ሱዳንና የፖለቲካው ትንንቅ፣ | አፍሪቃ | DW | 04.07.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ሱዳንና የፖለቲካው ትንንቅ፣

በሱዳን መዲና በካርቱም፣ የኑሮ ውድነትን፣ የፍትኅና ርትእ እጦትንና የመሳሰሉ የኅብረተሰቡን ችግሮች መነሻ በማድረግ፤ ተቃዋሚዎች በተከታታይ አደባባይ እየወጡ ሰልፍ ሲያሳዩና የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎችም፤ በጭካኔ አመጹን ለማረቅ

ሲጥሩ ነበረ የሰነበቱት። በሌላ በኩል የአገሪቱ አመራር ያስመረራቸው ተቃዋሚ ኃይሎች በዳርፉርና ደቡብ ኮርዶፋን ብረት አንስተው ከመፋለም አልተቆጠቡም። በሌላም በኩል የካርቱም መንግሥት፣ ከጁባ አስተዳደር ጋር እንደገና እስከመቆራቆስ መድረሱና አሁን በሸምጋዮች ጥረት አዲስ አበባ ላይ
የሰላም ውይይት በማካሄድ ላይ መሆኑ የታወቀ ነው።በካርቱም የተቃውሞ ሰልፈኞች ፤ በተደጋጋሚ አደባባይ እየወጡ በሥርዓቱ ላይ ያላቸውን ምሬት ሲገልጡ ሰንብተዋል። በዕቃ ዋጋ ግሽበት፤ በገንዘቡ ዋጋ መቀነስ የተቆጣው ምን ያህሉ ነው? ወይስ ባጠቃላይ በኦማር ሐሰን ኧል በሺር አገዛዝ ላይ ያነጣጠረ የፖለቲካ ተቃውሞ ነው? ፍሎሪያን ዴነ---
«ዋናዉ የተቃዉሞ መንስኤ የፖለቲካ ነፃነት ማጣት ከሚለዉ ይልቅ ከማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋ የተያያዘ ነዉ። ከሁለት ሳምንታት በፊት መንግስት ቤንዚን እና ስኳር ላይ ያደርግ የነበረዉን የገንዘብ ድጎማ ሲያቆም፣ የዋጋ ንረት በመከሠቱ ለበርካታ ሰዎች ሱዳን ዉስጥ ኑሮዉ ከኤኮኖሚ አንፃር አስቸጋሪ ሆኗል። ተቃዉሞዉ የተነሳዉ ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ሲሆን፣ በኤኮኖሚዉ ችግር የሚሰቃየዉ ሌላዉ የኅብረተሰብ ክፍልም ተሳትፏል። ይኸዉም ከጡረተኞች ክፍያ ጥያቄ አንስቶ የተጀመረዉ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ በአብዛኛዉ እስከ አንድ መቶ ሰዎች የሚሳተፉበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ።»

እነዚህ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ቁቻቸው ምናልባት ከማየሉ የተነሣ፤ በግብጽ መዲና በካይሮ ፣ በታህሪር አደባይ ይታይ የነበረውን ዓይነት የህዝብ አመጽ የሚያጋግሊ ይመስሎታል?
«ይህን እጠራጠራለሁ። እስካሁን ያለዉ በርካታ ህዝብ ከሚሳተፍበት የተቃዉሞ ንቅናቄ የራቀ ሁኔታ ነዉ። በዚያ ላይ የፀጥታ ኃይሎች የጭካኔ ርምጃ ለመዉሰድ ወደኋላ አይሉም፤ በዚህ ምክንያትም የመብት ተሟጋቾችና ተቃዋሚዎች ባለፉት ቀናት እስር ቤት ታጉረዋል። ስለዚህ የተቃዋሚዎቹ የማንቀሳቀስና የማስተባበሩ አቅም በመገደቡ ለምሳሌ በታህሪር አደባባይ እንደሆነዉ ኻርቱም ላይ መንግስትን ወጥሮ ለመያዝ የሚያስችል ሁኔታ በቅርቡ አይጠበቅም።»


የሱዳን አገዛዝ፤ ተቃዋሚ ሰልፈኞቹን፤ አንዴ ጽዮናውያን ያሰማሯቸው፤ ሌላ ጊዜም በዳርፉሮች የተቆሰቆሱ ናቸው እያለ ሲዘልፍ ይሰማል። ይህ ከተጨባጩ የአገር ውስጥ ውዝግብ ጋር የሚገናኝበት ሁኔታ አለ? በሌሎች ላይ ለማላከክ መንግሥት የሚያደርገው ጥረት እስከምን ድረስ ተዓማኒነት አለው ይላሉ?
«ይህን እውነትን ወደ ጎን እየገፉ፤ የማይዛመድን ጉዳይ እያስመሰሉ ለማቅረብ የሚደረግበትን ጥረት በርግጥ ማንም አያምንም፤ አይቀበልም። ቀደም ብዬ እንተናገርኩት ህዝብ በብዛት የሚሳተፍበት ተቃዉሞ በአሁኑ ሰዓት የለም። እናም ይህ የፅዮናዉን ጣልቃ ገብነት የሚለዉ ቅዠት ወይም የፀጥታ ኃይሎች ርምጃ የሚለዉ ማደናገሪያ መሆኑን ከሞላ ጎደል ሊያሳይ ይችላል። ይህም የመንግስት ዉሸት መሆኑንም አብዛኛዉ የሱዳን ህዝብ በእርግጠኝነት ያዉቃል።»
በሰሜን ሱዳን ተቃውሞ በመካሄድ ላይ እንዳለ፣ በካርቱም መንግሥትና በጁባ መንግሥት መካከል አዲስ አበባ ውስጥ፣ ድርድር በመካሄድ ላይ ነው። በዚያም የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ይካሄዳል። በሱዳን ጉዳዮችም ላይ መነጋገሩ እንደማይቀር ይገመታል። ለሰሜንና ደቡብ ሱዳን ውዝግብ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ በሚካሄድ ውይይት መላ ማግኘት የሚቻል ይመስሎታል? ወይስ በመጨረሻ ጦር መሣሪያ ነው የሚፈታው?


«የፖለቲካ መፍትኄ ከመሻት በስተቀር፤ ሌላ አብነት የለውም። እዚያ እስኪደረስ ደግሞ፣ የጠብመንጃ ድምፅ ማስተጋባቱ አይቀሬ ነው። የሚመስለው ከነአካቴው፤ ፀጥ ያለበት ሁኔታም አጋጥሞ አያውቅም። በሰሜንና ደቡብ ያለው ድንበር ፤ የነዳጅ ዘይት ሀብት ገቢ፤ የዜግነት ጥያቄ፣ እነዚህና የመሳሰሉ አንዳንድ በግልጽ የሚታወቁ ጥያቄዎች፤ ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን ስትቀዳጅ፤ እልባት ሳይደረግላቸው በእንጥልጥል የተሸጋሸጉ ናቸው። እናም በአጭር ጊዜ ችግሩ የሚፈታ አይመስልም። እርግጥ የነዳጅ ዘይት ገቢን በተመለከተ ሁለቱም ጽኑ ፍላጎት ስላላቸው ይህኛው ጉዳይ ቶሎ መፍትኄ ያገኝ ይሆናል። አንገብጋቢው የድንበር ጉዳይ እልባት ሳይደረግለት የነዳጁ ጉዳይ ቀድሞ መላ ሳይፈለግለት አይቀርም። በአንዳንድ አውራጃዎች ላይ የተነሣው ይግዛት ይገባኛል ጥያቄ ግን፣ አሁንም ቢሆን ጠብመንጃ ማማዘዙ እንደማይቀር ነው ማሰላሰል የሚቻለው።»

ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሰ

ተዛማጅ ዘገባዎች