ሲኖዶስ፣ የአርቲስት ፍቃዱ ኅልፈት፣ የዚምባብዌው ፎቶ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 03.08.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ሲኖዶስ፣ የአርቲስት ፍቃዱ ኅልፈት፣ የዚምባብዌው ፎቶ

ከሁለት ዐሥርተ-ዓመታት በላይ የሀገር ቤት እና የውጪው በሚል ተለያይቶ የቆየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሲኖዶስ አንድነት እምነት ሳይለይ በርካቶችን አስደስቷል። በዛው መጠን ደግሞ ኢትዮጵያ እጅግ እንቁ የሆነው የጥበብ ባለሞያዋን ማጣቷ ከጥግ እስከ ጥግ የሐዘን ድባብ አስፍኗል። ሌላ ያልተጠበቀም ነገር ተከስቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:07
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:07 ደቂቃ

አስደሳች፣ አሳዛኝ እና አስደማሚ ክስተቶች በሳምንቱ

ከሁለት ዐሥርተ-ዓመታት በላይ የሀገር ቤት እና የውጪው በሚል ተለያይቶ የቆየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሲኖዶስ አንድነት እምነት ሳይለይ በርካቶችን አስደስቷል። በዛው መጠን ደግሞ ኢትዮጵያ እጅግ እንቁ የሆነው የጥበብ ባለሞያዋን ማጣቷ ከጥግ እስከ ጥግ የሐዘን ድባብ አስፍኗል። ሌላ ያልተጠበቀም ነገር ተከስቷል። ለምርጫ ኃዛቢነት ዚምባብዌ ያቀኑት የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ይመለከታል ጉዳዩ። አቶ ኃይለማርያም መዲናይቱ ሐራሬ ውስጥ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር ቆመው ከተነሷቸው ፎቶግራፎች ፈገግ እንዳሉ የሚታይበት መሰራጨቱ በማኅበራዊ መገናና አውታር ተጠቃሚዎች ዘንድ ድብልቅልቅ ስሜት አጭሯል።

የሲኖዶስ አንድነት

ረቡዕ ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓም በኢትዮጵያውያኖች ዘንድ መቼም የማይረሳ ቀን ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከ26 ዓመታት በኋላ የሀገራቸውን ምድር ዳግም የረገጡበት ቀን።

ይህን አስመልክቶ ሃይደር የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «በቅዱስ መርቆሪዮስ ዕለት አቡነ መርቆሪዮስ ከ26 ዓመት መከፋፈል እና የስደት ኑሮ በኋላ በክብር ወደ አገራቸው ተመለሱ! ዶ/ር አቢይ አህመድ ብዙ ክብር እና ምስጋና! ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!» ሲል ጽፏል።

ቅዱስ ፓትሪያርኩ ረቡዕ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በ19 ሊቃነ ጳጳሳት፤ ካህናት እና የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ታጅበው ብሎም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በአንድነት ነው። ሀገር ቤት ሲመለሱ ታዲያ በቦሌ አየር ማረፊያ እጅግ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ቀኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ላለፉት 26 ዓመታት በሁለት ሲኖዶሶች መከፈሏ ከእንግዲህ ማብቃቱ የተበሰረበት ወቅት ነበር። 

«አስደሳች ዜና»  ሲል ጽሑፉን ያንደረደረው ዮናታን «ላለፉት 27 ዓመታት ለሁለት ተከፎሎ የነበረው ሲኖዶስ አንድ ሆኗል፤ እርቀ ሠላም-ወርዷል! ሁለት የሚባል ነገር ዛሬ አበቃ። አንዲት ቤተክርስቲያን፤ አንድ ሲኖዶስ፤ አንድ ህዝብ!» ብሏል የትዊተር ጽሑፉ ላይ።

በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች የቤተክርስቲያኒቱን የአንድነት ብሥራት ከረዥም ጊዜ አንስቶ ሲጠብቁ እንደነበር ተናግረዋል። አንድነቱን በተመለከተ በእምነቱ ተከታዮች በፌስቡክ ከተሰጡ የእንኳን ደስ ያላችሁ እና የምሥጋና ቃላት ባሻገር ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያንም ስለ ቤተክርስቲያኒቱ አንድነት ደስታቸውን ገልጠዋል።  ከነዚህም መካከል አደም ሾሞሎ ዘሃራ በሚል የፌስቡክ ተጠቃሚ፦«አንድነትን የሚጠላ ሰይጣን ነዉ። ደስ ብሎኛል አንድ ስለሆናቹ የተዋሕዶ ልጆች» የሚል መልእክት ሰፍሯል። ለማ ሽጉጤ በበኩሉ፦«እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ታረቃት!!!እግዚአብሔር ይመስገን!!!» ሲል ደስታውን ገልጧል። «በጣም ደሰ ይላል እንደዚህ ነው የሚያምረው» ያለው ደግሞ ጀማል ሰኢድ አህመድ ነው። ሠሚራ መህዲ፦ «እንኳን ደስ ያላችሁ ክርስቲያን ወገኖቼ በጣም ደስ ይላል፤ ሰላም ያብዛልን» ብላለች።

የሀገር ቤት እና የውጭ በሚል ከሁለት ዐሥርተ-ዓመታት በላይ ለሁለት ተከፍሎ የቆየው ሲኖዶስ አንድ መኾኑን በይፋ ለማብሰር ለቅዳሜ ሚሌኒየም አዳራሽ ቀጠሮ መያዙ በቤተ ክርስቲያኗ አባቶች ተገልጧል። በብሥራት ዝግጅቱ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ 25 ሺህ ግድም ታዳሚያን እንደሚጠበቁም ተያይዞ ተነግሯል።

የአርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ኅልፈት

ማክሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2010 ዓም ማምሻውን ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ በድንገት የተነገረለት አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ከተጫወታቸው ቴአትሮች የተቀነጨበ ነበር። ከቴአትሩ በአጭሩ የተቀነጨበውን ይህንኑ የቪዲዮ ምስል ያያዘው ጋዜጠኛ ፍስሐ ተገኝ፦ «እጅግ አብዝተህ ለሰጠኸን እናመሠግንሀለን ፍቃዱ ተክለማርያም፤ ግዙፍ ነበርክ» ሲል ትዊተር ላይ ጽፏል።

በመድረክ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌሺዥን እንዲሁም በፊልም በርካታ የጥበብ ትሩፋቶቹን ለሕዝብ በማቋደስ ዝናን የተቀዳጀው አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም በድንገት ማረፉ የተነገረው በፌስቡክ ነበር። ዜና ኅልፈቱን ድንገት በፌስቡክ ይፋ ያደረገው «ሀበሻ የአረጋውያን መርጃ ማዕከል» የተሰኘው ገጽ ነበር። ማዕከሉን በመስራችነት እና በላይነት ይመራ የነበረው አርቲስት ፍቃዱ እንደነበር ይነገራል።

«ሀበሻ የአረጋውያን መርጃ ማዕከል» የፌስቡክ ገጽ ማክሰኞ አመሻሹ ላይ ያሰፈረው ዜና ረፍት «ኢትዮጵያ አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያምን አጣች» ሲል ይነበባል። «በኩላሊት ኅመም ሲሰቃይ የነበረው የድርጅታችን ሀበሻ የአረጋውያን መርጃ ማዕከል መስራች አንጋፋው አርቲስታችን በወሎ ሲሪንቃ አርሴማ ፀበል ሲከታተል ቆይቶ ዛሬ አመሻሽ ለይ ከእዚህ አለም በሞት ተለየ።» ጽሑፉ፦ «ነፍስ ይማር አባታችን!» በማለት ይጠናቀቃል።

‏ክብሮም ሳቢያን፦ «ምንጊዜም እናስታውስሀልን አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም፤ በሰላም እረፍ» ሲል ጽፏል። ይርጋለም ደግሞ እዛው ትዊተር ላይ፦ «ነፍስ ይማር ኢትዮጵያ ሌላ ግዙፍ ሰው አጣች! ላደረግኸው በሙሉ እናመሰግንሀልን» ሲል ሐዘኑንም አድናቆቱንም ገልጧል። አብዱ ሞሐመድ በፌስቡክ ጽሑፉ፦ «ይች ወር ስንቱን ሰው ቀማችን» ብሏል በአጭሩ።

ማሩ ግዛቸው እዛው ፌስቡክ ላይ ያሰፈረው አስተያየት እንዲህ ይነበባል። « የሞራል ልእልናው መጨረሻ ደረጃ ላይ የደረሠ እምነቱ ከዉቂያኖስ በታች እንደሚገኝ ከአለት የጠነከረ ጀግና ነው።  ማን ነው ከሞት ጋር ተፋጦ የራሱን ሕይወት አሳልፎ ለሌላ ሰው ሕይወት የሚሰጥ የሠራኸው ትልቅ ሥራ በእግዚአብሔር ዘንድ ትልቅ ዋጋ አለው።»

አማበላይ ዘርአይ በፌስቡክ ከቀብር ስነስርዓቱ በፊት የነበረውን ፎቶግራፍ አያይዞ በእንግሊዝኛ፦ «አርቲስቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት በብሔራዊ ቴአትር ለፍቃዱ ተክለማርያም አሸኛኘት ተደርጎለታል» ሲል ጽፏል።

አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም፦ በበርካታ የጥበብ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ጉልህ አሻራውን አሳርፏል። የሬዲዮ ትረካዎቹ ዛሬም ድረስ በበርካታ አድናቂዎቹ ልብ ታትመው መቅረታቸውን የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ገልጠዋል። ከመድረክ ሥራዎቹ መካከል፦ ቴዎድሮስ፣ ንጉሥ ኦርማህ፣ መቃብር ቆፋሪውና የሬሣ ሳጥን ሻጩ፣ የሰርጉ ዋዜማ፣ አቡጊዳ ቀይሶ፣ ባለካባ ባለዳባ፣ መልዕክተ- ወዛደር ፣ ኦቴሎ፣ ኤዲፐስ ንጉሥ እና ሐምሌት ይጠቀሳሉ።

ሁለቱ የቀድሞ መሪዎች በሐራሬ

ሌላው በሳምንቱ የብዙዎች መነጋገሪያ የነበረው የኢፌዴሪ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በዚምባብዌ ከኮሎኔል መንግሥቱ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸው መገለጡ እና ፎቶግራፍ መታየቱ ነበር። ይህን በተመለከተ ሣሙኤል ቲ ገብረአብ በእንግሊዝኛ የጻፈው የትዊተር መልእክቱ እንዲህ ይነበባል፦ «በአፍሪቃ ፍትኅ እና ተጠያቂነት አለመኖሩ ያሳዝናል። ካለፉት ስህተቶች እና ወንጀሎች ካልተማርን አሁንም አሁንም እኒያኑ ስህተቶች ለመደጋገም ቆርጠናል ማለት ነው።»

አማኔኤል ተስፋዬ ትዊተር ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ፦ «ኢሳያስን ደምሮ መንግስቱን ሲያዩ መበርገግ» ሲል የኢትዮጵያ የቀድሞው ፕሬዚዳንትን ማየት አንፈልግም የሚሉትን በመተቸት ጽፏል፤ ለማንኛውም ነገር መዋዠቅ አስፈላጊ አለመኾኑንም ጠቁሟል።

የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ቡድን አባል አጥናፍ ብርሐኔ፦ «መንግሥቱ ኃይለማርያም ወደ ሀገሩ ሲመለስ ምናልባትም የጀግና አቀባበል ያገኝ ይኾናል፤ ስለዚህ ኋላ ከመደነቃችሁ በፊት ራሳችሁን አዘጋጁ» ሲል ጽፏል። ዐይኑን ጨፍኖ ጥርሶቹ ከጥግ እስከ ጥግ የሚታዩ ምስለ ትዊትም (smiley) አያይዟል።

ያሬድ አሥራት፦«ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሀት) ሞቶ መቀበሩን ላልሰማችሁ ወይም ላላመናችሁ፣ ይኸው ማረጋገጫ!» ሲል የሁለቱ የቀድሞ መሪዎችን ፎቶግራፍ አያይዟል።

ኤርሚያስ በላይ፦«መንግሥቱ በእጆቹ የበርካቶች ደም አለበት፤ እናም ገና ድሮ ነበር መታሰር የነበረበት። ኃይለማርያም ደሳለኝ ከዚህ እኩይ አምባገነን ጋር መገናኘቱ እጅግ ያስደሰተው ይመስላል። በእርግጥስ የቀይ ሽብር ሰማዕታትን ቤተ-መዘክር ጎብኝቷል?» ሲል ጠይቋል።

ጋዜጠኛ ግርማ ሞሐመድ፦ «መንግሥቱ ኃይለማርያም ምንም ያህል ጨካኝ ቢኾን ሊጸጸት አይገባም የሚል አስተሳሰብ የለኝም» ብሏል። ከምንም በፊት ግን ኮሎኔል መንግሥቱ መንግሥታቸው በኢትዮጵያውያን ላይ ትቶት ስላለፈው ሰቀቀንና ኅመም ያለአንዳች ማመንንታት ይቅርታ መጠየቅ እንዳለባቸው ጠቁሟል። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝም ምን ጉዳዮችን አንስተው ከኮሎኔሉ ጋር እንደተወያዩ ኢትዮጵያውያን ሊያውቁ ይገባል ብሏል።

ሞገስ ደሳለኝ፦ «መደመር ደመ-ቀዝቃዛ ነፍሰ-ገዳይ ለሆነው መንግሥቱ ኃይለማርያም ይቅርታ ማድረግ ከሆነ ወጥቼበታለሁ» ሲል ይርጋለም ኃይሌ በበኩሉ፦ «ኢሕአዴግ በገዛ ስርዓቱ ያለውን ጭካኔ እየተመለከትክ፤ ከፋፋይ ፖለቲካውም ሀገራችንን እንዴት ወደ መቀመቅ እንደከተታት እየታዘብክ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ምህረት አይገባቸውም ለማለት የሞራል ልዕልናው የለህም» ብሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ
 

Audios and videos on the topic