ሰርቢያና እተመሣቀለ መንትያ መንገድ ላይ ያስገባት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፧ | ዓለም | DW | 21.01.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሰርቢያና እተመሣቀለ መንትያ መንገድ ላይ ያስገባት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፧

ሰርቢያ ውስጥ ትናንት በተካሄደው 60% ህዝብ አደባባይ በወጣበት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፧ ከሰባት የማያንሱ ተወዳዳሪዎች ቢሳተፉም፧ ዋንኞቹ ተፎካካሪዎች ሁለት ናቸው፧ እነርሱም፧ አክራሪ ብሔረተኛ የሚሰኘው ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ Tomislav Nikolic እና ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከሚሰኘው፧ አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንት Boris Tadic ናቸው።

በሰርቢያው ማጣሪያ መሰል ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከሁሉም የላቀ ድምጽ ያገኙት፧ ቶሚስላቭ ኒኮሊች፧

በሰርቢያው ማጣሪያ መሰል ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከሁሉም የላቀ ድምጽ ያገኙት፧ ቶሚስላቭ ኒኮሊች፧

ኒኮሎች፧ 39.4% ታዲች ደግሞ 35.4% ድምፅ በማግኘታቸው በሁለቱ መካከል እንደገና ጥር 25 ቀን 2008 ዓ ም፧ የመጨረሻ ውድድር ይካሄዳል። ዝርዝሩን ተክሌ የኋላ...
የትናንቱ የሰርቢያ ምርጫ ሂደትና ውጤት፧ ውስጣዊና የውጭ ምክንያቶች ጫና ያሰረፉበት መሆኑ አልታበለም። በቀድሞው ግትር ሶሺያሊስት መሪዋ እስሎቦዳን ሚሎሼቪች ብልሃት በጎደለው አያያዝና፧ በምዕራባውያን መንግሥታት ተጽዕኖ የቀድሞዋ የስድስት ሶሺያሊስት ፌደራል ሪፓብሊኮች ኅብረት፧ ዩጎዝላቪያ ተገነጣጥላ የቀረችው ሰርቢያ ብቻ ናት፧ የሰርቢያ፧ የግዛት ግማድ የሆነው ኮሶቮም፧ እንዲገነጠልም ሆነ ነጻነት እንዲያውጅ፧ ከዩናይትድ እስቴትስና ከአብዛኞቹ የአውሮፓው ኅብረት አባል አገሮች፧ ድጋፍ እየተሰጠው ነው። በዚህ የኮሶቮ የመገንጠል ጥያቄ፧ በሰርቢያ የፕሬዚዳንትነት ምርጫ ዋንኞቹ ተፎካካሪዎች፧ አንድ አቋም ነው ያላቸው። መገንጠሉን የሚቃወም። በተረፈ ግን፧ ፕሬዚዳንት ታዲች፧ ሰርቢያን ከአውሮፓው ኅብረት ጋር ለማሥተሣሠር የሚከተሉትን ፈለግ እንደሚገፉበት ሲያስታውቁ፧ ኒኮሊች፧ ከሩሲያ ጋር ነው፧ የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖር የሚፈልጉት። ኒኮሊች፧ በምርጫው ዘመቻ አቋማቸውን ረገብ አድርገው ቢቀርቡም፧ የኮሶቮን መገንጠል ከሚቀበሉ አገሮች ጋር ሁሉ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት እንዲቋረጥ ከማድረግ እንደማይመለሱ ነው በይፋ ያስታወቁት።ጥር ኻያ አምስት ቀን በሚካሄደው ድጋሚ ምርጫም «አሸንፋለሁ« ሲሉ ነው በልበ-ሙሉነት የተናገሩት።
«ሰርቢያ፧ ፍላጎቴን በሚገባ መገንዘቧን አሳይታለች። ለተሟላ ድል እጅግ ተቃርበናል። ማንም አያስቆመንም። የተስተካከለ አቋም ለሚይዙት ወገኖች፧ ሰርቢያ ምንጊዜም ቀጥተኛውን መንገድ እንድምትይዝ የታወቀ ነው፧ ማንም ሊገታባትም አይችልም።«
ፕሬዚዳንት ታዲች በበኩላቸው ባሰሙት ንግግትር ላይ እንዲህ ነበረ ያሉት.....
«በሰርቢያ፧ እንደገና መንፈስን የሚያዳክም የጨለምተኛነት አመለካከት እንዲሠርጽ አልፈቅድም። የትንኮሳ መልእክትም እንዲሠራጭ አላደርግም። እ ጎ አ 1990 ኛዎቹ ዓመታት ወደነበረው ሁኔታ እንድንመለስ አልፈቅድም። እርግጥ ነው፧ ኮሶቮ የአገራችን አንድ አካል በመሆኑ፧ አንድነቱ እንደጸና እንዲቀጥል አሁንም ትግላችን ይቀጥላል። ነገር ግን፧ ወደፊትም ቢሆን ዕጣ ፈንታችን ከአውሮፓ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ይህ እንዲገታ አናደርግም።«
ትናንት በተካሄደው ማጣሪያ በመሰለው ምርጫ፧ ሁለቱ ዋንኛ ተፎካካሪዎች ያገኙት ውጤት ከታወቀ ወዲህ፧ ጥር ኻያ አምስት ቀን ለሚካሄደው ወሳኝ ዳግመኛ ውድድር፧ ዘመቻቸውን ፋታ ሳያደርጉ ቀጥለዋል። የዚህ ዘመቻቸው ዋና ዓላማ፧ ያን ያህል የጎላ የድምፅ ድጋፍ ላላገኙት እጩ ተወዳዳሪዎች ድምፅ የሰጡትን መራጮችች ለእነርሱ እንዲወግኑ ማግባባት እንደሚሆን ተመልክቷል። የመሠረተ ልማት ጉዳይ ሚንስትሩ Velimir Ilic በትናንቱ ምርጫ በሦስተኛ ደረጃ 7.9% የመራጩን ድጋፍ ማግኘታቸው ታውቋል። ለዘብ ያለ አቋም ያላቸው ዴሞክራቱ Cedomir Jovanovic 5.6% እንዲሁም፧ ሶሺያሊስቱ Milutin Mrkonjic 6% ማግኘታቸው የታወቀ ሆኗል። ከዚህ በተረፈ፧ ኀዳጣኑን ወገኖች 300,000 የሚሆኑትን በጎሣ ወገንነት ሃንጋሪያውያን፧ በዜግነት ግን ሰርቢያውያን የሆኑትን ጭምር ለማግባባት ዘመቻው መቀጠሉ ታውቋል።
በሰርቢያ፧ ከኮሶቮና ወደፊት የአውሮፓው ኅብረት አባል ለመሆን ካለ እቅድ ባሻገር፧ የኑሮ ዕድገት ጥያቄም ወሳኝነት ያለው ነው። በሰርቢያ አማካዩ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ 400 ዩውሮ በታች ማለትም ከ 585 ዶላር በታች መሆኑ ነው የሚነገረው።