ሲአይኤን ያጋለጠው ሠነድ | ዓለም | DW | 10.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ሲአይኤን ያጋለጠው ሠነድ

የአሜሪካው የስለላ ተቋም «CIA» በሽብርተኝነት ተጠርጣሪ እስረኞችን በምርመራ ወቅት በከፍተኛ ሁናቴ ማሰቃየቱን የሚያጋልጠው ሠነድ በስተመጨረሻ ይፋ ሆኗል። የሰብአዊ መብት ተሟጋቿ ሎውራ ፒተር ሠነዱን፦ «ለበርካታ አሜሪካውያን እጅግ አስደንጋጭ ነው» በማለት ገልፀዋል።

ይኽ ሠነድ ይፋ ከመሆኑ በፊት የዩናይትድ ስቴትስ የምክር ቤት አባላትን እጅግ አከራክሯል፣ አጨቃጭቋል፤ በበርካቶች ዘንድም በጉጉት ሲጠበቅ ነበር። ሠነዱ «911» በመባል ከሚታወቀው የመስከረሙ የአሸባሪዎች ብርቱ ጥቃት ወዲህ፥ የዩናይትድ ስቴትስ የደኅንነት አባላት በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ከተያዙ እስረኞች መረጃ ለማውጣጣት በሚል በምርመራ ወቅት ያከናወኑትን ከባድ የማሠቃየት ሂደት ያጋልጣል። ሎውራ ፒተር ሠነዱ «እጅግ ጠቃሚ» ነው ይላሉ።

«እጅግ ጠቃሚ መረጃ ነው። የሲ አይ ኤ የገዛ ጥራዝ እንደሚያሳየው ማሰቃየቱ ከዚህ ቀደም ከሚታሰበው በከፋ መልኩ እጅግ ጭካኔ የተመላበት ብቻ ሳይሆን፤ ጠቃሚ መረጃ ለማውጣጣት ስኬታማ መንገድ እንዳልነበረ ነው።»

አሜሪካዊቷ ሴናተር ዳያን ፋይንስታይን

አሜሪካዊቷ ሴናተር ዳያን ፋይንስታይን

ይፋ ለመሆን አምስት ዓመት የፈጀበት ይኽ ከ600 በላይ ገጾች ያካተተው ሠነድ ለበርካታ ጥያቄዎች በሚገርም ሁናቴ ምላሽ እንደሰጠም ተገልጧል። አሜሪካዊቷ ሴናተር ዳያን ፋይንስታይን ሠነዱን ለምክር ቤቱ አባላት ይፋ ሲያደርጉ አንዳችም ዙሪያ ጥምጥም መጓዝ አላስፈለጋቸውም። በቀጥታ አነጋገር ሠነዱን ቢያንስ 119 ሰዎች «በሲ አይ ኤ ከሀገር ውጭ በምሥጢር መታሰራቸውን እና ባንዳንድ ቦታ ዎችም ላይ ማሠቃየትን ያካተተ የግዳጅ ምርመራ ሂደት» መፈፀሙን ያጋለጠ ጥራዝ ሲሉ ገልጸውታል።

ሠነዱ ይፋ ከመሆኑ አስቀድሞ በዩናይትድ ስቴትስ የምክር ቤት አባላት ዘንድ ከባድ ጭቅጭቅ አስነስቶ እንደነበረም ታውቋል። ዋሽንግተን ፖስት የተሰኘው ጋዜጣን ጨምሮ አንዳንዶች አሜሪካ ጦርነት ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት ይህን ሠነድ ይፋ ማድረግ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ሲሉ ነቅፎዋል። የሰብአዊ መብት ተሟጋቿ ሎውራ ፒተር ሠነዱ ሕዝብ ዘንድ ሳይደርስ ለማዳፈን በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ እንደነበር ገልጠዋል።

«ሠነዱ ያካተተው መረጃ ይፋ እንዳይሆን ሲ አይ ኤ ከፍተኛ የማከላከል ዘመቻ አኪያሂዷል። ሲ አይ ኤ ላይ ምርመራ ያደረገው ብቸኛው አካል የሲ አይ ኤ የስለላ ሂደትን ሲያጠና የነበረው የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ኮሚቴ ነው። ኮሚቴው ኋይት ሐውስን ጨምሮ በርካታ ተግዳሮቶች ቢገጥሙትም፤ ሠነዱን ይፋ ለማድረግ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም።»

የሲ አይ ኤ ወለል ሲጸዳ

የሲ አይ ኤ ወለል ሲጸዳ

አንዳንድ ሬፓብሊካውያን እና ዴሞክራቶች ሠነዱን ተከትሎ ሲ አይ ኤ ላይ ነቀፌታሰንዝረዋል።በቪየትናም ጦርነት ወቅት የማሰቃየት ምርመራ የተከናወነባቸው እና ለአምስት ዓመት ከመንፈቅ የጦር ምርኮኛ የነበሩት ሬፓብሊካኑ የምክር ቤት አባል ጆን ማክ ኬይን ሳይቀሩ ባልተለመደ መልኩ የሲ አይ ኤን ድርጊት ነቅፈዋል። ሲአይ ኤ የተባለውን ድርጊት የፈጸመው የሬፓብሊካኑ ፓርቲ ሥልጣን ላይ በነበረበት የጆርጅ ቡሽ የአስተዳደር ዘመን ነበር።

ዴሞክራቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በበኩላቸው «መሰል ክስተት መቼም ቢሆን አይደገምም» ሲሉ ትናንት በጽሑፍ ይፋ አድርገዋል። የሲ አይ ድርጊት ዩናይትድ ስቴትስ በዓለም ዘንድ ያላትን ተዓማኒነት በእጅጉ መጉዳቱም ተዘግቧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic