ሰርከስ ደብረብርሃን በጀርመን ብሩል ከተማ | ባህል | DW | 07.11.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ሰርከስ ደብረብርሃን በጀርመን ብሩል ከተማ

ከተመሠረተ ከ20 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የሰርከስ ደብረብርሃን ቡድን በአሁን ሰዓት አውሮፓ ውስጥ እየተዟዟረ ትርዒት በማቅረብ ላይ ይገኛል። በኮሮና ምክንያት ሰባት የቡድኑ አባላትን ብቻ ይዞ የተጓዘው ሰርከስ ደብረብርሃን ሰሞኑን በዚህ በጀርመን የተለያዩ ከተሞች ተዟዙሮ ብቃቱን ያሳየበት ብቻ ሳይሆን የባህል ልውውጥም ያደረገበት ነበር።

ሰርከስ ደብረብርሃን በጀርመን ብሩል ከተማ

ኢትዮጵያ ውስጥ ዝናን ያተረፈው የሰርከስ ደብረብርሃን ቡድን ከቦን ከተማ በአቅራቢያችን በምትገኘው ብሩል በተሰኘችው ከተማ ውስጥ ትርዒት ሲያሳይ ያለፈው እሁድ የመጀመሪው ነው። ታዳሚዎቹ በብዛት ጀርመናውያን ናቸው። በኮሮና ምክንያት ሰባት የቡድኑ አባላትን ብቻ ይዞ የተጓዘውን የሰርከስ ቡድን ለማጀብ ደግሞ በርካታ ወጣት የጀርመን ተማሪዎች ከመግቢያው በር አንስቶ ሽር ጉድ ይላሉ። ኋላም ከኢትዮጵያውያኑ እንግዶቻቸው ጋር አብረው ወደ መድረክ በመውጣት የተለያዩ የኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜዎችን እና ትርዒቶችን ያሳዩ እንዲሁም እንግዶቻቸውን ያስተዋውቁ ጀመር።
ለብሩል የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች  ዕለቱን ለየት የሚያደርገው ከሰርከስ ደብረብርሃን ቡድን ጋር አብረው መድረክ ላይ መቅረባቸው ብቻ አልነበረም። በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለረዥም ጊዜ የተቋረጠው ፕሮጀክታቸው መቀጠል በመቻሉም ነው።«አዎ በርካታ ሳምንታት እና ወራት አለፉ። እረ እንደውም ፕሮጀክታችን ተገደን ከተቋረጠ አንድ ዓመት ተኩል አልፎታል። በዚህም የተነሳ ለአንድ ዓመት ተኩል  ያህል ምንም አይነት የባህል ልውውጥ ሳናደርግ ቆይተናል። አሁን እንደዚህ መገናኘት መቻላችን በጣም ደስ የሚያሰኝ ነው።» 
 «ከማክሰኞ ምሽት ጀምሮ ሰርከስ ደብረብርሃን ብሩል ከተማ በመገኘት ከእኛ ከተማሪ ቤተሰቦች ቤት በእንግድነት አርፏል። እኛም በመጨረሻ ዓለም ተመልሳ አንድ መሆን መቻሏ ተሰምቶናል። አብረን መሆን፤ አብረን ማብሰል፣ መደነስ እና አክሮባቲክ እየሠራን አዲስ እና የጋራ የሆኑ ነገሮችን እየተለዋወጥን መደሰት ጀምረናል።»
አስትሪድ ፋይፈር የዚህ መርኃ-ግብር ኃላፊ እና የተማሪዎቹ መምህር ናቸው። ሰርከስ ደብረብርሃን ወደ ትምህርት ቤታቸው ሊመጣ የቻለው (KinderKulturKarawane) በሚባል ድርጅት አማካኝነት እንደሆነ ለዶይቸ ቬለ (DW) አስረድተዋል። «ኪንደር ኩልቱር ካራቫነ መቀመጫውን ሀምቡርግ ከተማ ያደረገ ድርጅት ሲሆን በየዓመቱ ከስድስት እስከ ስምንት የሚደርሱ የጥበብ ቡድኖችን ከላቲን አሜሪካ፣ አፍሪቃ እና እስያ ይጋብዛል። በብዛት ከህፃናት አንስቶ ወጣት እና ጎልማሶችን ወደ ጀርመን በመጋበዝ እነሱም በየትምህርት ቤቱ እየተዟዟሩ ባህላዊ ግንኙነት እንዲፈጠር ይደረጋል።»  ከዚህ በፊትም በተለያዩ አጋጣሚዎች በዚህ በጀርመን ሀገር የሰርከስ ትርዒት አቅርቦ የነበረው ሰርከስ ደብረብርሃን ዘንድሮ ወደ ጀርመን እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ጎራ ያለው «ህልም አለኝ» የሚል መሪ ቃል አንግቦ ነው። 

የቡድኑ አባል የሆነችው ቤዛዊት አበበ ስታብራራ « መልዕክቱ አንዲት ሴት ልጅ እንዴት ከህልሟ መድረስ እንደምትችል ነው። ብዙ ፈተናዎችን አሳልፋ፣ አባቷ የእሷን ህልም ይቃወም ነበር። እናቷ ደግሞ አባቷ ሳያውቅ ልጃን ትደግፋታለች። እና ያንን አሳልፋ ዘፋኝ የመሆን ህልሟን ታሳካለች።» ከሌሎች ሁለት ሴቶች እና ሦስት ወንድ የሰርከስ አባላት እንዲሁም የሰርከሱ ኃላፊ ሄኖክ አሻግር ጋር በመሆን ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጀርመን የመጣችው። የ18 ዓመቷ ቤዛዊት ወደ ሰርከስ እንድትገባ የገፋፏት የዳንስ ችሎታዋን የተመለከቱት ወላጆቿ ነበሩ። « ሰርከስ መስራት ከጀመርኩ ሰባት አመት ሆነኝ። ብዙ ታሪኮችን አቅርበናል።» 
«ሰርከስ ደብረብርሃንን የሙዚቃ ባንድ እና ሰርከስ ያካተተ ነው። በሰርከሱ ውስጥ ማየት እና መስማት የተሳናቸው አካል ጉዳተኞች ይገኙበታል። እኛ የምናየው ብቃትን ነው።»  በማለት ሰርከስ ደብረብርሃንን የሚገልፀው ኢሳቅ ክበበ ሌላኛው የሰርከሱ አባል ነው። ኢሳቅ ሰርከስ መሥራት የጀመረው ገና በሰባት ዓመቱ ሲሆን፤ ሰርከስ ደብረብርሃንን ከተቀላቀለ ደግሞ ዘጠኝ ዓመት ሆነው ። የወንድሙ ሰርከስ መስራት ነበር ያበረታታው። 
የሰርከስ ደብረብርሃን ኃላፊ ሄኖክ አሻግር ሰርከሱን ከ1993 ዓ.ም አንስቶ እየመራ ይገኛል። ቡድኑ በ1989 ዓ.ም ነፃነት አሰፋ በተባለ ሰው የተመሠረተ ሲሆን፤ መስራቹም የሄኖክ ጓደኛ ነው። ሄኖክ ከዚህ ከዝግጅት በኋላ እንደገለፀልን ምንም እንኳን የቀረበላቸው መድረክ ትንሽ የነበረ ቢሆንም፤ ተስማሚ በሆነ መልኩ በማዘጋጀት ታዳሚውን እንዳስደሰቱ ያምናል። « ሰው ደስ ብሎታል። እኔም ደስ ብሎኛል» ሌላው ሄኖክን ያስደሰተው ነገር በተጓዙባቸው አካባቢዎች አልፎ አልፎ የአካባቢው ነዋሪዎች ቤት ማረፍ መቻላቸው ነው። « እሱ ራሱ ራሱን የቻለ የባህል ልውውጥ አለው,»

«በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በቤታቸው እንግዳ ተቀባይ ቤተሰቦችን ለማግኘት ትንሽ ከባድ ነበር» ያሉን መምህርት አስትሪድ ፋይፈር በመጨረሻ ግን እንግዶቹም ይሁኑ ተቀባዮቻቸው ደስተኛ ሆነው እንዳገኟቸው ይናገራሉ። «ሁሉም እንግዳ ተቀባይ ቤተሰቦች በጣም ደስተኛ ናቸው። ከሌላ ባህል ጋር ለመተዋወቅ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖ አግኝተውታል። ተማሪዎቹም በአርቲስቶቹ ላይ በመተማመን ወዲያው ነበር የተግባቡት።» ሰርከስ ደብረብርሃን እንደ ፖላንድ፤ ቡልጋሪያ እና ጀርመን የመሳሰሉ የተለያዩ  የአውሮፓ ሀገራት ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆየበትን ሰርከስ ዛሬ አጠናቆ ወደ ሀገሩ ይመለሳል። 

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

Audios and videos on the topic