ሱዳን የዳርፉር ቀውስና የአማፃያኑ ጥያቄ | የጋዜጦች አምድ | DW | 20.10.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ሱዳን የዳርፉር ቀውስና የአማፃያኑ ጥያቄ

በዳርፉር የስደተኞች መንደር

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ሀይል ዳርፉር እንዲሰፍር የፀጥታው ምክርቤት ያሳለፈውን ውሳኔ እንደማትቀበል በገለፀችበት አቋሟ አሁንም የፀናች መሆኗን ሱዳን አስታወቀች ። ስለዚሁ ጉዳይ ከዋሽንግተን መንግስት ከፍተኛ ልዑክ ጋር ካርቱም ውስጥ የተነጋገሩት የሱዳኑ መሪ ኦማር አልበሽር አማካሪ ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት ሱዳን በዚህ ጉዳይ ላይ አቋምን አልቀየረችም ። የግንቦቱን የዳርፉር ስምምነት የሚቃወሙትና ግዛቲቱ ነፃ እንድትወጣ የሚፈልጉት የዓማፅያን ቡድኖች ደግሞ ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ነን ይላሉ ። የረድኤት ሰራተኞችና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች በበኩላቸው የአውሮፓ ህብረት በሱዳን መንግስት ላይ ጠንካራ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል ። ሱዳን የፀጥታው ምክርቤት ያሳለፈውን ውሳኔ እንድትቀበል ለማግባባት ካርቱም ለሄዱት የዩናይትድስቴትሱ ልዑክ አንድሪው ናትስዮስ ከዚህ ቀደም በይፋ የሰጠችውን መልስ ነው የደገመችው ። የምክርቤቱን ውሳኔም አልቀበልም ስትል ። የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ከፍተኛ አማካሪ ግሀዚ ሳላዲን ከዩናይትድ ስቴትሱ ልዑክ ጋር ከተነጋገሩ በኃላ ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት የመንግስታቸው ፍላጎት የዳርፉሩ የሰላም ስምምነት በአፍሪቃ ህብረት ሀይል ተፈፃሚ እንዲሆን ነው ። ይህ የሱዳን መንግስት አቋምም አልተቀየረም ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አሰከባሪ ሀይል ዳርፉር መስፈሩን የምትቃወመው ሱዳን ይልቁንም በችግር የተተበተበው ዳርፉር የሚገኘው የአፍሪቃ ህብረት ሀይል የሚረዳበትን መንገድ በሚመለከት ከመንግስታቱ ድርጅት ጋር መወያየት ትሻለች ። በዳርፉር ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን የተሰማራው ሰባት ሺህ የአፍሪቃ ሰላም አስከባሪ ሀይል በቂ ትጥቅ የለውም ። የገንዘብ ድጋፉም ዝቅተኛ ነው ። ይኽው ችግር የአደባባይ ሚስጥር ቢሆንም የአፍሪቃ ህብረት ሀይል አዛዥ ጀነራል ኮሊንስ ኢሄኪሬ እንደተናገሩት ዓለምዓቀፉ ማህበረሰብ ዳርፉርን የወሬ ማጣፈጫ ከማድረግ ውጭ የህብረቱን ሀይል ለመርዳት ምንም አልፈየደም ።
ድምፅ
“ባለፉት ሰባት ወራት ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የሚያስፈልገንን እንዲያውቅ አድርገናል ። ሆኖም በአሳዛኝ መልኩ ዳርፉር ለነርሱ የወሬ ማሳመሪያ ነው የሆነችው ። እኛ እናወራለን ህዝቡ ያልቃል “ ከግንቦቱ የሰላም ስምምነት ወዲህ የዳርፉር ፀጥታ ከድጡ ወደማጡ ተሸጋግሯል ። ገንዘብ ያጠረው የአፍሪቃ ህብረት ሀይል በአካባቢው እየተባባሰ የሄደውን ግጭት የማብረድ አቅሙ ደክሟል ። የረድኤት ሰራተኞች እንደሚሉት በሺህዎች የሚቆጠር ህዝብም መኖሪያውን ለቆ ተሰዷል ። በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ በደቡብ ምስራቅ ቻድ የስደተኞች መንደር በተነሳ ግጭት ወደ ሶስት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል ። የዕርዳታ ድርጅቶች ተግባርም በግጭቱ ምክንያት ተስተጓጉሏል ። በዚህ መልኩ ወደ ከፋ ሁኔታ በመሸጋገር ላይ ያለውን የዳርፉር ቀውስ ለመታደግ የአውሮፓ ህብረት የገንዘብ እርዳታ እንደሚለግስ ከሁለት ሳምንት በፊት ዳርፉርን የጎበኙት የህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ጆሴ ማንዌል ባሮሶ ተናግረዋል ። ባሮሶ በወቅቱ ቀውሱ በዚህ መልኩ መቀጠል የለበትም ነበር ያሉት
ድምፅ
“በግልፅ አባባል አሁን ያለው ሁኔታ ዘላቂነት አይኖረውም ተቀባይነትም የለውም ነው ማለት ያለብን ። ተጨባጮቹን የሰላም አማራጮች በማጠናከር የዳርፉሩን የሰላም ስምምነት እንደገና በሁለት እግሩ ለማቆም በሚያስችል መንገድ ሁኔታውን መለወጥ ይኖርብናል ። አጀንዳችን ሰላም ነው ። ሌላ አጀንዳ የለንም ።”
ባሮሶ ይህን ሲሉ ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ተምልካች ድርጅት ሂዩመን ራይትስ ዎች ደግሞ በዳርፉር በሰላማዊ ሰዎች ላይ ለደረሰው ዕልቂትና ትርምስ ተጠያቂ ባላቸው በሱዳኑ መሪ ኦማር አልበሽርና በሌሎችም ከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው ላይ የአውሮፓ መንግስታት ማዕቀብ እንዲጥሉ ጥሪ አድርጓል ። የድርጅቱ የአፍሪቃ ክፍል ዳይሬክተር ፒተር ታኪራምቡዴ በአውሮፓ ደረጃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ማዕቀብ መተግበሪያው ጊዜ አሁን ነው ሲሉ የአውሮፓ መንግስትት በዳርፉር ጉዳይ ላይ ሊመክሩ በተዘጋጁበት ዋዜማ ላይ አሳስበዋል ።
የግንቦቱን የሰላም ስምምነት የተቃወሙትና አዲስ ህብረት የመሰረቱት የዓማፅያን ቡድኖችም መንግስትን እያጠቁ ነው ። አቡጃ ናይጀሪያ ውስጥ የተፈረመውን የዳርፉር የሰላም ስምምነት የሚቃወሙት የዓማፅያን ቡድኖች የመሰረቱት አዲስ ህብረት የካርቱም መንግስት ለንግግር ዝግጁ ከሆነ እኛም ለመደራደር እንቀመጣለን ብሏል ። አዲሱ ህብረት ዳርፉር ትውጣ ነው የሚለው ።