ሱዳን «መንታ መንገድ» | የጋዜጦች አምድ | DW | 29.11.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ሱዳን «መንታ መንገድ»

የግብፅ ገዢዎች የኑብያ አረብን ከፖለቲካ ሥልጣን ሌላ ከምጣኔ ሐብቱ፣ ከእዉቀቱ፣ ከጉልበቱም እያጋሩ ጥቁሩን መርገጣቸዉ ያዉ «ዘር ከልጓም ይስባል» ከማሰኘት ሌላ ብዙ ትንታኔ አያስፈልገዉ ይሆናል።አናሶችን እያስጠጉ፣ እያስታጠቁ፣ በአብዛሐዉ ላይ እያዘመቱ በመግዛቱ ጥበብ የተካኑት የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች በ1898 ነፃነት የጠየቁ የመሕዲ አማፂዎችን ከግብፅ አጋሮቻቸዉ ጋር ደምስሰዉ ሱዳንን ከተረከቡ በሕዋላ ግብፆች የጀመሩትን ሥልት አሳምረዉ ቀጠሉበት።

ነጋሽ መሐመድ

«የሱዳን ሕዝብ እንዲሕ አይነቱን ለዉጥ ለረጅም ጊዜ ከሚገባዉ በላይ ጠብቋል።በሱዳን መንግስትና በሱዳን ሕዝብ ነፃ አዉጪ ንቅናቄ መካካል የተደረገዉ ድርድር የሚጠናቀቅበት፣ የተደረሰዉ ስምምነት ገቢር መሆን የሚጀመርበት ዋና ወቅት አሁን ነዉ።»-የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን።

የፀጥታዉ ምክር ቤት ዉሳኔ ገቢር ከሆነ-አናን እንዳሉት ያን እዉነት ለዘመናት ለጠበቀዉ ለሱዳን ሕዝብ አስደሳች ነዉ።-የተፋላሚ ሐይላት ቃል ከተከበረ-የምሥራች።ለአካባቢዉ ሠላምም-የበጎ ተስፋ ጭላንጭል ፈንጣቂ ነዉ።የርዳታና የመብት ተሟጋቾች መጠራጠራቸዉ፣ በሱዳኑ የርስ በርስ ጦርነት እጃቸዉ አለበት ከሚባሉ ገሚሶቹ ክፉ ደግ አለማለታቸዉ ግን ደስታ፣ የምሥራች፣ ተስፋዉን አደብዝዟታል።ሱዳን መንታ መንገድ ላይ ነች።


«ለሱዳን ሕዝብ፣ ለአፍሪቃ፣ ለአለም አቀፉ ማሕበረሰብ በያዝነዉ አመት ማብቂያ በሚመጣዉ አመት መግቢያ የሠላም መባዕ-ሥጦታ ለመስጠት ሙሉ በሙሉ ቁርጠኞች ነን።»-የሱዳኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ዓሊ ኦስማን ጣሐ።-

የሱዳን ሕዝብ ነፃ አዉጪ ንቅናቄ መሪ ጆን ጋራንግም ደገሙት።

«ችግሮቹን ለይተን ሐገራችንን አንድ ለማድረግ የምንችለዉን ሁሉ እናደርጋለን።ከመንግስታቱ ማሕበረሰብ በሠላም፣ በልማትና ብልፅግና እንድንቀላቀል።»

የትላልቆቹ ሐገራት ፖለቲከኞች-ግዙፍ መገናኛ ዘዴዎችም በተደጋጋሚ እንደሚነግሩን፣ የትናንሾቹ ሐገራት ትላልቅ ፖለቲከኞች፣ ትናንሽ መገናኛ ዘዴዎችም በየቋንቋችን እንደሚደጋግሙልን የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት የተጀመረዉ በ1983 (ዘመኑ በመሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ነዉ።

ብሪታንያዊዉ እዉቅ ምፀተኛ ደራሲ ጆርጅ ኦርዌል-(እዉነተኛ ሥሙ Eric Arthur Blair ነዉ) እድሜዉ ከገፋ፣ ዝናዉ ከናኘም በኋላ በ1930ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ «---ማንኛዉንም እዉነት ወይም ሁነት ጋዜጦች በትክክል እንደማይዘገቡት ያወቅሁት ገና በልጅነቴ ነዉ---»ብሎ ነበር።ጋዜጠኝነት እንደየ ሙያ መስኩ ሁሉ በረቀቀ፣ በሠፋ-በጠለቀበት፣ በጣሙን የእዉነት-ሐሰት እንዴትነት በሐይለኞችና ሐብታሞች ፍላጎት በሚበይንበት በዚሕ ዘመን ኦርዌል ዘር ማንዘሮቹ የሚሉ-የሚያደርጉት ቢያይ የሚለዉን አናዉቅም።

የሱዳንን የርስ በርስ ጦርነት በ1983 መጀመሩን የሚነግሩ፣ የሚስነግሩ፣ የሚያናግሩንም የትላልቆቹ ሐገራት ግዙፍ መገናኛ ዘዴዎች ግን የጦርነቱን ምክንያት፣ የኦርዌል ሐገር እዉቅ ዜና አገልግሎት ሮይተር ፣ ባለፈዉ ሐሙስ ዘገባዉ እንዳረጋገጠዉ የካርቱም መንግሥት እስላማዊ ሕግ ገቢር ለማድረግ መመከሩ ክርስያኖችንና ሐይማኖት የለሾችን በማስቀየሙ ነዉ።

በ1994 ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያለቀበት የሩዋንዳ ጭፍጨፋ-ምክንያት ለትላልቆቹ ሐገራት ፖለቲከኞች ለየመገናኛ ዘዴዎቻቸዉ፣ እነሱ ያሉትን እዉነት-ሐሰትነት ሳይመረምሩ ለሚያራግቡ አላዋቂዎችም የጎሳ ጠብ እንጂ፣ የቤልጂግ ቅኝ ገዢዎች የቀበሩት የልዩነት መርዝ ምርቅዛት መሆኑ እንደተድበሰበሰ ነበር።

የኮትዲቪያር የርስ በርስ ጦርነት፣ የፈረንሳይ ቅኝ ገዢዎች የደቡቡን የሐገሪቱን ሕዝብ አስጠግተዉ ለሐብት፣ እዉቀት-ስልጣን ሲያበቁት ሰሜኑን የመግፋታቸዉ አስተጋብኦት ዉጤት መሆኑ ባይዳፈን አይገለጠም።The SUN የተባለዉ የብሪታንያ ጋዜታ የቀድሞ ዋና አዘጋጅ ሮናልድ ሥፓርክ በ1991 እንዳለዉ እዉነቱን ተናግሮ ሐገሩን ከሚጎዳ ጋዜጣ የእዉነቱን አንድ ጫፍ ብቻ የሚፅፍ አንድ ሚሊዮን ጊዜ ይሻላል።መርሁ እንዲሕ የሆነዉ መገናኛ ዘዴና ፖለቲከኛ ሥለሱዳን፣ ሥለሩዋንዳ፣ ሥለኮትዲቯር፣ ሥለ መላዉ አፍሪቃ ወይም ሥለአለም ባጣቃላይ ከእዉነት ቁንፅል-በላይ መሠረታዊዉን እዉነት ባይል አይደንቅም።

የትንናሾቹ ሐገራት ፖለቲከኛና መገናዘዴዎች አንዳዴ ሥለየራሳቸዉ ሳይቀር-ትላልቆቹ የሚሉ የሚያደርጉትን እዉነት ሐሰትነት ሳይመረምሩ መድገማቸዉ ነዉ-ቀቢፀ ተስፋዉ።ማንም ምን ቢለዉ እዉነቱ በርግጥ አንድ ነዉ።በተድበሰበሰዉ እዉነት ላይ ተመስርቶ የሚሰጠዉ የተድበሰበሰ መፍትሔ በየጊዜዉ እየተናደሌላ ችግር መዉለዱ---ነዉ ድቀቱ።ለሱዳን፣ ለመላዉ አፍሪቃም---ሥለሶማሊያ፣ ሥለ ብሩንዲ፣ ሥለኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ሥለኮትዲቫር፣ ሥለ ላይቤሪያ፣ ሥለኢትዮ-ኤርትራ ሠላም በተደጋጋሚ የተፈረመዉ ዉል ቀለም ሳይደርቅ ሌላ የእልቂት-ሥጋት ከመጋሙ መጥፎ ልምድ ሌላ አስተማሪ አይኖርም።

----------------------------

የግብፅ ገዢዎች የኑብያ አረብን ከፖለቲካ ሥልጣን ሌላ ከምጣኔ ሐብቱ፣ ከእዉቀቱ፣ ከጉልበቱም እያጋሩ ጥቁሩን መርገጣቸዉ ያዉ «ዘር ከልጓም ይስባል» ከማሰኘት ሌላ ብዙ ትንታኔ አያስፈልገዉ ይሆናል።አናሶችን እያስጠጉ፣ እያስታጠቁ፣ በአብዛሐዉ ላይ እያዘመቱ በመግዛቱ ጥበብ የተካኑት የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች በ1898 ነፃነት የጠየቁ የመሕዲ አማፂዎችን ከግብፅ አጋሮቻቸዉ ጋር ደምስሰዉ ሱዳንን ከተረከቡ በሕዋላ ግብፆች የጀመሩትን ሥልት አሳምረዉ ቀጠሉበት።

የለንደን ቅኝ ገዢዎች በ1956 የሡዳንን ነፃነት መቀበላቸዉን ሲያስታዉቁ የካርቱምን ቤተ-መንግሥት ያስረከቡት ወትሮም ለገዢነት ላዘጋጁዋቸዉ አናሳ አረቦች ነበር።ግብፆችና እንግሊዞች የጨቆኑት አብዛሐዉ ጥቁር ሱዳናዊ ከነፃነትም በሕላ ሥልጣናም፣ ሐብትም፣ መብትም መነፈጉ ያሳደረበት ብሶት ከአመፅ ሌላ፣ ሌላ ምርጫ አላሳየዉም።የደቡቡ ጥቁር በነፃነት ማግስት፣ የምዕራቡ (ዳርፉር) ደግሞ በ1969 ግድም ብረት አንግቦ አመፀ።

የጥቁሮቹ አመፅ፣ ከኮሚንስቶች ሴራ ጋር ተዳምሮ የሱዳንን ሲቢላዊ መንግሥት ሲገዘግዘዉ ጄኔራል ጀዓፈር አኑሜሪ የሰለለዉን ቀጭን ገመድ በጥሰዉ የካርቱምን ቤተ-መንግሥት ጠቀለሉት።1969። ኑሜሩ ሥልጣን በያዙ ባመቱ ወደ ኮሚንስቶቹ ያዳሉ የነበሩት የግብፅ ብሔረተኛ መሪ ገማል አብድናስር ሞተዉ ምክትላቸዉ አንዋር አሳዳት መተካታቸዉ ኮሚንስቶችን ያድኑ ለነበሩት የምዕራብ ሐይላት የድርብ ድል ጅምር ነበር።

ከግብፅና ሱዳን ጋር የነበራትን ግንኙነት እንደ ጥሩ ቅርስ የተጠቀመችዉ ብሪታንያ በቀጥታ፣ ዩናይትድ ስቴትስና ሌሎች ተባባሪዎችዋ በስዑዲ አረቢና በሌሎች የአካባቢዉ ወዳጆቻቸዉ አማካይነት ሳዳትን ከጃቸዉ አስገብተዉ በሳዳት በኩል አምባገነኑን ኑሜርን ሲጠልፉ---ኑሜሪ የጠቅላይ ሚንስትርነት ሥልጣን ሳይቀር የሰጧቸዉን የሱዳን ኮሚንስቶች አጨዱ።ለኑሜሪ ዉለታ የሱዳን ጥቁሮች የጀመሩትን አመፅ ማዳፈኑን እንደ አንዱ ብልሐት ያዩት የምዕራብ ሐይላት በኢትዮጵያዉ ንጉሠ-ነግሥት አፄ ሐይለ-ሥላሴ በኩል በ1972 የካርቱም መንግሥትንና አማፂያኑን የሠላም ዉል አፈራረሙ።

በ1983 ሱዳን ላይ የነበረዉ መንግሥት ከምዕራቦች በገፍ ይረዳ የነበረዉ የኑሜሪ አምባገነን እንጂ እስላማዊ መንግሥት አልነበረም።ምዕራቦች፣ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ሶሻሊስታዊ መንግሥት፣ የሊቢያና የዩጋንዳ፣ ተፃራሪዎቻቸዉን ለማዳካም የካርቱምን መንግሥት ጃስ ሲሉ ለኑሜሪ ዉድቀት ይቆፍሩ የነበሩ ምሥራቆች ባንፃሩ በአካባቢዉ ተባባሪዎቻቸዉ በኩል የተዳፈዉን የደቡብ ሱዳን ጥቁሮችን አመፅ ለኮሱት።

በ1989 በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙት ጄኔራል ዑመር ሐሰን አልበሽር በአል-ቱራቢ ምክር የሸሪዓ ሕግን ገቢር ለማድረግ ሲያዉጁ ምዕራቡ ወትሮ ኑሜርን በመቃወማቸዉ እንደጠላት ይመለከታቸዉ ለነበሩት ለደቡብ ሱዳን አማፂዎች ድጋፉን ይሰጥ ገባ።የዉጊያዉ ሰበብም ከፖለቲካ ይልቅ የሐይማኖት-ጭቆና፣ ከርዕዮተ-ዓለም ይብስ፣ የዘር-ቅራኔ መሆኑ ይነገረን ያዘ።ሁለት ሚሊዮን የሚገመት ሱዳናዊም ያልቅ ጀመር።አራት ሚሊዮን ይፈናቀል።

የወቅቱ የፀጥታዉ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የዩናይትድ ስቴትሱ አምባሳደር ጆን ዳንፎርዝ ለምክትል ፕሬዝዳንት ዓሊ ኦስማን ጣሐና ለሊቀመንበር ጆን ጋራንግ እንደነገሩት የፈረሙት ሥምምነት ገቢር አይሆንም ብለዉ የሚጠራጠሩ ወገኖች መሳሳታቸዉን ማረጋገጥ የሁለቱና ሁለቱ የሚወክሏቸዉ ወገኖች ፋንታ ነዉ። ከአስራ አንድ አመት እፎይታ ሌላ የሱዳንን ሕዝብን የሚፈጀዉን ጦርነት የማስቆሙ ዋና ሐላፊነት በርግጥ የተፋላሚዎቹ ፋንታ ነዉ። የነሱ ብቻ ግን አይደለም።

«ሱዳንን የበለፀገች፣ ከራስዋና ከጎረቤቶችዋ ጋር ሠላም ወዳወረደች ሐገርነት የመለወጡ ሒደት ባስቸኳይ መጀመር አለበት።ሱዳን ሰብአዊ መብት የሚከበርባት፣ አመፅ በፖለቲካዊ ድርድር የሚለወጥባት ሐገር መሆን አለባት።ይሕ ሒደት ሳይዘገይ መጀመር አለበት።» -አምባሳደር-ዳንፎርዝ

ሰፊዋ፣ በረሐማ ሐገር እንደ ጥንቱ የጥጥ፣ የሒና፣ የሰሊጥ፣ የብረትና መዳብ መቃረሚያ ብቻ አይደለች።በቀን የሚዛቅባት፣ የተከማቸባት ነዳጅና ጋስ አለምን ያጓጓል።አምባሳደር ዳርፎርዝ እንዳሉት አለም የሱዳንን ሰላምና ብልፅግና ለማየት የሚሻዉ ሐብቷ አጓጉቶት ይሁን ወይም ለሰላሟ በመሰብ ቅንነት---አይታወቅም።የፀጥታዉ ምክር ቤት በታሪኩ ከሰወስቴ በላይ አድርጎት የማያዉቀዉን ለሱዳን ሲል ማድረጉ፣ የአለም ዘዋሪዋ ሐገር ትልቅ ዲፕሎማት ያሉትን ማለታቸዉ ግን ሐያላኑ እስካሁን በሱዳን ላይ የሚያደርጉትን ለሱዳን ለማድረግ የመወሰናቸዉ ዋቢ ነዉ።

ሒዩማን ራይትስ ወች የተባለዉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት እንደሚለዉ ግን የፀጥታዉ ምክር ቤት ዉሳኔ የሱዳን መንግሥት በዳርፉር ሕዝብ ላይ የሚፈፅመዉን በደል እንዲቀጥል ዋስትና የመስጠት ያህል የሚቆጠር ነዉ።ባለፈዉ የካቲት እንደገና ባገረሽዉ የዳርፉር ዉጊያ ሰባ ሺሕ ሕዝብ ተገድሏል።ከአንድ ሚሊዮን ተኩል በላይ ተፈናቅሏል።የሱዳን መንግስትና የዳርፉር ተፋላሚዎች ከሁለት ሳምንት በፊት አቡጃ-ናጄሪያ ዉስጥ የተፈራረሙት ስምምነት ሌላ የሰላም ተሥፋ አጭራል። አምንስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለዉ ግን በካርቱም መንግሥት ላይ የጦር መሳሪያ ካልተጣለ ሠላም ዛሬም ሩቅ ነዉ።

-----------------

የተፋላሚዎች ቃል፣ የአለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዉሳኔ መጠበቅ ለሱዳን ብቻ ሳይሆን ለአካባቢዉም ሠላም እጅግ ጠቃሚ ነዉ።ግን አምንስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚዘረዝረዉ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ
ቤሎሩስ፣ ዩክሬን፣ ፖላንድ፣ ኢራን፣ ስዑዲ አረቢያ፣ ሌሎችም ለሱዳን ተፋላሚዎች ጦር መሳሪያ ይሸጣሉ።የብሪታንያ፣ የአይርላንና የብራዚል ኩባንዮች የጦር መሳሪያዉን ያቀባብላሉ።የግብፅ፣ የሊቢያ፣ የዩጋንዳ፣ የኤርትራ፣ የኢትዮጵያ መንግሥታት በሱዳኑ ጦርነት ተነካክተዋል።የናይሮቢ-አቡጃዉ ቃል ዉሳኔ የፈጠረዉ ደስታና ተስፋ እንዲፀና የሁሉንም ይሁንታ ማግኘት አስፈላጊ ነዉ።