ሱዳን ያልተጠናቀቀዉ አብዮት | አፍሪቃ | DW | 27.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ሱዳን ያልተጠናቀቀዉ አብዮት

ገመድ ጉተታዉ፣ዑመር ሐሰን አልበሽር ባለፈዉ ሚያዚያ 11 ከስልጣን  ሲወገዱ የሐገሪቱን ሕዝብ ባደባባይ ያስደሰተ፣ያስፈነደቀ፣ያስጨፈረዉን የዴሞክራሲ፣የፍትሕ ብልፅግና ተስፋን ባያጨናጎል አመንምኖታል።አልበሽርን የተኩት የጦር ጄኔራሎች እንደ ቀዳሚዎቻቸዉ በሕዝብ አመፅ የተገፈተሩትን የቀድሞ አለቃቸዉን ከነታማኞቻቸዉ ወሕኒ መዶሉ በርግጥ አልገደዳቸዉም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:08

ሱዳን በጥልጥል ያለዉ አብዮት

ጄኔራሎቹ እንደ ጦር አዛዥ በለዉ፣እሰረዉ ማለት አንድም ስላልፈጉ ሁለትም ስላልቻሉ፣ እንደ ማስፈራራትም፣ እንደ ዲፕሎማት እንደመደራደርም እያሉ ትናንትን በዛሬ፣ዛሬን በነገ እየተኩ ጊዜ በጊዜ እስኪሻር ያደባሉ።የሱዳን ሕዝብ የጄኔራሎቹ ማስፈራሪያ ግልምጫ፣ የድርድር-ዉይይት ማሳሰቢያ፣ የረመዳን ፈርድም ሳያግደዉ የካርቱም አደባባዮችን ሙጥኝ እንዳለ ነዉ።ነባር ፖለቲከኞች፣ ኃይማኖተኞች፣ ሕዝብን ለተቃዉሞ ያደረጁ አቀንቃኞች  እስካሁን የፀና አንድነታቸዉ በሳምንቱ ማብቂያ ስስም ቢሆን ነፋስ ሽዉ ያለበት መስሏላ።የሪያድ፣ አቡዳቢ፣ የካይሮ ገዢዎች የሱዳን ጉዳይ የሱዳኖች እንዳይሆን እየባተሉ ነዉ።የሱዳን ሕዝባዊ አብዮት እንደ ቱኒዚያ የዴሞክራሲ ብስራት-ምልክት ወይስ እንደ ግብፅ የዴሞክራሲ ቅጭት አብነት?

የሱዳን ወታደራዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄኔራል አብድል ፈታሕ ቡርሐን በመፈንቅለ መንግስት ቤተ-መንግሥትን ተቆጣጥሮ በሕዝባዊ አመፅ ወሕኒ  ቤት መወርወርን ለማወቅ ሽቅብ ወደ ቱኒዝ፣ ወደ ካይሮ ወይም አግድም ወደ ኢንጃሚና  መመልከት አያስፈልጋቸዉም።እዚያዉ ካርቱም በ1964 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) በጄኔራል ኢብራሒም አብቦድ፣ በ1985 በጄኔራል ጅዓፈር አል ኑሜሪ የደረሰዉ ቢርቃቸዉ የዘንድሮዉ የጄኔራል ዑመር ሐሰን አልበሽር ፍፃሜ፣ ፍፃሜያቸዉ እንደሚሆን ጠንቅቀዉ ያዉቁታል።

የሱዳን ሕዝብ የጄኔራል ዑመር አልበሽርን አገዛዝ ለመቃወም የካርቱም አደባባዮችን ላይ ሰብሰብ-በተን ማለት ሲጀምር አንዳዶች በ2011 ቱኒዚያ የተጀመረዉ የአረብ ሕዝባዊ አመፅ ነፀብራቅ ወይም ተቀፅላ አድርገዉት ነበር።ሱዳኖች ግን በሕዝባዊ አመፅ አምባገነን ገዢን ለማስወገድ ሌሎችን አስተማሪ እንጂ ከሌሎች ተማሪ አይደለንም ባዮች ናቸዉ።አላበሉም።

የሱዳን ሕዝብ በ1964 የጄኔራል ኢብራሒም፣ በ1985 የጄኔራል ኑሜሪን አገዛዞች ባደባባይ ሰልፍ እያሽቀነጠረ ሲጥል ቱኒዝ፣ካይሮዎች ወደ ካርቱም ተመልካቾች ነበሩ።ሱዳኖች ጄኔራል ሆነ ፖለቲከኛ፣ ወታደር ሆነ፣ ሰልፈኛ ከጎረቤቶቻቸዉ ይልቅ ካያት፤ አባት ቀዳሚዎቻቸዉ በቅርብ ምናልባትም እኩል በሚያዉቁት ስልት አልበሽርን ባስወገዱ ማግሥት አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለመጣል ጄኔራሎቹ እንደ አዲስ ገዢ ሲቢሎቹ እንደ ተቃዋሚ መፋጠጣቸዉ ክፋቱ።የፖለቲካ ተንታኝ የሱፍ ያሲን ገመድ ጉተታ ይሉታል።

ገመድ ጉተታዉ፣ዑመር ሐሰን አልበሽር ባለፈዉ ሚያዚያ 11 ከስልጣን ሲወገዱ የሐገሪቱን ሕዝብ ባደባባይ ያስደሰተ፣ያስፈነደቀ፣ ያስጨፈረዉን የዴሞክራሲ፣የፍትሕ ብልፅግና ተስፋን ባያጨናጎል አመንምኖታል። አልበሽርን የተኩት የጦር ጄኔራሎች እንደ ቀዳሚዎቻቸዉ ሁሉ በሕዝብ አመፅ የተገፈተሩትን የቀድሞ አለቃቸዉን ከነታማኞቻቸዉ ወሕኒ መዶሉ በርግጥ አልገደዳቸዉም።

የካርቱም አደባባዮችን በተለይም የጦር ዕዞቻቸዉን አካባቢ ሙጥኝ ያለዉን ሕዝብ ግን አልፎ አልፎ ከመጎሸም ባለፍ ከአቡድ እስከ አልበሽር እንደነበሩ ቀዳሚዎቻቸዉ በኃል ሊደፈልቁት ቢያንስ እስካሁን አልቻሉም ወይም አልፈለጉም።

ጄኔራሎቹ በጊዚያዊነት የያዙትን ሥልጣን እንደያዙ ለመቀጠል እንደ ብልሐት የያዙት እሶስ የሚከፈል ግን ለአንድ ግብ ያለመ ስልት ነዉ።እነሱ ሥልጣን ከለቀቁ ሐገሪቱ ትተራመሳለች እያሉ ማስፈራራትን-አንድ፣ ከተቃዋሞዉ አስተባባሪዎቹ ጋር መደራደር-ሁለት፣ የዉጪ በተለይም የአረብና የአፍሪቃ መንግስታትን ድጋፍ መማፀን-ሶስት።

ታዛቢዎች እንደሚሉት ሶስቱ ተዳምረዉ ጊዜዉ በጊዜ ሲተካ አደባባይን ሙጥኝ ያለዉ ሕዝብ እየተሰላቸ፣አስተባባሪዎቹ እየተከፋፈሉ፣ የዉጪዉ ግፊት ወደ ድጋፍ እየተለወጠ ሲመጣ፣ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ ቡርሐን፣ ወይም ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሐምደቲ) አልበሽርን-የተኩ አልበሽሮች ሆነዉ ቁጭ ማለት ነዉ ግቡ።

የሽግግር መንግስቱን የሚመራዉን ኃይል ማንነት፣ዘመነ-ሥልጣኑንና ኃላፊነቱን ለመወሰን የሚደረገዉ ድርድር በየሰበብ አስባቡ ደንበር ገተር እንዳለ ነዉ።ወታደራዊዉ ምክር ቤት ሐገሪቱን ለሲቢላዊ አስተዳደር እንዲያስረከብ የሚቀርብለትን ጥያቄ «ፀጥታ ይታወካል» በሚል ማማኻኛ በተደጋጋሚ ዉድቅ አድርጎታል።የተቃዋሚዉ መሪዎች ደግሞ ጦር ሐይሉ ፀጥታ ከማስከበር ባለፍ ባስተዳደር ጉዳይ መግባት የለበትም ባዮች ናቸዉ።ባለፈዉ ሳምንት ድርድሩ ጨርሶ ቆሟል።የድርድሩ መቋረጥ፣ ወታደራዊዉ ምክር ቤት  ድርድሩን «ለጊዜ መግዢያ» እየተጠቀመበት ነዉ የሚለዉን አስተያየት አጠናክሮታል።የፖለቲካ ተንታኝ የሱፍ ያሲን ግን የጊዜዉ መራዘም ለጄኔራሎቹ ብዙም አይጠቅምም ባይ ናቸዉ።

ተቃዉሞዉን የሚያስተባብሩ ወገኖች የመሠረቱት የነፃነትና የለዉጥ ኃይላት የተሰኘዉ ስብስብ በበኩሉ የወታደራዊ ምክር ቤቱን «ጊዜ የመግዛት» ሥልት ለመስበር ነገና ከነገ ወዲያ የስራ ማቆም አድማ ጠርቷል።ቃል አባይ ጀዓፈር ዑስማን እንደሚሉት የሱዳን ሕዝብ ድምፅ መሰማት አለበት።

«የሕዝቡን ድምፅ ለማሰማት አሁን ባለንበት ደረጃ የመረጥነዉ የሁለት ቀን የስራ ማቆም አድማ የማድረጉን ዴሞክራሲያዊ መብትን ነዉ።ሥለዚሕ በዚሕ አድማ መላዉ ሱዳናዊ ሲካፈል፣የነፃነትና የለዉጥ ኃይላት ሰፊ ድጋፍ እንዳለዉ ለወታደራዊዉ ምክር ቤት  ጠንካራ መልዕክት ያስተላልፋል።አድማዉ አደባባይ ያልጣዉንም ሕዝብ ስለሚያካትት፣ የመላዉ ሱዳንን ሕዝብ ድምፅ ለወታደራዊ ምክር ቤት ማስተላለፍ ይችላል።»

የነፃነትና የለዉጥ ኃይልን ከመሠረቱት ነባር ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ዑማ የተሰኘዉ የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትር የሳዲቅ አል-መሕዲ ፓርቲና የሱዳን አንድነት የተባለዉ ፓርቲ የሥልራ ማቆም አድማዉን አልደገፉትም።ሁለቱ ፓርቲዎች በየፊናቸዉ እንዳስታወቁት ወታደራዊዉ ምክር ቤት አልደራደርም እስካለለ ድረስ የስራ ማቆም አድማ መደረግ የለበትም።ይሁንና በተለይ ዑማ ፓርቲ እንዳስታወቀዉ በስራ ማቆም አድማ የሚካፈሉ ሠራተኞች ከሥራ የመታገድም ሆነ ሌላ ቅጣት ሊደርስባቸዉ አይገባም።እስካሁን ባንድነት ፀንተዉ የቆዩት የተቃዋሚዎቹ ኃይላት በስራ-ማቆም አድማዉ ላይ ያሳዩትን ልዩነት አንዳዶች የመከፋፈላቸዉ መጀመሪያ፣ ሌሎች ደግሞ ያንድነታቸዉ የመጨረሻ መጀመሪያ ብለዉታል።

በሳምንቱ ማብቂያ የካርቱምን አደባባይ ያጥለቀለቁት የእስልምና ኃይማኖት ተከራካሪዎች ደግሞ የሺርዓ ሕግ እንዳይሻር አደራ ብለዋል።ለሸርዓ ሕግ መከበር የሚሟገቱ ወገኖች እንደ ሌሎቹ ተቃዋሚዎች ሁሉ አጠቃላይ ጥያቄዎችን ከማንሳት በስተቀር ኃይማኖታዊ ጉዳይን አንስተዉ ለብቻቸዉ አደባባይ ወጥተዉ አያዉቁም።

ከልፈኞቹ ተወካዮች አንዱ መሐመድ ዓሊ ጃዙሊ እንደሚሉት ከ1983 ጀምሮ የፀናዉ የሸሪዓ ሕግ መሻር የለበትም።በተለይ ኮሚንስቶች ብቻቸዉን ሥልጣን ሊይዙ አይገባም።«ወታደራዊዉ ምክር ቤት ከሁሉም የሱዳን ወገኖች ጋር በእኩል ርቀት ላይ መቆም አለበት እንላለን።ሁሉም ወገን መካተት አለበት።ይሁንና እስላማዊዉን አምባገነን ያስወገድነዉ በግራ አምባገን ለመተካት አይደለም።»

ስድስት ወር የበለጠዉን የተቃዉሞ ሰልፍ የሚያስተባበሩና የመሩት ወገኖች በሥራ-ማቆም አድማዉ አለመግባባታቸዉና የሸሪዓ ሕግን ትልቅ ጥያቄ ያደረጉ ወገኖች አደባባይ መዉጣታቸዉ በለዉጥ ፈላጊዉ ኃይል መካከል ልዩነት መኖሩን ጠቋሚ ባዮች አሉ።ልዩነቱ የወታደራዊዉ ምክር ቤት መሪዎች የሚፈልጉት ምናልባትም የለዉጡን ተስፋ ጨርሶ የሚያዳፍን ሊሆንም ይችላል።

ተቃዉሞ ሰልፈኛዉ ግን ዛሬም የሱዳን ሕዝብ ጥያቄ አንድ ነዉ ባይ ነዉ። «መላዉ የሱዳን ሕዝብ ከጦር ኃይሉ ጠቅላይ እዝ ፊትለፊት በሚደረገዉ የቁጭታ አድማ እየተሳተፈ ነዉ።ሁሉም የሚጠይቀዉ ሲቢላዊ አስተዳደር እንዲመሠረት ነዉ።ሙሉ በሙሉ ሲቢላዊ የሆነ አስተዳደር።»

ሰልፈኛዉ እንዳሉት የሱዳን ሕዝብ ባንድነት ቆመም ተለያየ የሕዝቡ ጥያቄ ሕዝባዊ ተመራጭን ቤተ-መንግስት ሳይዶል ለመደፍለቅ ጄኔራሎቹ አጥብቀዉ እየጣሩ ነዉ።የግብፅን፣ የሊቢያን፣የሶሪያና የየመንን ሕዝብን የነፃነት፣የዴሞክራሲና የፍትሕ ጥያቄን በንጭጩ የደፈለቁት የካይሮ፣የሪያድና የአቡዳቢ ገዢዎችን ለጄኔራሎቹ ቀጥታ ድጋፍ እየሰጡ ነዉ።

የወታደራዊዉ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄኔራል አብዱል ፈታሕ ቡርሐን በመፈንቅለ መንግሥት ማግሥት የጄኔራልነት መለዮቸዉን በኮት ካራቫት ከቀየሩት ከግብፁ መሪ ከአብዱል ፈታሕ አልሲሲ ምናልባት ምክር፣ ከአልጋወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ዘይድ ቼክ ለመቀበል በሳምንቱ ማብቂያ ካይሮና አቡዳቢ ነበሩ።ምክትላቸዉ መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ደግሞ አልጋወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማንን ለማነጋገር ሪያድ ነበሩ።

ጄኔራሎቹ ከሪያድና ከአቡዳቢ «በሚቆረጥላቸዉ ዶላር»፤ ተማርከዉ እንደ አል-ሲሲ ተቃዋሚዎቻቸዉን ባደባባይ «መጭፈጭፍ» ከጀመሩ የሱዳን ብቻ ሳይሆን የአካባቢዉ ሰላምም መታወኩ አይቀርም።ኢትዮጵያና ኤርትራ በየፊናቸዉ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮቻቸዉን ወደ ካርቱም ከመላካቸዉ በስተቀር ካርቱም የ2013ና 14ቷን ካይሮን ብትሆን የአካባቢዉን ሠላም ለማስከበር ያደረጉት ዝግጅት ወይም የያዙት አቋም ግልፅ አይደለም።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic