ሱዳን ዳግም ሕዝባዊ ተቃዉሞ | አፍሪቃ | DW | 18.10.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ሱዳን ዳግም ሕዝባዊ ተቃዉሞ

ለሱዳኖች ከዋሽግተን፣ ለንደን ብራስልስ አድናቆትና ሙገሳ ሲንቆረቆርላቸዉ ኢትዮጵያ ሶስት ዓመት የተፈራረቀባት የተስፋ-ቀቢፀ ተስፋ ፍትጊያ አድማሱ ሰፍቶ ከርስበርስ የእልቂት ባሕር ዘፍቋት ነበር።የኢትዮጵያ መዳከም  ዳፋዉ ባንድ ወይም በሌላ መንገድ ለጎረቤቶችዋ እንደሚተርፍ ለማወቅ የካርቱም ፖለቲከኞች የተንታኞችን ተጠየቅ መጠበቅ አልነበረባቸዉም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:39

የሱዳን ፖለቲካዊ ቀዉስና አዲስ ተቃዉሞ

 

ኢትዮጵያ ዉስጥ ሚያዚያ 2018 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የፈነጠቀዉ የለዉጥ፣የሠላም፣የዴሞክራሲ፣የፍትሕ ተስፋ ደብዘዝ፣ቀዘዝ፣ፈዘዝ ፈንገጥ ሲል በ2019 አጋማሽ ሱዳን ዉስጥ አዲስ ተስፋ አጎንቁሎ የሠላም፣ነፃነት አብነት አስመስሏት ነበር።የኢትዮጵያ ተስፋ በፖለቲካ ቀዉስ፣ በጎሳ ግጭት፣ግድያ ግራ ቀኝ ሲላጋ አዝግሞ ሐገሪቱን በለየለት ጦርነት ሲያወድማት ሱዳን በተለይ በምዕራባዉያን ዘንድ ከተስፋ ሰጪነት ወደ ጠንካራ ወዳጅነት፣ከሠላም አብነት ወደ ምስራቅ አፍሪቃ ተመራጭ ሐገርነት ከፍ-ላቅ፣ ጠጋ-ደገፍ ስትደረግ ነበር።ሰሞኑን ከፖርት-ሱዳን እስከ ካርቱም የሚደርሱ አካባቢዎችን የሚንጠዉ ተቃዉሞ ግን የሰፊዋ አፍሪቃዊት ሐገር የተስፋ፣ድጋፍ፣ተመራጭነቷ ፍፃሜ እንዳይሆን እያጠያያቀ ነዉ።እኛም ላፍታ እንጠይቅ?

 የቀድሞዉ የሱዳን ፕሬዝደንት ኮሎኔል ጃዓፈር መሐመድ አን ኑሜሪ በ1983 ዩናይትድ ስቴትስን ሲጎበኙ ፕሬዝደንት ሮናልድ ሬገንና ከፍተኛ ሹማምን

ቶቻቸዉ ያደረጉላቸዉ አቀባበል ደማቅ፣ መስተንግዶዉም ሞቅ ያለ ነበር።

የ1970ና 80ዎቹ የአሜሪካ ፖለቲከኞች አምባገነን ገዢዎችን Son of a Bich «የዉሻ ልጅ» እያሉ መጥራት የይቀናቸዋል ይባላል።ይሁንና አምባገነኑ ገዢ የዋሽግተኖችን ፍላጎትና ጥቅም የሚያስከብር ከሆነ ስድቡ «our» (የኛ) የሚል ቅድመ ቅፅል ይለጠፍበትና ይሻሻላል አሉ።Our Son of a Bich ተብሎ።

ኮሎኔል ኑሜሪም ለአሜሪካኖች እንዲያ ሳይሁኑ አልቀረም።የፕሬዝደንት ሬገን መስተዳድር አረብ-አፍሪቃዊዉን  መሪን በልዩ ክብር የተቀበለዉ ግን ኑሜሪ ከነ አንዋር አሳዳት ጋር አብረዉ በዩናይትድ ስቴትስዋ ጥብቅ ወዳጅ እስራኤል ላይ ያወጁትን ጦርነት ስለሰረዙ አልነበረም።

የደቡብ ሱዳኑንን ጦርነት በሰላም ስለፈቱ ወይም በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሥልጣን ስለያዙ አልነበረም።ኑሜሪ ለባለ ቅፅሉ የወዳጅነት «ስድብ» ለልዩ ግብዣ መስተንግዶዉም የተመረጡት ለአሜሪካኖች በአሜሪካኖች በኩል ለምዕራባዉያን በሙሉ ቀንደኛ ጠላት ለነበረችዉ ለሶቭየት ሕብረት ያደረዉን የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን ሶሻሊስታዊ መንግሥት ለማዳከም ሱዳንን እንደ ጥሩ፣ የቅርብ መሳሪያ እንዲጠቀሙባት ኑሜሪ በመተባባራቸዉ እንጂ።

ኑሜሪ በ1985 ለሁለተኛ ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስን ሲገበኙ ሥልጣን ላይ የነበረዉ ከሁለት ዓመት በፊት ሞቅ-ደመቅ አድርጎ የተቀበላቸዉ የፕሬዝደንት ሬገን መስተዳድር ነበር።ይሁንና የሱዳኑ መሪ በሕዝባቸዉ ዘንድ የነበራቸዉ ክብር፣ዝና፣ ድጋፍ ከስሞ፣ሕዝብ እያመፀባቸዉ ስለነበረ ዋሽግተኖች ለቀድሞ ወዳጃቸዉ የቀድሞዉ ዓይነት አቀባባል ቀርቶ፣ ለማነጋገር ሰፊ ጊዜ እንኳን አልሰጧቸዉም።ኑሜሪ የጠየቁትን የገንዘብ ርዳትም አልሰጧቸዉም።

የኑሜሪ አገዛዝ ያስመረረዉ የሱዳን ሕዝብ «ያቀርቶ ሌላ----» ዓይነትን በሚዚያምበት በዚያ ዘመን አሜሪካኖች «ትዝአለኝ የጥንቱ»ን የሚያንጎራጉሩበት» ምክንያት አልነበረም።ኑሜሪም ከዋሽግተን ሳይወጡ መከላከያ ሚንስትራቸዉ ጄኔራል አብደል ራሕማን ስዋር አል-ሐብ በመሩት መፈንቅለ መንግስት ስልጣኑን ይዘዉ የቀድሞ አለቃቸዉን ለስደት ዳረጓቸዉ።መአሰላማ-እንዲል ሱዳን።

ኑሜሪ ሥልጣን የያዙትም፣ ከስልጣን የተወገዱትም፣ በኑሮ ዉድነት በተለይም በምግብ ዋጋ ንረት ሰበብ በተቀጣጠለ  ተከታታይ ሕዝባዊ አመፅ ግፊት ነበር።

ኢትዮጵያዉያን በጣሙን ወጣቱ ባደረገዉ የአደባባይ ተቃዉሞ የ27 ዓመታት ገዢዎቹን አስወግዶ ባዲስ መሪዎቹ የቃል ተስፋ በሚበሻበሽበት በ2018ቱ ታሕሳስ ካርቱም ላይ ብልጭ-ድርግም ማለት የጀመረቺዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞም ሰበቧ የምግብ ዋጋ ንረት ነበር።

የካርቱሟ ተቃዉሞ ባጭር ጊዜ ዉስጥ ተቀጣጥላ የፕሬዝደንት ዑመር ሐሰን አልበሽርን የ30 ዘመን  አገዛዝ ካስወገደች በኋላ በተደረገ ተከታታይ ድርድርና ዉይይት የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን የያዙት ዶክተር አብደላ ሐምዶክ አመፁ የተጫረበት አንደኛ ዓመት ሲዘከር ዋሽግተን ዲሲ ነበሩ።ታሕሳስ 2019።

ኑሜሪ በ1985 ካደረጉት ወዲሕ አንድ የሱዳን መሪ ዩናይትድ ስቴትስን በይፋ ሲገበኝ ሐምዶክ የመጀመሪያዉ መሪ ሆኑ።ከደማቅ አቀባባል፣የድጋፍ ቃል ተስፋዉ ጋር አንላንቲክ ምክር ቤት በተባለዉ ተቋም በተደረገላቸዉ ግብዣ ላይም የለዉጡን ታላቅነት አወደሱ።

«አምና በዚሕ ወር ታሕሳስ፣እኛ ሱዳናዉያን በኩራት አብዮት የምንለዉ፣ በኩራት በቅርብ ታሪክ ከተከናወኑ ትላላቅ የዓለም እዉነቶች እንደ አንዱ የምንቆጥረዉ አብዮት ተጀመረ።ይሕንን እዉነት የዓለምን ገፅታ ከቀየረዉና የሊቢራል ዴሞክራሲን ካጎናፀፈዉ ከታላቁ የፈረንሳይ አብዮት ጋር ብናመሳስለዉ ተገቢ እንደሆነ ይሰማናል።

በርግጥም ሕዝባዊዉ አመፅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን፣ ሴቶችን፣የመንግስት ሠራተኞችና ባለሙያዎችን ያሳተፈ፣ ለተከታታይ ወራት የተደረገ ብዙ ሕይወት፣አካል፣ ክብርንም ያስገበረ ታላቅ ንቅናቄ ነበር።ለሱዳኖች አኩሪ፣ ለሌሎች አረብ-አፍሪቃዉያን አብነት።

ሕዝባዊዉ አመፅ የጄኔራልነት ማዕረጋቸዉን በሱፍ-ከራቫት ወይም በጀለቢያ የቀየሩ ገዢዎችን በአዳዲስ ጄኔራሎች መቀየሩ ያስከተለዉ አዲስ አመፅና ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲወገድ የአፍሪቃ ሕብረት ጥረት፣ የኢትዮጵያ ሽምግልና ያበረከቱት አተዋፅኦ ቀላል አልነበረም።

ከብዙ ድርድርና ዉይይት በኋላ የሱዳንን የመሪነት ስልጣን የያዙት የጦር ይባሉ የሲቢል ሹማምንት ከአዲስ አበባ ይልቅ ዋሽግተንን፣ ከኢትዮጵያ ይበልጥ ግብፅን ይባስ ብለዉ ለረጅም ጊዜ «ጠላት» የሚሏትን እስራኤልን ነበር የመረጡት።

ከክፉ ቀን ወዳጆቻቸዉ ምናልባትም ከሕዝባቸዉም ፍላጎት ካስቀደሟቸዉ ኃያላን  ሙገሰ፣አድናቆት፣ ድጋፉ ይንቆረቆርላቸዉም ገባ።ቀዳሚዉ ያዉ መቅደም ያለባቸዉ ናቸዉ።

 «የሱዳን ሪፐብሊክና የእስራኤል መንግስት ሠላም ለማዉረድ ተስማምተዋል።ሁለቱ ሐገራት ለረጅም ዓመታት እንዲያዉ ለዘብ ለማድረግ የተቃቃሩ ነበሩ።ግንኙነታቸዉን ለማሻሻል ተስማሙ።በቅርቡ ታሪክ ትልቅ ስምምነት ነዉ።የሱዳን ሕዝብ በጨካኝ እስላማዊ አምባገነን ሲገዛ ነበር።ሱዳን የኦሳማ ቢን ላደን መኖሪያ ነበረች።የሽብር፣ የዘር ማጥፋትና የሌሎች ድቀት ሥፍራ ነበረች።ዛሬ ታላቁ የሱዳን ሕዝብ ሐገሩን ተቆጣጥሯል።አዲስ ዴሞክራሲ መሰረት እየጣለ ነዉ።አሁን የጠቀስኳቸዉ ሁለቱ ሰዎች በጣም የተከበሩ፣ በጣም፣በጣም የተከበሩ መሪዎች ናቸዉ።»

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራም።አምና ጥቅምት።

ለሱዳኖች ከዋሽግተን፣ ለንደን፣ በርሊንና ብራስልስ ድጋፍ፣አድናቆትና ሙገሳ ሲንቆረቆርላቸዉ ኢትዮጵያ ሶስት ዓመት የተፈራረቀባት የተስፋ-ቀቢፀ ተስፋ የተቃርኖ ፍትጊያ አድማሱ ሰፍቶ ከርስበርስ የእልቂት ባሕር ዘፍቋት ነበር።የኢትዮጵያ መዳከም  ዳፋዉ ባንድ ወይም በሌላ መንገድ ለጎረቤቶችዋ እንደሚተርፍ

ለማወቅ የካርቱም ፖለቲከኞች የተንታኞችን ተጠየቅ መጠበቅ አልነበረባቸዉም።

የኢትዮጵያን በጣሙን ከራሷ ከሱዳን የሚያዋስነዉ የኢትዮጵያ ግዛትን የሚያወድመዉን ጦርነት ለማስቆም መሸምገል፣ማማለዱ ቢቀር እንደሩቅ ታዛቢ መመልከቱ በርግጥ ምርጫ ላጣ የብልሆች እርምጃ ባሰኘ ነበር።ካርቱሞች የወለፊንዱን ማድረግ-መሞከራቸዉ ነዉ አስተዛዛቢዉ ሐቀ።

የኢትዮጵያ ስደተኞችን ለማስተናገዳቸዉ በጎ ምልክት ተመስግነዉ ሳያበቁ ከኢትዮጵያ ጋር የሚወዛገቡበትን የድንበር ግዛት በኃል ያዙ።ከግብፅ ጋር አብረዉ የኢትዮጵያን የግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ከግብፅ ጋር አብረዉ ዓለምን ያስተባብሩ፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፊት ይሟገቱም ገቡ።

የምዕራቡ ኃያል ዓለምም የካርቱሞችን «እንጣጥ እንጣጥ» እንደ ዘላቂ አቅም ቆጥሮ የፖለቲካ-ዲፕሎማሲ፣ የገንዘብ ድጋፉን ከአቅማቸዉ በላይ ይግታቸዉ ያዘ።ፕሬዝደንት ትራምፕ አዳዲሶቹን የካርቱም መሪዎችን ባደነቁ፣በሰባተኛ ወሩ ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐንና ዶክተር አብደላ ሐምዶክ ፓሪስ ነበሩ።ፈረንሳይ ሱዳን ላይ የነበራትን 5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ሰረዘች።ሱዳን ለዓለም ባንክ መክፍል የነበረባትን ዕዳ እንድትከፍል ደግሞ ፈረንሳይ «ድልድይ» ያለችዉን 1.5 ቢሊዮን ዶላር አዲስ ብድር ሰጠች።የፈረንሳይን ድጋፍ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ ሐላፊነትን እንደመወጣት ነዉ-የቆጠሩት።

 ብዙ ሳይቆይ «የፓሪስ ክለብ» የተባለዉ የአበዳሪ ሐገራት ስብስብ የሚያስተናብራቸዉ ሐገራት ሱዳን ላይ ከነበራቸዉ ዕዳ 14 ቢሊዮን ዶላሩን ሰረዙ።የተቀረዉ ዕዳ የሚከፈልበትን ጊዜ ለማሸጋሸግና ወለዱን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ለመሰረዝ ወስነዋልም።

የምዕራብ ኃያላንና የዓረብ ሐብታሞች ለሱዳን ያደረጉና የሚያደርጉላትን ድጋፍ መንግስታቸዉ ለስራ አጡ ወጣት ሥራ ለመፍጠር እንደሚያዉለዉ የምጣኔ ሐብቱ ሊቅ አብደላ ሐምዶክ ቃል ገብተዉ ነበር።

«ይሕን የመጨረሻዉን እንቅፋት ማስወገዳችን ሱዳን ከዓለም አቀፉ የልማት ማሕበረሰብ መቀየጧን ያበስራል።ይሕን እድል በመጠቀም ከሁለት ዓመት ግድም በፊት አደባባይ ለተሰለፉ ሴትና ወንድ  ወጣቶቻች ጥያቄ መልስ የሚሰጥ የሥራ አድል ለመፍጠር እንጠቀምበታል።»

ግንቦት።ሰኔ በተስፋ አለፈ።ኃምሌ፣ነሐሴም።መስከረም ሲጠባ የቡርሐን-ሐምዶክ አመራር ያማራራቸዉ ወታደሮች መፈንቅለ መንግስት ሞከሩ።ከሸፈ።በዚያዉ መስከረም በሽግር መንግስቱ አልተካተትንም ያሉ የምሥራቅ ሱዳን የጎሳና የፖለቲካ መሪዎች የጠሩት ተቃዉሞ ሰልፈኛ የሱዳንን ወደቦች ዘጋ።ባለፈዉ ቅዳሜ ደግሞ ካርቱም ባዲስ የተቃዉሞ ሰልፍኛ ተጥለቀለች።

 የሰልፋኞቹ ፖለቲካዊ ዓላማና ፍላጎት ለየቅል ነዉ።አንድ ያደረጋቸዉ ግን አንድ ጉዳይ ነዉ።የኑሮ ዉድነት።ከሰልፈኞቹ አንዱ እንዲሕ ይላል።

«የሱዳን ሕዝብ በአብዮቱ ወቅት አደባባይ የወጣዉ ሕልሙ እዉን እንዲሆን ለመጠየቅ ነበር።እስካሁን ግን  የሱዳን ሕዝብ የሚኖረዉ በዉድመትና ትቢያ መሐል ነዉ።ዛሬ አንድ ኪሎ ሱካር 550 የሱዳን ፓዉድ

ነዉ።ዳቦ 100 ፓዉንድ ነዉ።እሱንም ለማግኘት ሕዝቡ ረጃጃም ሰልፎችን መጠበቅ አለበት።ዉጪ ስትወወጣ የደሕንነት ዋስትና የለሕም።እቤት ዉስጥ እንኳን ሆነሕ ምንም ደሕንነት አይሰማሕም።»

አብዛኛዉ ሰልፈኛ ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል  ቡርሐን ሰልፈኛዉ «የረሐብ መንግሥት» ያለዉን የጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክን መንግስት በኃይል እንዲያስወግዱ እየጠየቀ ነዉ።ቅዳሜ የተጀመረዉ ሠልፍ ከትንንት ጀምሮ ባደባባይ የቁጭታ አድማ ተለዉጧል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክና ደጋፊዎቻቸዉ ጦር ኃይሉን የሚደግፈዉን ሰልፈኛ የሚቃወም ሌላ ሰልፈኛ አደባባይ እንዲወጣ ከመጥራት ሌላ ለጊዜዉ ያቀረቡት አማራጭ የለም።ካለም በጦር ኃይሉና በሲቢል ፖለቲከኞች መካከል ያለዉ ልዩነት መካረሩን ማመን ነዉ።

«የዚሕ ቀዉስ ዋና መሠረቱ በአብዮታዉያንና በለዉጡ ኃይላት መካከል በጋራ ብሔራዊ መርሕ ላይ ለመግባባት አለመቻላቸዉ ነዉ።»

አዲሱ  ተቃዉሞ የካርቱም ፖለቲከኞች ለሕዝባቸዉ የገቡትን ቃል ገቢር ያለማድረጋቸዉ ነፀብራቅ መሆኑ አላጠራጠረም።ጦር ኃይሉንና የሲቢል ፖለቲከኞችን ለማግባባት ከካይሮ እስከ ሪያድ፣ ከፓሪስ እስከ ዋሽግተን ያሉት የቡርሐን-ሐምዶክ የቅርብ ወዳጆች እስካሁን ያደረጉት ካለ አልተሰማም። ካርቱሞች ዳግም አምባሳደር ማሕሙድ ዲሪርን እየጠበቁ ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ 

ታምራት ዲንሳ 

Audios and videos on the topic