ሰርቢያ ና የአውሮፓ ህብረት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 07.03.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ሰርቢያ ና የአውሮፓ ህብረት

ስርቢያ የአውሮፓ ህብረት አባል የመሆን ተሰፋዋባለፈው ሳምንት ለምልሟል ። ባለፈው ሳምንት ብራሰልስ ቤልጂየም የተካሄደው የህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች ጉባኤ ሰርቢያን ለህብረቱ አባልነት አጭቷል ።

ስርቢያ የአውሮፓ ህብረት አባል የመሆን ተሰፋዋ ባለፈው ሳምንት ለምልሟል  ። ባለፈው ሳምንት ብራሰልስ ቤልጂየም የተካሄደው የህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች ጉባኤ ሰርቢያን ለህብረቱ አባልነት አጭቷል ። የሰርቢያ የአውሮፓ ህብረት አባልነት ተስፋ ና ቀሪ ቅድመ ግዴታዎቿ የዛሬው አወሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው ።

«ለሰርቢያ የአውሮፓ ህብረት የጩ አባልነት ደረጃ ለመስጠት ዛሬ ማታ ተስማምተናል ። ይህ ታላቅ ግምት  የሚስጠው ወጤት ነው ። ቤልግሬድና ፕርስቲና ባካሄዱት ውይይት ፣ በሁለቱ ወገኖች ጥረት የተገኘ ውጤት ነው  ። »

የአውሮፓ ህብረት ፕሬዝዳንት ኽርማን ፋን ሮምፖይ ባለፈው ሳምንት ብራሰልስ ቤልጂግ ውስጥ ከተካሄደው የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ጉባኤ በኋላ ፣ ለሰርቢያ ና የህብረቱ አባልነቷ እንዲፋጠን ለሚፈልጉ ወገኖች ያበሰሩት መልካም ዜና ! ከመልካሙ ዜና በፊት ግን የሰርቢያ ዕጩነት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ወድቆ ነበር ።

ሰርቢያ በሃገርዋ በሚገኙ አናሳ ሮማንያውን ላይ የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ እንድታስወግድ ከዚህ ቀደም ከሮማንያ ጋር የተስማሙበትን ሰነድ ካልፈረመች በስተቀር ሮማንያ አባልነትዋን እንደማትቀበል ስታሳውቅ ለጊዜውም ቢሆን ተሰፋዋ ድበዝዞ ነበር ። ሆኖም ሰርቢያ ሰነዱን እንድትፈርም ከተደረገ በኋላ ጉባኤው የሰርቢያን ዕጩነት ሊያፀድቅ በቅቷል ። የአውሮፓ ህብረት ለአባልነት ያጫት የቀድሞዋ የዩጎዝላቭያ ግዛት ሰርቢያ ለህብረቱ ሙሉ አባልነት የሚያበቃት አንድ ትልቅ እርምጃ ላይ ደርሳለች ። ለዓመታት ከተካሄደ ጦርነት ና ይህም ካስክተለባት መገለል በኋላ ሃገሪቱ ለዚህ መብቃቷ በ 1990 ዎቹ በተካሄዱ ጦርነቶች ብዙ ህዝብ ባለቀበት በምዕራብ ባልካን ሀገራት ሰላም በማውረድ ረገድ  ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል ። የአውሮፓ ህብረት እንዳለው ሰርቢያ ለዕጩነት የሚያበቃትን መመዘኛዎች አሟልታ ነው ለአባልነት የታጨችው ። ሮዛ ባልፎር መቀመጫውን ብራሰልስ ቤልጂግ ያደረገው የአወሮፓ ፖሊሲ የጥናት ማዕከል ባልደረባ ናቸው ። በርሳቸው ግምገማ ከምዕራብ ባልካን ሃገራት በተሻለ +ደረጃ ላይ የምትገኘው ሰርቢያ ለአውሮፓ ህብረት አባልነት የተቀመጡትን ቅድመ ግዴታዎች የምታሟላ ሃገር ናት ።

«ክምዕራብ ባልካን ሃገራት ሰርቢያ ምናልባትም ለዚህ መዋቅራዊ ዝግጅት ያደረገች ሃገር ናት ። ከሌሎቹ ሃገራት አጅግ የተቀላጠፈ የህዝብ አሰተዳደር አላት ። ተቋማቷ ጠንካራ ና  የኮፕንሃገኑ መመዘኛዎች የሚጠይቋችውን ልዩ ልዩ ማማሻሻያዎች ተግባራዊ የማድረግ ከፍተኛ አቀምም ያላቸው ናቸው ። በተጨማሪም እነዚህን ሃገራት ወደ ዘመናዊ ዲሞክራሲ ለማሽጋገር የተቀመጡትን ብዙ ጥረት የሚያስፈልጋቸውንና ፈጣን  ማሻሻያዎችን ማካሄድ ትችላለች  ። »

የኮፕንሃገኑ መመዘኛ አንድ ሃገር የአውሮፓ ህብረት አባል ለመሆን የሚያበቃው ደንብ ነው ። በመሰፈርቱ መሠረት አባል መሆን የሚፈልግ  ሃገር ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ተግባራዊ ማድረግና ሰብዓዊ መበት ማስከበር የሚያስችሉ ተቋማት ሊኖሩት ይገባል ። የገበያ ኤኮኖሚን ማራመድ እንዲሁም የአውሮፓ ህብረትን ሃላፊነቶችና ዓላማዎችም መቀበልም ይኖርበታል ። እነዚህ የአባልነት ቅድመ ግዴታዎች እጎአ ሰኔ 1993 ኮፕንህገን ዴንማርክ ውስጥ በመደንገጋችው መስፈርቶቹ የኮፕንሃገኑ መመዘኛዎች በመባል ይጠራሉ  ።

ሰርቢያ ለአውሮፓ ህብረት አባልነት ማመልከቻ ስታስገባ ከቀረቡላት ቅድመ ግዴታዎች ውስጥ አንዱ በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የተፈፀሙ የጦር ወንጀሎቸን ለማጣራት በተቋቋመው በሄጉ ዓላም ዓቀፍ የጦር ወንጀሎች መዳኛ ፍርድ ቤት ይፈለጉ የነበሩትን 2 ቱን ቀንደኛ የጦር መሪዎች ማስረከብ ነበር ። ሰርቢያም ተፈላጊዎቹን ራዶቫን ካራቺችንና ራትኮ ምላዲችን በተከታታይ ዓመታት ይዛ አሥራ እንዳስረከበች በአውሮፓውያኑ 2011 መጨረሻ  ማለትም በታህሳስ ወር ላይ ለህብረቱ አባልነት ትታጫለች ተብሎ እየተጠበቀ ነበር ። ምንም እንኳን ሰርቢያ  በምዕራባውያን የተጠየቀችውን ሁሉ ብታሟላም የአባልነት ጥያቄዋን እስካሁን ወደ ኋላ ያጓተተባት አንዱና ዋነኛ ቸግር ገን እሳክሁንም መፍትሄ አላገኘም ። በባልፎር ግምገማ መሠረት ሰርቢያ አሁንም ግዛቴ ናት ለምትላት ለቀድሞዋ አካልዋ ለኮሶቮ እውቅና አለመስጠትዋ ትልቁ ዕንቅፋት ነው ።  በመሠረቱ ሰርቢያ ለኮሶቮ ዕውቅና እስካልሰጠች ድረስ ደግሞ የአውሮፓ ህብረት አባል መሆን አትችልም ። 

የአውሮፓ ህብረት ይህን ጉዳይ አንስቶ አሁን  በቀጥታ ባያናግርም ይላሉ ባልፎር የከዚህ ቀደሙን ስህተቱን ግን መድገም አይፈለግም ። እጎአ ከ1970 ዎቹ ጀምሮ የግሪክና የቱርክ ተብለው የተከፈሉት ሁለቱ ቆጵሮሶች ያቀረቡት የውህደት ጥያቄ መፍትሄ ሳያገኝ  ነበር ፣ ህብረቱ እጎአ  በ 2004 የግሪክ ቆጵሮስን የአውሮፓ ህብረት አባል ያደረገው ። በባልፎር አምነት አሁን ይህ ዓይነቱ ሁኔታ አይደገምም ።

«የአውሮፓ ህብረት የቆጵሮስ ዓይነት ችግር ሊገጥመው አይችልም ። ሰርቢያና ኮሶቮ ልዩነቶቻቸውን እስኪፈቱና ሰርቢያም በስተመጨረሻ  ለኮሶቮ እውቅና እስክትሰጥ ድረስ የአውሮፓ ህብረት ስረቢያን አባል አያደርግም ። የአውሮፓ ህብረት ይህን በማያሻማ መንገድ በግልጽ ማለት አይችልም ።ሆኖም ሁኔታው ይሄ ነው ።»

የአውሮፓ ህብረት እጎአ በ 1999 በቀድሞዋ የሰርብ ግዛት ኮሶቮ በተካሄደው ናበመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት በጠፋበት ጦርነት ምክንያት እንዲሁም ኮሶቮ  ክ 3 ዓመት በፊት ነፃነቷን በማወጇ ሰበብ የተካረረውን የሰርቢያና የኮሶቮን ፀብ  ሲሸመግል ነው የከረመው ።  ሰርቢያ ለህብረቱ ዲሞክራሲያዊ እሴቶች ተገዥ እንድትሆን ይፈልጋል ። በአካባቢውም ዘርን መሠረት ያደረገ ግጭት ዳግም እንዳይቀሰቀስ ማረጋገጥ ይሻል ። እጎአ ከ 1992 እሰከ 1995 በዘለቀው በቦስኒያው ጦርነት ፣  የቦሰኒያ ሰርቦች ከሙስሊሞችና ከክሮእቶች ጋር ባካሄዱት ውጊያ ወደ 100 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ህይወት እንደጠፋ ነው የሚገመተው ።

በወቅቱ ሰርቢያ ፣ የቦስኒያ ስርቦችን በጦር መሣሪያና በገንዘብ ስትደግፍ ነበር ። የአውሮፓ ህብረት ከጓሮው የደረሰውን ይህን የባላካን ጦርነት ና እልቂት ለማሰቆም ተገቢውን ጥረት ባለማድረጉ አንደ አንድ ድከመት ይወስድብበታል ። አጎአ በ1990 ዎቹ  የያኔው የሰርቢያ መሪ ስሎቦዳን ሚሎሶቪች በክሮሺያ በቦስኒያ ና በኮሶቮ ላይ ጦርነት ሲከፍቱ ሰርቢያ ከህብረቱ ተግላ ነበር ።  በ 1999 NATO በኮሶቮው ጦርነት ጣልቃ ገብቶ በሰርቢያ ላይ የአየር ድብደባ ካካሄደ በኋላ ነበር ሁለቱ ወገኖች ለድርድር የተቀመጡት  ። ጦርነቱ ከቆመ ከአንድ አሥርት ዓመታት በኋላ ነው ህብረቱ የቀድሞዋን ዩጎዝላቪያ ግዛቶች ወደ ማህበሩ ማስገባት የጀመረው ። ስሎቬንያ ከቀደሞዋ የዩጎዝላቪያ ግዛቶች የህብረቱ አባል በመሆን የመጀመሪያዋ ሃገር ናት ። እጎአ በ 2004 ህብረቱን ተቀላቀለች ። ሌላዋ የቀድሞዋ የዩጎዝላቪያ ግዛት  ክሮኤሽያ  ደገሞ በሐምሌ 2013 የህብረቱ 28 ተኛ አባል እንደምትሆን ባለፈው ዓመት ይፋ ሆኗል ። እጎአ በ2008 ነፃንቷን ያወጀችው የቀድሞዋ የሰርቢያ ግዛት ኮሶቮም ክህብርቱ ጋር በፖለቲካና በኤኪኖሚ ይበልጥ የምትቀራረብበትን መንገድ ቀይሳለች ። ራስዋን ክሰርቢያ ለገነጠለችው ኮሶቮ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ክ 80 በላይ ሀገራት እውቅና ስጥተዋል ። ከነዚህም 22 ቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ናቸው ።  ከመካከላቸው 5 አባል ሃገራት እስካሁን የኮሶቮን መገንጥል አልተቀበሉም ።  ሰርብያ አሁንም ግዛቴ ናት ለምትላት ኮሶቮ እውቅና መሰጠቱን አጥብቃ እየተቃወመች ነው ። ሩስያም ሰርቢያን በመደገፋ የኮሶቮን ነፃነት ከሚቃወሙት ሃገሮች አንዷ ናት ። የኮሶቮ ጉዳይ የአውሮፓ ህብረት አባላትንም ለሁለት እንደከፈለ ነው ።  ያም ሆኖ ህብረቱ ሰርቢያንና ኮሶቮን በመሸምገሉ ጥረት ገፍቶ ባለቀ ሰዓት የቀረበ ገለጋይ ሃሳብ ሰርቢያ ለአውሮፓ ህብረት አባልነት እንድትታጭ መንገዱን ጠረጓል ። ይሁንና ባልፎር ፣ ሰርቢያ በኮሶቮ መገንጠል ያላት ቅሬታ ሳይፈታ ሁኔታ ባለበት ከቀጠለ ውጤቱ "አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ "ዓይነት መሆኑ አይቀርም ይላሉ 

« ጨለምተኛው ከሰተት ውይይቱ ወደ ሰመረ ግንኙነት የሚያመራ ቢሆንም  ሰርቢያ ለኮሶቮ እውቅና እንድትሰጥ የሚገፋፋ አለመሆኑ ነው ። በአካባቢው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታም አይለውጠውም ። ስለዚህ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሊገነፍል የታመቀ ሊባል የሚችል ዓይነት ውዝግብ ላይ መደረሱ አይቀርም ። ይህም በርግጥ ለአካባቢው በጣም የከፋ መዘዘዞችን  ሊያስከትል ይችላል ። እንደሚመስለኝ መዘዙ ለአውሮፓ ህብረትም ቢሆን ሊተርፍ የሚችል ነው ። »

ሰርቢያ ለአውሮፓ ህብረት አባልነት መታጨትዋ የዋነኛውን ተቃዋሚ ፓርቲ ድጋፋ ቢያገኝም ተቃዋሚም አላጣም ። ብሔረተኞች የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ቦሪስ ታዲች በምዕራባውያን የተጠየቁትን ሁሉ እሺ በማለት በተለይ በኮሶቮ ጉዳይ ላይ የተስማሙበትን ገላጋይ ሃሳብ አጥብቀው ይተቻሉ ። ታዲች ለአውሮፓ ህብረት አባልነት ሲሉ የሰርቢያን መሬት ሸጠዋል ፣ ሃገሪቱን በጥቅም ለውጠዋል በማለት እየከሰሱዋቸው ነው ። በተለይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሰርቢያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ  ፓርቲ መሪ ቮይስላቭ ኩስቱኒቻ ሰርቢያ አንዳችም የምትደሰትበት ውጤት አላገኘችም ነገሩ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ዓይነት ጨዋታ ነው ብለዋል ። በኩስቱኒቻ አባባል ሰርቢያ ለአውሮፓ ህብረት አባልነት ለመታጨት ብዙ ዋጋ ከፍላለች ፤ አሁን የሚፈነጥዘውም እንደርሳቸው ፣ ህዝቡ ወይም ስራ አጡ ሳይሆን ባለሥልጣናቱ ና ከነርሱ የተጠጋው ክፍል ብቻ ነው ። 

ለአውሮፓ ህብረት አባልነት መታጨት ወደ ህብረቱ ለመግባት የመጀመሪያው ደረጃ ነው ። ሰርቢያ ለአባልነት የሚያስፈልገውን ድርድር ለመጀመር ምናልባትም አንድ ዓመት ያህል መጠበቅ ይኖርባታል ። ድርድሩም ለዓመታት ለወስድ ይችላል ። 7.5 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ወደብ አልባዋ ሰርቢያ ባለፉት ጦሮነቶችና ማዕቀቦች ምክንያት ከባድ የኤኮኖሚ ችግሮች ከፊቱ የተጋረጡባት ሃገር ናት ። ስራ አጥነት በሰርቢያ ወደ ሃያ በመቶ ነው ቢባልም ጉዳዩን የሚያጠኑ ወገኖች ግን ከዚያም በላይ ይሆናል ሲሉ ይከራከራሉ ። ሃገሪቱ የአውሮፓ ህብረትን መቀላቀሏ ለነዚህ ችግሮቿ መፍትሄ ይሆናል የሚል ተስፋ አለ ። ሰርቢያ ወደ ህብረቱ ለመግባት የግድ ለኮሶቮ እውቅና መስጠት እንደሌለባት ፣ ለአካባቢው መረጋጋት ሲባል ግን ቤልግሬድና ፕርሽቲና ግንኙነታቸውን እንዲያሻሽሉ ነው የጠየቀው የአውሮፓ ህብረት ። እስካሁንም በህብረቱ አግባቢነት ሰርቢያና ኮሶቮ በርካታ ልዩነቶቻቸውን አጥበዋል ። ለምሳሌ ኮሶቮ በዓለም ዓቀፍ ጉባኤዎች ላይ በምን መልኩ እንደምትወከል መግባባት ላይ ደርሰዋል ። በስምምነቱ  መሠረት ፕሪሽቲና የባልካን ሃገራትን ቤልግሬድ ዕውቅና ባትሰጣትም እንድትሳተፍ መግባባት ላይ ደርሰዋል ። የድንበር አስተዳደር ጉዳዮችም ላይም ተስማምተዋል ።

ይህ ብቻ ግን በቂ አይደለም ወደፊት በሃይልና በቴሌኮምኒኬሽን ዘርፎች ባሉ ችግሮች ላይ መወያየት ይኖርባቸዋል ። በሚቀጥሉት ወራት የአውሮፓ ህብረት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚሽን  ከኮሶቮ ጋር ያላትን ግንኙነት መሻሻል አለመሻሻሉን እንዲሁም ሌሎች ማሻሻያዎችንም ይገመግማል ።ከዚህ በኋለ ነው ሰርቢያ ለህብረቱ አባልነት የሚያስፈልገውን ድርድር ለመጀመር ዝግጁ መሆንዋ የሚወሰነው ። ያም ቢሳካ እንኳን እንደ ቱርክ ካሉ ሃገራት ልምድ በመነሳት ሂደቱ በቀላሉ የሚያልቅ እንደማይሆን ነው የሚገመተው ። ከዛሬ 13 ዓመት በፊት ለህብረቱ አባልነት የታጨችው ቱርክ በተወሰኑ አባል  ሃገራት ተቃውሞ እስካሁን የአባልነት ጥያቄዋ እንደተገታ ነው ። መቄዶንያም ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ነው የምትገኘው ። የኮሶቮም ወደፊት የሚታይ ይሆናል ።

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 07.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14G4m

ተዛማጅ ዘገባዎች

 • ቀን 07.03.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14G4m