1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰብዓዊ መብት የመደበኛ ትምህርት አካል እንዲሆን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዳንኤል በቀለ ገለጹ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 1 2015

ሰብዓዊ መብት በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት እንዲካተት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥረት እያደረገ መሆኑን ዶክተር ዳንኤል በቀለ ተናገሩ። ይኸ ጥረት ከትምህርት ሚኒስቴር "በጎ ምላሽ" እንዳገኘ የገለጹት ኮሚሽነሩ ለኢትዮጵያ ተማሪዎች ሲሰጥ የቆየው ሲቪክ ትምህርት "የሰብዓዊ መብቶች መርኆዎችን የሚጣረሱ አስተሳሰቦች" እንደተገኙበት ተናግረዋል

https://p.dw.com/p/4KlsA
Äthiopien | Daniel Bekele | Äthiopische Menschenrechtskommission
ምስል Solomon Muchie/DW

ሰብዓዊ መብት በመደበኛ ትምህርት እንዲካተት የሚደረገው ጥረት በጎ ምላሽ እንዳገኘ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል

ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን ለማሰብ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የተጀመረው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ አዲስ አበባን ጨምሮ በአምስት ከተሞች ይካሄዳል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ዛሬ ይህንን አስመልክቶ ሲናገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብቶች አከባበርን በተመለከተ መሰረታዊ ትምህርት የሚያስፈልግ በመሆኑ ይህ እውን እንዲሆን ጉዳዩ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ እንዲካተት ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል።

"የኢትዮጵያ ተማሪዎች በሙሉ ከአነስተኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ደረጃ በሚማሩበት ጊዜ በመደበኛ ትምህርት ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት የትምህርት ሥርዓቱ አካል እንዲሆን እየሰራን ነው" ብለዋል።  

ኮሚሽነሩ ከመንግሥት እና ከሕወሓት ድርድር ጋር ተያይዞ የሽግግር ጊዜ ፍትሕ አስተዳደር አስፈላጊነት ታምኖበት ጉዳዩ እውቅና ማግኘቱን አድንቀዋል። ይህም እውነት እንዲወጣ እና እንዲታወቅ፣ ያጠፉ ሰዎች እንዲጠየቁና እንዲቀጡ ፣ የተጎዱ ሰዎች እንዲካሱ እና እንዲጠገኑ እንዲሁም ተመሳሳይ የመብት ጥሰቶች እንዳይፈፀሙ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ያግዛል ብለዋል። ይህም ሰላምና እርቅን በዘላቂነት በመፍጠር ግጭቶች እንዲቀንሱ ያግዛል ብለዋል። ውጥኑ በትክክል መፈፀሙንም በቅርበት እንደሚከታተሉም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤት
ሰብዓዊ መብት የመደበኛ ትምህርት አካል እንዲሆን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሚያደርገው ጥረት በጎ ምላሽ እንዳገኘ ዋና ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንኤል በቀለ ገልጸዋል። ምስል Solomon Muchie/DW

በፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ አሳሳቢ የመብት ጥሰቶች አሉ ይህንንም ለማረም በፊልሞች የሚተላለፉ መልእክቶች ስለ ሰብአዊ መብቶች እውቀት እንዲስፋፋ ያግዛልም ብለዋል። "ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ የታሰሩ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ በየ ፖሊስ ጣቢያው። በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ በሰዎች ላይ አካላዊ ጥቃት እየተፈፀመ እንደሆነ ምልክቶች አግኝተናል። አንዳንድ እሥር ቤቶች ውስጥ የታሰሩ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙ ይደረጋል። እነዚህ ሁሉ እንዲሻሻሉ ተቀራርበን እንሠራለን" ብለዋል 

ተፈናቃይ ዜጎች ድጋፍ የማግኘት ፣ ወደነበሩበት ሥፍራ የመመለስ መብታቸው እንዲጠበቅ ሕግ ያስገድዳል ያሉት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር ) ኢትዮጵያ ውስጥ ከፖለቲካ ፍላጎት የሚመነጩ ቀውሶች ፖለቲካዊ መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል፣ ለዘላቂ መፍትሔውም ይህ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል። የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አሁን ላለበት አሳሳቢ የሚባል ደረጃ ለመድረሱ ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ ስለ ሰብአዊ መብቶች ያለው አነስተኛ ግንዛቤ በአሉታዊ መልኩ አስተዋዖ አድርጓል በማለት እንዲታረምም ሁሉን አቀፍ ሰፊ ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

Äthiopien | Kämpfer der Fano-Miliz in Lalibela in der nördlichen Amhara-Region
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW
ዋናዉን ገፅ ተመልከት