ሱዳን፣ የዓለም ዓቀፉ ፍርድ ቤት ክስና እርምጃዉ | የጋዜጦች አምድ | DW | 28.02.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ሱዳን፣ የዓለም ዓቀፉ ፍርድ ቤት ክስና እርምጃዉ

የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት ባሳለፉ ዉሳኔ መሰረት በሱዳን ዳርፉር ለተፈፀመዉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂ የሆኑት ሰዎች በዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎት እንዲቀርቡ የሚያዘዉ መግለጫ ይፋ ሆኗል።

በዳርፉር ጉዳይ የተከሰሱት ሃሩን

በዳርፉር ጉዳይ የተከሰሱት ሃሩን

በዚሁ መሰረትም የሱዳን መንግስት ባለስልጣንና አንድ የዚሁ መንግስት ድጋፍ እንዳለዉ የሚነገርለት የጃንጃዊድ ሚሊሻ መሪ የሚጠየቁበት ጥፋት ተዘርዝሮ ክስ ተመስሮቶባቸዋል። ሰዎቹ ክስ ቢመሰረትባቸዉም የሱዳን መንግስት ጉዳያቸዉ በአገር ዉስጥ ፍርዴት እንደሚያታይ አሳዉቋል።

በሱዳን ዳርፉር ሲፈፀም ለቆየዉና አሁንም ለሚፈፀመዉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በፀጥታዉ ምክር ቤት ይሁንታ በዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎት መቅረብ የሚገባቸዉ ሰዎች ማንነት ፈፅመዉታል ከተባለዉ ወንጀል ጋ ተዘርዝሮ መቅረብ መጀመሩ በርካታ የመብቶች ተሟጋች ድርጅቶችንና ቡድኖችን አስደስቷል። እዚህ ደረጃ ላይ የተደረሰዉ ግን የፀጥታዉ ምክር ቤት ዓለም ዓቀፉ የውጀል ችሎት ጉዳዩን መርምሮ እንዲያቀርብ በወሰነ ማግስት አልነበረም። ሁለት ዓመታትን ወስዷል። በቅድሚያ ክሱ ከተመሰረተባቸዉ አንዱ የመንግስት የሰብዓዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ሲሆኑ ዓለም ዓቀፉ ችሎት በስልጣን ላይ ባለ የመንግስት ባለስልጣን ላይ ክስ ሲመሰርት ይህ የመጀመሪያ መሆኑ ተነግሯል። ይህም ይላሉ መቀመጫዉን ብራስልስ ያደረገዉ የዓለም ዓቀፍ ቀዉስ አስወጋጅ ቡድን ምክትል ፕሬዝደንት ኒክ ግሮኖ በከፍተኛ ስልጣን ላይ የሚገኙ የሱዳን መንግስት ሰዎች በዳርፉር ለደረሰዉ ሰብዓዊ እልቂት ሰፊዉን ሚና መጫወታቸዉን ያሳያል። ለጊዜዉ የሁለቱ ስም ይፋ ሆኗል በህግም ይፈለጋሉ ወደወንጀል ችሎቱ ማቅረብ የሚቻልበት መንገድ ምን ይመስላል፤ የዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በትናንትናዉ እለት በሁለቱ ሱዳናዉያን ላይ የመሰረተዉ ክስ እንዳስደሰተዉ ከገለፀዉ ዓለም ዓቀፍ ቀዉስ አስወጋጅ ቡድን አንድሪዉ ሽትሮላይን ይህን ይላሉ
«በመጀመሪያ ማንም ቢሆን ከሱዳን መንግስት እንዲህ ያለዉን ግራ አጋቢ ነገር መጠበቁ አይቀርም። ምክንያቱም ይህ አገዛዝ ነዉ በስልታዊ መንገድ የበርካታ ሰዎች ህይወት እንዲጠፋ፤ ጥቃት እንዲፈፀምባቸዉ፤ መንደሮች እንዲወድሙና ወደሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ የራሱ ህዝቦች ከቤት ንብረታቸዉ እንዲፈናቀሉ ምክንያት የሆነዉ። ስለዚህ ይህ የካርቱም አገዛዝ ወደዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎት ሰዎቹ እንዳይቀርቡ የማይሞክረዉ ነገር ይኖራል ማለት አንችልም።»

እንደእሳቸዉ እምነትም የፀጥታዉ ምክር ቤት የዛሬ ሁለት ዓመት ለዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎት ትዕዛዝ ሰጥቷልና ሁኔታዉን ለማስፈፀም የሚያግዝበት መንገድ ይኖራል። የሱዳን መንግስት ከመነሻዉ ክሱን አለመቀበሉም ሆነ ትናንትም ያሰማዉ የእኛዉ እንዳኛቸዋለን ምላሽ ነገሩን የሚያወሳስበዉ ይመስላልና መንገድ ይኖር ይሆን?

«በትክክልም አንድ አጋጣሚ የሚመስለኝ በተለይ ሃሩን ታማም በመሆናቸዉ የዉጪ ህክምና ይፈልጋሉ። ለምሳሌ ወደዮርዳኖስና ግብፅ ለጤና ችግራቸዉ በተደጋጋሚ ይሄዳሉ። በተለይ ደግሞ ዮርዳኖስ የዓለም ዓቀፉን የወንጀል ችሎት ደግፋ ፈርማለች። ወደሌላ አገር ቢሄዱ ግዴታ አለ፣ እንዲታሰሩ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማቅረብ ነዉ። እንደነዚህ ያሉት ሀገራት እርምጃ እንዲወስዱ ማድረግ ይቻላል። እንዳልኩት አጋጣሚዎች ይኖራሉ። በእርግጥ ሁኔታዉ አሁን ወይም በዚህ ሳምንት ሲታይ ሰዎቹ ሄግ የሚመጡ ላይመስሉ ይችላል፤ ዉሎ ሲያድር ግን እዚያ እንደሚሆኑ እንጠብቃለን።»

ትናንት ዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎት በጉዳዩ ዉስጥ እጃቸዉ አለ ያላቸዉን ሁለት ሰዎች ነዉ ይፋ ያወጣዉ በቀጣይም የሌሎቹን ማንነት ያሳዉቃል ተብሎ ይጠበቃል። የሱዳን መንግስት እነዚህንም ሆነ ሌሎቹን አሳልፎ ባለመስጠት ቢፀናስ? በዳርፉር ለተፈፀመዉ ተጠያቂዎች የተባሉት ስም ታወቀ፤ ከዚያስ ምን ይደረጋል፤ በክስ ብቻ ያቆማል? አንድሪዉ ሽትሮዉላይን ግን መንገድ አለ ባይናቸዉ

«የሰዎቹን እጅ እንዲሰጥ ካርቱም ባለዉ አገዛዝ ላይ የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ጫናዎች መደረግ ይኖርባቸዋል። በርካታ ነገሮችን ማድረግ ይቻላል። እንዲመስለኝ አዉሮፓዉያን ዘግየት ያሉ ይመስላል በካርቱም ላይ ጫናዉን ለማብዛት። ለምሳሌ በአዉሮፓ ደረጃ ማዕቀብ በመጣል እነዚህን ሰዎች ለፍርድ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ሰፋ ባለዉ መንገድም በዳርፉር ሰላምን ለማስፈን ይቻላል።»

ቀዉስ አስወጋጅ ቡድኑ በዳርፉር የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ላይ በተጀመረዉ የመጀመሪያ ደረጃ የፍርድ ሂደት መደሰቱን የገለፀበት መግለጫ እርምጃዉ ተመሳሳይ ድርጊት ለሚፈፅሙ ሌሎች መንግስታት መልዕክት እንዳለዉ ገልጿል።

«እንደሚመስለኝ ዋናዉ ተፈላጊዉ ጉዳይ ይህ ነዉ። ዓለም ዓቀፍ የወንጀል ችሎቱና ዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ በዚህ አጋጣሚ ያስተላለፈዉ መልዕክት፤ (ምክንያቱም የፀጥታዉ ምክር ቤት በመሆኑ ምርመራዉ እንዲደረግ ትዕዛዙን የሰጠዉ፤) መልዕክቱ የጦር ወንጀል ባለበት፤ በብዙሃን ላይ የሚፈፀም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በቸልታ አይታለፍም። ዉሎ አድሮ ጊዜ ሊወስድ ይችላል እንጂ ፍትህ ፊት ትቀርባላችሁ የሚል ነዉ። እንደማስበዉ ይህ በራሳቸዉ ህዝብ ላይ ወንጀል ለሚፈፅሙ ለሌሎች አምባገነኖችና ገዢዎች ጠንካራ መልዕክት ነዉ።»