1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኃይሌ ገብረስላሴ እና አግባው ሰጠኝ አነጋግረዋል

ዓርብ፣ ነሐሴ 12 2009

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኃይሌ ገብረሥላሴ ላይ የተነሱ ትችቶች፣ ተቃውሞዎች እና ድጋፎች በሳምንቱ ውስጥ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጎላ ብሎ ነበር፡፡ በቁጥጥር ስር ባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ በኢትዮጵያ እስር ቤቶች እየተፈጸሙ ነው የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም በብዙዎች ዘንድ መወያያ ሆነዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2iU5e
Bildergalerie Sportler aus Afrika - Haile Gebrselassie
ምስል Getty Images

ኃይሌ ገብረሥላሴ እና አግባው ሰጠኝ አነጋግረዋል

የብሪታንያዋ ለንደን የአልማዝ አያናን አስደማሚ የአስር ሺህ ሜትር አሯሯጥ እና ብቃት በድጋሚ መሰከረች፡፡ የአልማዝ ድል በተመዘገበ በሳምንቱ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ወርቅ በሙክታር ኢድሪስ አገኘች፡፡ ሙክታር ማንም አያቆመውም የተባለለትን ብሪታንያውዊውን ሞ ፋራህን በመሰናበቻ ውድድሩ ላይ ጉድ ሰራው፡፡ ድሉ ያልተጠበቀ ነበርና የኢትዮጵያውያን ደስታ ጣራ ነካ፡፡ ማህበራዊ ድረ ገጾች በሙክታር ፎቶዎች ተጥለቀለቁ፡፡ ለድሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተው ዮሚፍ ቀጀልቻም ተወደሰ፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኃይሌ ገብረስላሴ የተናገረለት “ኢትዮጵያዊ መንፈስ” ይህ ነው ተባለ፡፡ ለሀገር ጥቅም በጋራ መቆም፣ ተባብሮ መስራት እና የቡድን ሥራ ወሳኝ እንደሆነ በየፊናው ተተነተነ፡፡ እነዚህ ማብራሪያዎች ረገብ ብሎ የነበረውን የማኅበራዊ መገኛዎች ንትርክ እንደገና ቀሰቀሱት፡፡ 

16th IAAF World Athletics Championships London 2017   Yomif Kejelcha
ምስል Getty Images/D.Ramos

በኢትዮጵያውያን ማኅበራዊ መገናኛዎች ተጠቃሚዎች ዘንድ አንድ አጀንዳ መርጦ፣ ጎራ ለይቶ መወዛገብ ሳምንት ከሳምንት የሚታይ ሁነት ከሆነ ሰንብቷል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ማጠንጠኛው የዘውግ ማንነት እና ፖለቲካ ይሆናል፡፡ የለንደኑ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ከተቃረበ ወዲህ ብቅ ጥልቅ እያለ መወያያ ሆኖ የቆየው የኃይሌ ገብረ ሥላሴ ጉዳይም ከዚሁ ጋር ተያይዟል፡፡ የነገሩ መነሻ ኃይሌ የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ቡድንን ለመሸኘት ሰኔ 23 ቀን 2009 ዓ.ም በተዘጋጀ ስነ ስርዓት ላይ ባለቀለም እርሳሶችን ምሳሌ በማድረግ የተናገረው ንግግር ነው፡፡

“አያችሁ ሁልጊዜ አንድ ላይ ስንሆን ውበት ነን፡፡ አንድ ላይ ስንሆን ጠንካራ ነን፡፡ አንድ ላይ ስንሆን ማንም አይሰብረንም፡፡ ለብቻ ስትሆኑ ግን ይቺ ቀጭኗ ትሰብራችኋለች፡፡ በቃ! አለቀላችሁ፡፡ አያችሁ እዚህ መሬት ላይ ከማሳዘናቸው ማስጠላታቸው፡፡ በቃ! ጥቅምም አይሰጡም፡፡ ይህ ማለት ለየብቻችሁ ስትሄዱ እናንተ ናችሁ፡፡ ይሄ ማለት እርሱ እዚያ ሀገር ነው፣ አርሱ እዚህ ጋር ነው ስትሉ ቀለማችሁም አያምርም፡፡ ለየብቻችሁ አንዱ አረንጓዴ ሊወድ ይችላል፣ አንዱ ቀይ ሊወድ ይችላል፡፡ በቃ!፡፡ በኅብረት ስትሆኑ ግን ታምራላችሁ፡፡ ሥዕልም ሥዕል የሚሆነው በኅብረታዊ ቀለም ሲመጣ ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ቡድን የምንለፈልፈው ነው፡፡ ወደ ሀገርም ከፈለጋችሁ ቀይሩት፡፡ ስለዚህ አትነጣጠሉ፡፡ ለየብቻ አትሁኑ፡፡ ለየብቻ ከሆናችሁ ደካማው ሰው ይሰብራችኋል፡፡ ደካማው ያሸንፋችኋል፡፡”

ይህ የኃይሌ ንግግር እና በዚያው ሰሞን የሰጣቸው አስተያየቶች “የዘውግ ማንነት ሊከበር ይገባል” በሚሉት ዘንድ ከፍተኛ ትችቶች አስከትሎበታል፡፡ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መገለጫ እንጂ “የኢትዮጵያዊነት መንፈስ” በሚል የብሔር ማንነቶች ሊጨፈለቁ አይገባም ሲሉ ሞግተዋል፡፡ ሁለት ሳምንት የተሻገረውን የሰሞኑን ውዝግብ ይበልጥ ያጋጋለው ግን ኃይሌ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት ስልጣኑን በገዛ ፍቃዱ የማይለቅ ከሆነ የአድማ እርምጃ እንደሚወሰድበት የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ከተሰራጨ በኋላ ነበር፡፡ የኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተደጋጋሚ ደርሰውበኛል ያላቸውን በደሎች የገለጸበት ደብዳቤም በማስረጃነት ሲቀርብ ተስተውሏል፡፡

ይህንን ተከትሎ በርካቶች ሀሳባቸውን በድጋፍ እና በተቃውሞ ገልጸዋል፡፡ ለኃይሌ ተቆርቋሪነት ካሳዩት መሀል አንዱ ዳዊት ተስፋዬ ነው፡፡ “ከልጅነት እስከ ዕውቀታችን፤ ልክ አንገታችንን ልንደፋ ስንል፤ ልክ በቃ የኛ ፀሐይ ጠልቃለች ልንል ስንል፤ ወረኛውን፣ አልኩ-ባዩን፣ አላጋጩን፣ ፌዘኛውን፣ ዘረኛውን፣ ጎጠኛውን፣ ጎሰኛውን፣ ከፋፋዩን፣ ሴረኛውን፣ ምቀኛውን፣ ሸረኛውን...አፍ የሚያዘጋ አንድ ብቻ ጀግና ሰው አለ፤ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ይባላል!” ሲል ማክሰኞ ዕለት በፌስ ቡክ ገጹ ጽፏል፡፡

Spanien Äthiopien Haile Gebrselassie
ምስል picture-alliance/epa/J. L. Cereijido

ሀብታሙ ስዩም በበኩሉ በፌስ ቡክ ተከታዩን ብሏል፡፡ “የኃይሌ ጥፋቱ ደጋግሞ ‘የኢትዮጵያዊነት መንፈስ’ ወደ አትሌቲክሱ ሰፈር እንዲመጣ መጣሩ ነው፡፡ የብሔር ጉዳይን በማፋፋም ኑሯቸውን ለመሰረቱ ወገኖች የኃይሌ የኢትዮጵያዊነት ስሜትን የማደስ ዘመቻ የገቢ ምንጭን በኮንክሪት እንደመድፈን ነው፡፡ እናም በአጠገባቸው ሳያልፍ ልቤን ልቤን ብለው መንፈራፈራቸው መጭውን ዘመን ከመፍራት የመነጨ ነው- ለዚያ ነው ወቅታዊ ብቃትን በሚፈልገው የአትሌቲክስ ተሳታፊዎች አመራረጥ፣ ጥብቅ ስነምግባር በሚፈልገው የአሰልጣኝ እና ሰልጣኝ ግንኙነት መሃል ሽብልቅ ሆነው የሚገቡት፡፡ ኃይሌ የኢትዮጵያዊነት ምልክት ነው” ሲል ሀብታሙ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡      

መለሰ ድሪብሳ በኃይሌ ተቀነቀነ የተባለለትን “ኢትዮጵያዊነት መንፈስ”ን በተመለከተ ሦስት ነጥቦች በማንሳት ተችቷል፡፡ “አንደኛ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በራሱ የጠፋው አንዱ በስመ የኢትዮጵያዊነት ተቆርቋሪነት፣ የኢትዮጵያዊነት ሰጪና ነሺ ሆኖ ከመንፈሱ ገፊ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛ የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ መንፈሱን በማናፈስ አይደለም የምታሰርፀው፡፡ ኢትዮጵያዊነት እንዲሰማው በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የሚያኮራውና የሚደሰትበት ነገር አንዲኖር በማድረግ ነው፡፡ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ጭቆናን እንጂ ምንም ላላየው ህዝብ ሺህ ጊዜ ኢትዮጵያዊነት ብለህ ብትለፍፍበት ጉዳዩም አይሆንም፡፡ ሶስተኛ አሁን የኢትዮጵያዊነት ስሜት ያጎለበታችሁ መስሏችሁ አላስፈላጊ መንገድ እየሄዳችሁ፤ ጉዳት ያለው ስልት እየተጠቀማችሁ፤ ጠፋ፣ የለም፣ ተዳከመ ወዘተ የሚባለው ‘የኢትዮጵያዊነት መንፈስ’ ይባሱኑ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጠላ እያደረጋችሁ መሆኑን ማን በነገራችሁ” ሲል ትችቱን አሰፍሯል፡፡

አባቡ ረሺድ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ኃይሌ ከፌደሬሽን ይልቀቅ ከተባለም እርሱን መተካት ያለባቸው ባለሙያዎች መሆን አለባቸው ይላሉ፡፡ “የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በአዲስ መልኩ በሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ በአትሌት ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ማርያም ሲያዝ፣ ከተደሰቱት ውስጥ ነኝ። በእነዚህ አትሌቶች የስልጣን ዘመን ምንም ውጤት ባይገኝ ፌዴሬሽኑ ባይሻሻል እንኳን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የፖለቲከኞች መቀለጃ አሊያም መጫወቻ እንዲሆን አልመኝም። በምንም መልኩ፣ በምንም ተዓምር ጉዳዩ የማይመለከታቸው ስለ ስፖርት ምንም ዕውቀቱ እና ግንዛቤው የሌላቸው እነዚያ ፖለቲከኞች ተመልሰው ወደ ፌዴሬሽኑ እንዲመጡ አልመኝም። እነ ኃይሌ ባይሆንላቸው ሌሎች አትሌቶች እና አሰልጣኞች ናቸው መተካት ያለባቸው።”

Amnesty International - Welcome to hell fire
ምስል Chijioke Ugwu Clement

ወደ ሁለተኛው ርዕሰ ጉዳያችን ተሻግረናል፡፡ በኢትዮጵያ በእስር ቤቶች ስለሚፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተደጋጋሚ ዘገባዎች አውጥተዋል፡፡ እውቅ የሆኑ የፖለቲካ ሰዎች፣ ጋዜጠኞች እና ባለስልጣናት ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የሚያሰሟቸው እሮሮዎችም በእስር ቤቶች ስላለው አያያዝ ተጨማሪ ማስረጃዎች ሆነው ይቀርቡ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ህዝብ ዘንድ ያልደረሱ የበርካታ ታሳሪዎች ችግሮች ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በመጠቀም ለአደባባይ እየበቁ ነዉ፡፡ 

የሰማያዊ ፓርቲ ምክር ቤት አባል የሆኑት እና አሁን በቂሊንጦ በእስር ላይ ያሉት የአቶ አግባው ሰጠኝ ጉዳይ የሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ በሽብር ወንጀል ተከስሰው የነበሩት አቶ አግባው ከክሱ ነጻ ቢባሉም በቂሊንጦ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ በድጋሚ በሽብር ተከስሰው ጉዳያቸው እየታየ ነዉ፡፡ ሰኞ ነሐሴ 8 ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርበው የተናገሩትን ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በፌስ ቡክ ገጹ አጋርቷል፡፡ “ጎንደር ላይ ሰው ሲሞት እኔ ላይ ነው በቀል የሚፈጽሙት፡፡ ከደበደቡኝ በኋላ ይቅርታ ብለው ዞን ሁለት ካሉ እስረኞች ጋር ቀላቅለውኛል፡፡ ይህም ከበስተጀርባው አላማ አለው፡፡ አሁንም ለህይወቴ ዋስትና የለኝም፤” ሲሉ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሰዎች የሚደርስባቸውን በደል መናገራቸውን ጽፏል፡፡ በቂሊንጦ የማረሚያ ቤት የጥበቃና ደህንነት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ዋና ሱፐር ኢንቴንደት ገብረ እግዚያብሔር ገብረ ሐዋርያት በደብዳቤ ያቀረቡትን ማስተባበያ ቅጂም አያይዟል፡፡

በቅርቡ ከእስር የተፈታው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩም በቂሊንጦ በነበረበት ወቅት አግባው በከባድ ድብደባ ምክንያት የደረሰበትን ጉዳት እንዳሳየው በፌስ ቡክ ጽሁፉ ገልጿል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየተቻውን ካጋሩት መካከል ሰለሞን መንገሻ ‪“አንዳንዴ የአቅመ ቢስነት ስሜት ጠፍንጎ ይይዘኛል፡፡ ብዙ በደሎችን ሰምቼ ምንም ሳልል አልፋለሁ፡፡ ‬ያሳፍረኛል፡፡ ‬አንገታቸው ላይ ሜዳሊያ ሊጠለቅላቸው የሚገባ ሰዎች ሁላ እጃቸው በካቴና ታስሮ ሳይ ያመኛል፡፡ ‬‬የምንፋረድበት ቀን ይመጣል! ፅናቱን ይስጥህ አግባው ሰጠኝ! መልካም ልደት ጋሽ በቄ፤” ሲል በዚህ ሳምንት የልደት በዓላቸውን ያከበሩትን የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባን ደርቦ አስታውሷል፡፡መንበረ ካሳዬ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ “የአግባው ሰጠኝ ጉዳይ እጅግ በጣም አሣሣቢ ነው” በሚል ርዕስ ተከታዩን በፌስ ቡክ አስፍረዋል፡፡ “አግባው የደረሰበት በደል ወይንም መደብደቡን ለማመን ምንም ማስረጃ አያስፈልግም። እስር ቤቶቹ ሲኦል ናቸው። የሰው ልጅ ላይ አለ የለም የሚባል በደል የሚፈፀምባቸው። እስር ቤቱ ‘ከአቅም በላይ ሆኖብኛል፤ አልቻልኩትም’ ሲል ከዛ ቦታ ወዴት እንዲተላለፍለት ፈልጎ ነው? አንድ ቀን አግባው ሰጠኝ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ተብሎ እስር ቤቱ አግባው ሰጠኝ የሚባል እስረኛ የለም ብሎ መልስ እንዳይሰጥ እሰጋለሁ፤” ብለዋል፡፡     
በቀለ ደገፋ በፌስ ቡክ ገጻቸው “ ‘የደርግ ባለስልጣናትን ላደረጉት ግፍና ጭቆና ለፍርድ አቅርቤያለሁ’ ብሎ የሚኩራራ ቡድን ይህን ዘግናኝ ግፍ ሲፈጽም ማየት ምን ይሉታል። ነግ በእኔም አለ” ሲል የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት የተባለ ድርጅት ሰሞኑን በአግባው ዙሪያ ያሰራጨውን ሥዕላዊ መረጃ አጋርቷል፡፡ ድርጅቱ በእስር ላይ የምትገኘውን የፖለቲካ አራማጅ ንግስት ይርጋን አስመልክቶ በዚህ ሳምንት ለዕይታ ያበቃው አጭር የአኒሜሽን ቪዲዮም ብዙዎች ተቀባብለውታል፡፡  

Folter Asien Symbolbild
ምስል AFP/Getty Images

 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ