ሲሪላንካ የ«ነብሮቹ» ፍፃሜና የሰላም ተስፋ | ዓለም | DW | 25.05.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሲሪላንካ የ«ነብሮቹ» ፍፃሜና የሰላም ተስፋ

በጎ ተስፋ-እያጎነቀለ፥ ሳያሸት ለሚቀጭጭባት፥ጥሩ-ምልክት፥ ቀና አብነት እየበረቀ ለሚጨልምባት ደሴት ግን ሁሉም ሁሌም ነበረ-አለባት

default

ድል አድራጊዉ-ራጃፓክስ

የቀረፋ-ሻይ ቅጠል፣ የሰንደል-ዛፍ ደኗ፣ ሥልታዊነቷ የዘመነ-ዘመናት ሐብት-ኩራትዋ መሠረት-እንደሆኑ ሁሉ፤ የሐይለኞች-ጡንቻ መፈተሻነቷ-የመወረር-መገዛትዋ-ምክንያቶችም ናቸዉ።ባሁን ስሟ ሲሪ ላንካ።ከፈርዕኖች ጀምሮ ሲንሐዎች፣ ሕንዶች፤ ማሌዎች፤ ፖርቱጋሎች፣ ዳቾች፤ እንግሊዞች አሸንፈዉ-እንደ ጨፈሩ-እንዳስጨፈሩባት-ሁሉ፣ተሽንፈዉ-አጥፍተዉ ጠፍተዉባታል።ሰሞኑን ሰንሔላዎችን በድል ደስታ-ስታስቦርቅ፣ታሚሎችን በሽንፈት አሸማቃለች።አለምን-ሥለቀጣይ ጉዞዋ ታነጋግራለች።ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።የድል-ሽንፈቱን ተቃርኖ እያነሳት ሥለ ደቡብ እስያቱ ደሴት ጥቂት እንላለን አብራችሁን ቆዩ።

-----------------------------------------------------------------------------

«ብዙዉ አለም LTTE አይሸነፍም ብለዉ ያምናሉ።ይሁንና መንግሥቴ፥ በጦር ሐይላችን ፅኑ ተጋድሎ፥ ከዚሕ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሰብአዊነት በተመላበት ዘመቻዉ፥ በመጨረሻ-መጨረሻ LTTEን ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን ሥናገር ታላቅ ኩራት ይሰማኛል።»

የሲራላንካ ፕሬዝዳት ማሒንዳ ራጃፓክሰ-ባለፈዉ ሳምንት።ፕሬዝዳንቱ በእሳቸዉና በደጋፊዎቻቸዉ እምነት አኩሪ-ታሪክ ሠሩ።ይሕ ቢቀር የሰላሳ-ዘመኑን የሐገራቸዉን ታሪክ በርግጥ ቀየሩ።ምሕረት የለሹን፥ ደፋሩን፥ አይበገር-አይነኬዉን ጠላታቸዉን አስወገዱ።የታሚሎቹ ነብሮች-ነብር ተገደሉ።አዲዮስ-ቬሉፒላይ ፕራብሐ-ካራን ይል-ይሆናል ታሚል-በታሚልኛ።

የኮሎምቦዉ የሰላምና የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ ጄሐን ፔሬራ እንደሚሉት ደግሞ የፕራብሐ-ካራን መገደል-ታሚሎች የሚኖሩበትን አካባቢ ነፃ ለማዉጣት በነፍጥ የሚዋጋዉ የታሚል ኤላም ነፃ አዉጪ ነብሮች (በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ የLTTE) ም ፍፃሜ ነዉ።

Sri Lanka LTTE Führer Velupillai Prabhakaran Tamilen Tiger

ተሸናፊዉ (ሟቹ)ፕራብሐካራን ከመሐል

«ይሕ (የፕራብሐካራን መገደል) ማለት LTTE ከእንግዲሕ የለም ማለትም ነዉ።ምክንያቱም ፕራብሐካራን የንቅናቄዉ ሕይወት፥ አላማ፥ አነቃቂም ነበሩና።»

በብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች አረመኒያዊ አገዛዝ ልባቸዉ የበገነዉ የታሚል ወጣቶች ለነፃነት የሚያታግላቸዉን የወጣቶች ሊግ ያሉትን ድርጅት በ1930 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሲመሰርቱ ከአራት መቶ አመታት በፊት ሐገራቸዉ ከአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎች እጅ የወደቀችበትን ሰበብ ምክንያት ጠንቀቀዉ ያዉቁት ነበር ማለት ይቻላል።

የሰዉ ልጅ የባሕር ጉዞን ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ-ሥልታዊ አቀማመጧን ለመቆጣጠር፣ የቅመም-አትክልት ደኗን፤ የምድር ማዕድኗን ለመመዝበር በየዘመኑ የተነሱት የዉጪ ሐያላንን ብዙ ጊዜ እየመከተ ከሁለት ሺሕ ዘመን በላይ የፀናዉ የሲንሐ ሥርወ-መንግሥት ከተገረሰሰ ወዲሕ ሕንዶች፤ ማሌዎች፤ አሽካሮች ሲፈራረቁባት ዘመነ-ዘመናት ያስቆጠረችዉ ደሴት የአዉሮጶች ጡንቻ ባበጠበት በአስራ አምስተኛዉ ክፍለ-ዘመን-እሰወስት የተከፈለች ድኩም ሐገር ነበረች።

ግሪኮች ታፕሮባኔ፥ አረቦች ሴራንዲብ (የአለም መገኛ እንደማለት ነዉ) እያሉ ሐብት ዉበትዋን ለአዉሮጳ ያስተዋወቋትን ሐገር ፖርቱጋሎች በ1505 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሲረግጧ የካንዲይ፤ የኮተ፤ የልፓናም ወይም የጃፍና ትናንሽ ሥርወ መንግሥታት ማዕከላዊ፥ ምዕራባዊና ሰሜናዊ ግዛትዋን ለሰወስት ተቃርጠዉ ይገዟት ነበር።

ያቺ ሐገር እሰወስት መከፈሏ መጀመሪያ ለፖርቱጋል፥ ቀጥሎ ለዳች፥ አሰልሶ ለብሪታያ ቅኝ ገዢዎች በቀላሉ እንዳጋለጣት፥ ክፍፍሉ ወይትሮም የየደረሱበትን ሐገር ሕዝብ በዘር-በጎሳ-ለሚከፋፍሉት ቅኝ ገዢዎች ጥሩ መሠረት መሆኑን የ1930ዎቹ ወጣቶች አዉቀዉት ነበር።እኒያ የታሚል ወጣቶች የአያት-አባቶቻቸዉን ሥሕተት፥ የቅኝ ገዢዎቹን የከፋፍለሕ-ግዛ ሻጥርን ለማወቃቸዉ የወጣቶች ሊግ ያሉት ድርጅታቸዉ ሁሉንም ዘር ጎሳ-የሚያሳትፍ፥ ለመላዉ ሐገሪቱ ነፃነት የሚታገል፥ የጋንዲ፥ የኔሒሩን የትግል ሥልት የሚጋራ እንዲሆን ከማድረጋቸዉ በሌላ-ሌላ መረጃ መደርደር አያስፈልግም።

የታሚል ወጣቶች የጠነሰሱት የነፃነት ትግል ለድል በቅቶ በ1948 የያኔዋ ሲሎን ነፃ ስትወጣ ቡደሐዉ፥ ሙስሊሙ፥ ክርስቲያኑ፥ ሲንሐሌ-ታሚሉ፥ ሙርስ፥ካፊሩ፥ ቡርጋርስ፥ ማላዬዉ በነፃነት በእኩልነት የሚኖር፥ የሚሠራባት-የሚሠራላት ሐገር ሆነች ነበር-ተስፋ ምልክቱም።

ሕንዶች-እሁለት ኋላ እሰወስት፥ ኮሪያዎች እሁለት ለመገመስ በሚያጣጥሩበት በዚያ ዘመን፥ ሲሎን ከነፃነት ጋር ከሰወስትነት አንድነትን መምረጧ ለብዙዎቹ የአካባቢዉ ሐገራት ደግሞ ጥሩ አብነት ነበር።ከ1400 አመተ-አለም ጀምራ ቀረፋ-የዝሆን ጥርስ ለፈርኦኖች ትሽጥ የነበረችዉ፥የመጀመሪያዉን ሆስፒታል ለአለም ያስተዋወቅችዉ፥በ47 አመተ-አለም በእስያ ክፍለ-አለም የመጀሪያዋን ሴት ያነገሰችዉ ዉብ ደሴት በእስያ ምድር በርግጥ ሌላ አዲስ ታሪክ ሰራች-አሰኝቶ ነበር።

በ1956-የሲንሐሌዎቹ ቋንቋ የሐገሪቱ ብቸኛ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆን ሲበየን ግን ተስፋ-ምልክቱ፥ አብነት ኩራቱ ሁሉ በርግጥ-በስምንተኛ አመቱ በነነ።

ሲንሔሌዎች የሚመሩት መንግሥት ታሚሎችን ጨምሮ በሐገሪቱ አነሳ-ጎሳዎች ላይ የሚፈፅመዉ ግፍ-በደል ያንገሸገሻቸዉ የታሚል ወጣቶች ለሌላ-ትግል ከመነሳት ባለፍ በርግጥ ሌላ ምርጫ አልነበራቸዉም።ግንቦት አምስት 1976 የያኔዉ የሃያ-ሁለት አመት ወጣት ቬሊፒላይ ፕራባሐካራን የታሚል-ኤላም ነፃ አዉጪ ነብሮች ያሉትን ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ለመመስረትም እንደዘመናቸዉ የአለም ፈሊጥ በቂ ምክንያት፥ አሳማኝ መሠረት የፖለቲካ ተንታኝ ጄሐን ፔሬራ እንደሚሉት ደግሞ ትልቅ አላማ ነበራቸዉ።

«ለአንድ መሠረታዊ አላማ ሲዋጉ የነበሩ ሰዉ ነበሩ።ያ አላማ ደግሞ የታሚል መንግሥት መመሥረት ነዉ።ከዚሕ አላማቸዉ ፍንክች ብለዉ አያዉቁም።»

አላማዉ-ግን እንደ ኦሪት ሕግ የገደለን-ከመግደል ባለፍ የሰላማዊ መንገድን የዘጋ፥ የአንድነትን እሳቤ የደፈለቀ፥ከሁሉም በላይ በ1930ዎቹ መላዉን ሲሎኖዊ ባንድነት፥ ላንድ ሐገር ነፃነት ያንቀሳቀሱትን፥ ለአኩሪ ድል-አብነት ያበቁትን የታሚል ወጣቶችን አስተምሕሮት መቃራኑ ነዉ-ጥፋቱ።ፕራባሐባራን ከተዋጊ ጀልቦች እስከ ትናንሽ አዉሮፕላኖች የታጠቀ ፥ከሐገር አልፎ የሕንድን ጠቅላይ ሚንስትር እስከ መግደል የደረሱ አጥፍቶ-ጠፊዎ-አሸባሪዎችን የሚያዘምት ደፈጣ ተዋጊ በመመሥረት በደፈጣ ተዋጊዎች ታሪክ ለአለም አዲስ ግን ከንቱ-ታሪክ-መመስረታቸዉ ነዉ-የከንቱ ከንቱዉ ክፋት።

Flüchtlinge in Sri Lanka

ተፈናቃዩ

«የሚቃረኗቸዉን ሁሉ ገድለዋል።የሲሪላንካ መሪዎች ይሁኑ ወይም የተለየ አመለካከት ያላቸዉን የታሚል ፓርቲ መሪዎችን ገድለዋቸዋል።»

እንደኖሩበት፥ ሌሎች እንደገደሉ-እንዳስገደሉ ተገደሉ።መገደላቸዉ የፖለቲካ አዋቂ ፔሬራ እንዳሉት የዚያ ሐይለኛ ግዙፍ ልዩ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ፈፃሜ፥ የሐገሪቱ ፕሬዝዳት እንዳሉት ለኮሎምቦ መንግሥት ኩራት፥ የኮሎምቦ አደባባዮችን በዳንስ-ዳንኪራ ላጨናነቁት ለሲንሐሌዎች ብሥራት፥ለአብዛኛዉ ታሚል ሐዘን ወይም ሐፍረት ይሆን-ይሆናል።ያሸነፈን-ስታስጨፍር፥ ተሽናፊን ስታሳፍር፥ ዘመነ-ዘመናት ላስቆጠረችዉ ሐገር ግን በርግጥ አዲስ አይደለም።

በጦርነቱ ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለዉ ሰወስት መቶ ሺሕ የታሚል ሕዝብ እየተረበ፥እየታመመ፥ እየተሞተ-በአደባባይ መፈንደቅ መቦረቁ በዚያች ደሴት ሕዝብ መካካል ያለዉን የጎሳ ልዩነት ስር-እንደሰደደ የአደባባይ ምስክር ነዉ።በሳምንቱ ማብቂያ ሲሪላንካን የጎበኙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን እንዳሉትም የኮሎምቦ መንግሥት ሥር የሰደዉን ክፍፍል ማጥፋት፥የአነሳ ጎሳዎችን መብት ማክበር አለበት።

«ፕሬዝዳት ራጃፓክስ እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ታሚሎችንና ሙስሊሞችን ጨምሮ ከሐገሪቱ አናሳዎች ጋር ሁሉንም ያካተተ ዉይይት ያደርጋል የሚል ተስፋ አለኝ።»

ሰላሳ-ሁለት ሐገራት በአሸባሪነት የፈረጁት ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ከነመሪዉ መደምሰስ የፈነጠቀዉ የሰላም፥ የእኩልነት ተስፋ-እዉን ካልሆነ ግን የዛሬ አሸናፊዎች-እንዳሸነፉ መቀጠላቸዉ በርግጥ አጠራጣሪ ነዉ።በጎ ተስፋ-እያጎነቀለ፥ ሳያሸት ለሚቀጭጭባት፥ጥሩ-ምልክት፥ ቀና አብነት እየበረቀ ለሚጨልምባት ደሴት ግን ሁሉም ሁሌም ነበረ-አለባት። ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

dw,Zpr

ነ ጋሽ መሐመድ፣

ተክሌ የኋላ፣

►◄