ሰብ ሕድሪ ሲቭል ማሕበረሰብ ትግራይ አመራሮቹ እስርና ማዋከብ እየገጠማቸው መሆኑን አስታወቀ | ኢትዮጵያ | DW | 21.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ሰብ ሕድሪ ሲቭል ማሕበረሰብ ትግራይ አመራሮቹ እስርና ማዋከብ እየገጠማቸው መሆኑን አስታወቀ

ሰብ ሕድሪ ሲቭል ማሕበረሰብ ትግራይ የተሰኘው የሲቪክ ተቋም አመራሮቹና አባላቱ እስርና ማዋከብ እንደገጠማቸው አስታወቀ። ማኅበሩ "ዴሞክራሲ የሰፈነበት ሥርዓት እንዲታነፅ፤ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፤ ከሙስና የፀዳ ሥርዓት እንዲኖር" ለመስራት የተቋቋመ ነው። ሊቀ-መንበሩ አቶ መሐሪ ዮሐንስ እንደሚሉት ማኅበሩ ችግር የገጠመው ከምሥረታው ጀምሮ ነው

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:19

የክልሉ መንግሥት መረጃ የለኝም ብሏል

'ሰብ ሕድሪ ሲቪክ ማሕበረሰብ ትግራይ' የተሰኘ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀስ የሲቪክ ተቋም በአባላቱና ደጋፊዎቹ ላይ ጥቃት እየደረሰ መሆኑን ገለጸ፡፡ ተቋሙ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የህዝብ ችግሮችን ያጋለጡ አባላቶቹ እንዲሁም ባዘጋጃቸው ህዝባዊ የውይይት መድረኮች የተገኙ ተሳታፊዎች እየታሰሩ እንደዚሁም ማስፈራርያ እና እንግልት እየደረሰባቸው ነው ብሏል፡፡
ሰብ ሕድሪ ሲቪክ ማሕበረሰብ ትግራይ የተባለው ተቋም ከትግራይ ክልል ፍትሕ ቢሮ ሕጋዊ ፍቃድ አግኝቶ በክልሉ መንቀሳቀስ የጀመረው በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም. ነው።  ተቋሙ በተለያዩ የትግራይ ከተሞች እየተንቀሳቀሰ በትግራይ ህዝብ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ዙርያ ከህዝብ ጋር የሚያደርገው ውይይት ዕንቅፋቶች እየገጠሙት እንደሆነ በዛሬው መግለጫው አስታውቋል። የሰብ ሕድሪ ሲቪክ ማሕበረሰብ ትግራይ ሊቀ መንበር አቶ መሐሪ ዮሐንስ "ከምስረታ ጀምሮ ይገጥመን የነበረ ችግር አሁን ተባብሶ አባላቶች እና ደጋፊ እስከማሰር እንዲሁም ማንገላታት ደርሷል" ይላሉ፡፡ 
በቅርቡ የሲቪክ ተቋሙ ሊቀመንበርን ጨምሮ ሰባት አባላት በትግራይ ክልል ፅጌረዳ ከተማ ከህዝብ ጋር በአስተዳደር ችግሮች ዙርያ ለመወያየት በተጓዙበት ታስረው "ከፍተኛ እንግልት" ደርሶባቸው መለቀቃቸውን ተቋሙ በምሳሌነት ጠቅሷል፡፡ በትግራይ ክልል ክልተ አውላዕሎ ወረዳ "ሰብ ሕድሪ በጠራው ስብሰባ ተገኝታችኋል" የተባሉ የህዝባዊ ውይይት መድረክ ተሳታፊዎችም "ታስረዋል፣ ተንገላተዋል፣ ማስፈራርያም ደርሶባቸዋል" ይላሉ አቶ መሐሪ፡፡
እንደሰብ ሕድሪ ሲቪክ ማሕበረሰብ ትግራይ ሊቀመንበር ገለፃ "ይህን እያደረገ ያለው የቀድሞውን የከሰረ መንገድ ለመመለስ የሚጥር የፖለቲካ ኃይል ነው"፡፡ ይህ አካሄድ ተቋሙ ይዞት የተነሳውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማነፅ ሂደት እና የመደገፍ ስራ እንደሚጎዳ በመጥቀስ በአስቸኳይ ሊስተካከል ይገባል ሲል ተቋሙ አሳስቧል፡፡
የተቋሙን አቤቱታ አስመልክቶ የተጠየቀው የትግራይ ክልል ፀጥታ እና አስተዳደር ቢሮ "በተቋሙ አባላትና ደጋፊዎች ላይ ደረሰ ስለተባለው በደል የደረሰን መረጃ የለም" ብሏል፡፡  "ጥቃት ተፈፀመባቸው" ከተባሉት ወረዳዎች መካከል አንዷየሆነችው የክልተ አውላዕሎ ወረዳ አስተዳዳሪን ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች