ሰሜን ኮርያ እና ዩኤስ አሜሪካ | ዓለም | DW | 14.02.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሰሜን ኮርያ እና ዩኤስ አሜሪካ

ከሁለቱ የኮርያ መንግሥታት ጎን፡ ዩኤስ አሜሪካ፡ ቻይና፡ ጃፓንና ሩስያ በፔኪንግ ባካሄዱት ድርድር ላይ ትናንት አንድ ስምምነት ተደርሶዋል።

የስድስቱ መንግሥታት ተደራዳሪዎች

የስድስቱ መንግሥታት ተደራዳሪዎች

ይህ ስምምነት የአቶም ጦር መሣሪያ ባለቤት የምትሆን ሰሜን ኮርያ በሩቅ ምሥራቅ ውስጥ የጦሩን መሣሪያ እሽቅድምድም የምታነቃቃበትን ሥጋት በርግጥ አስወግዶ ይሆን በሚል ጥያቄ ሲቀርብ ተሰምቶዋል። ሥጋቱ ግን ገና አለመወገዱ ነው የተገለፀው። ከሰሜን ኮርያ ጋር የተደረሰውን ስምምነት በተመለከተ የዩኤስ አሜሪካ ባለሥልጣናት የተለያየውን አስተያየት ሰንዝረዋል።
በስምምነቱ መሠረት፡ ሰሜን ኮርያ በዮንግቢዮንግ የሚገኘውን የኑክልየር ተቋም ሥራን ለማቆም ዝግጁነትዋን ገልፃለች። ዓለም አቀፉ የአቶም ኃይል ተቆጣጣሪ ድርጅትም ይህንን መቆጣጠር ይኖርበታል። ከጥቂት ጊዜ በኋላም፡ ሰሜን ኮርያ በሀገርዋ ያሉትን የአኑክልየር ተቋሞች በጠቅላላ መዝጋት ይኖርባታል። በማካካሻም የመገለል ዕጣ የገጠመው የፒዮንግያንግ መንግሥት ከዩኤስ አሜሪካ ጋር ቀጥተኛ ድርድር የሚጀምርበት ዕድል ይከፈትለታል፤ የሀገሩ ስምም ዩኤስ አሜሪካ ሽብርተኝነትን ይደግፋሉ በሚል ካወጣችው የሀገሮች ዝርዝር ይሰረዝለታል። ከዚህ በተጨማሪም፡ ሀምሳ ሺህ ቶን ዘይትና የምግብ ርዳታ ይቀርብለታል። ከብዙ ድርድር በኋላ አሁን የተደረሰው ስምምነት አዎንታዊ መሆኑን የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ጆርጅ ዳብልዩ ቡሽ በቃል አቀባያቸው ቶኒ ስኖው አማካይነት ባስተላለፉት መልዕክት ገልፀዋል።
« ስምምነቱ በመደረሱ ተደስቼአለሁ። የስድስቱ መንግሥታት ውይይት፡ ስለ ሰሜን ኮርያ የኑክልየር መርሀ ግብር በዲፕሎማቲካዊ መንገድ ለመምከር የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ከመሆኑም ሌላ፡ ከአቶም የጦር መሣሪያ ነፃ የሆነ የኮርያ ልሳነ ምድር ለመፍጠር ያለውን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ወገኖች የጋራ ጥቅም የሚያሳይ ነው። »
ይሁንና፡ በተመድ የቀድሞው የዩኤስ አምባሳደር ጆን ቦልተን በስምምነቱ አኳያ ጠንካራ ሂስ ነው የሰነዘሩት።
« ስምምነቱ ሰሜን ኮርያ ላሳየችው ንዑሱ ዝግጁነት ግዙፍ የኤኮኖሚ ርዳታ የሚያቀርብ ነው። »
በጆን ቦልተን አንፃር አሜሪካዊትዋ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኮንዶሊሳ ራይስ ለሰሜን ኮርያ የሚሰጠው ርዳታ የተጋነነ አለመሆኑን ገልፀዋል። በዩኤስ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የኑክልየር ጉዳይ ተጠሪ ክርስቶፈር ሂል ደግሞ የሰሜን ኮርያ ርምጃ መልካም መሆኑን በማመልከት፡ በዚህ ማቆም እንደሌለበት አሳስበዋል።
« ይህ ጥሩ የመጀመሪያ ርምጃ ነው። ግን ሌሎች መከተል ይኖርባቸዋል። »
ምንም እንኳን ትናንት በተደረሰው ስምምነት ባይጠቀስም፡ ሰሜን ኮርያ ያሉዋትን የአቶም የጦር አረሮችን በጠቅላላ እንድትደመስስና የኑክልየር ተቋሞችዋንም እንድትዘጋ የዩኤስ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ፍላጎት መሆኑን ራይስ በመግለፅ፡ ይህ እንደ ሁነኛ ርምጃ ሊታይላት እንደሚችል አስታውቀዋል። ይሁንና፡ ይኸው የራይስ አነጋገር ኢራንን ለመሳሰሉ ሀገሮች የተሳሳተ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ነው ጆን ቦልተን የገለፁት።
« ይህ፡ በዓለም የአቶም ጦር መሣሪያ ለማስፋፋት ለሚሹት ሁሉ የተሳሳተውን መልዕክት ያስተላላፋል። ብዙ ከጠበቁና የውእጭ ጉዳይ ሚንስቴር ተደራዳሪዎችን በድርድር ካደከሙ ጥሩ ማካካሻ እንደሚያገኙ ነው የሚጠቁመው። »
ይሁን እንጂ፡ በፔኪንግ የተካሄደው የስድስት መንግሥታት ድርድር ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ያካባቢ ሀገሮች አወያይቶ ውጤት ሊያስገኝ የቻለበት ድርጊት ከኢራን ጋር ለተጀመረውና እክል ለገጠመው ድርድር አበረታቺ ምሳሌ እንደሚሆን ነው አሜሪካውያኑ የሚያምኑት።