሌሎች ለማካፈል ቢቻልም በትምህርት መልክ ለማቅረብ ፍላጎት አላት።

ክላዉስ ሩየክ እና ኢታ ኒሃዉስ

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic