ሰሜን ኮሪያ የቦምብ ሙከራዋ «ስኬታማ ነበር» አለች | ዓለም | DW | 03.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሰሜን ኮሪያ የቦምብ ሙከራዋ «ስኬታማ ነበር» አለች

ዓለም በሰሜን ኮሪያ የሐይድሮጅን ቦምብ ሙከራ ጭንቅ ጥብብ ብሏት ውላለች። የሰሜን ኮሪያ ዜና አገልግሎት በአኅጉር አቋራጭ ሚሳይል ላይ ሊጠመድ የሚችል የሐይድሮጅን ቦምብ ሙከራው "ስኬታማ ነበር" ሲል ዘግቧል።

ከጃፓን እስከ አሜሪካ ከበርሊን እስከ ፓሪስ የሙከራው ዜና ሲወገዝ ውሏል።  የተለያዩ የሥነ-ምድር ምርምር ማዕከላትም  በሰሜን ምሥራቅ ሰሜን ኮሪያ ሰው ሰራሽ የምድር መንቀጥቀጥ መፈጠሩን መመዝገባቸውን ገልጠዋል።የደቡብ ኮሪያ ጦር ሙከራውን እየመረመርኩ ነው ሲል ጃፓን በበኩሏ የኪም ጆንግ ኡን ሀገር ሙከራውን ለማድረጓ እርግጠኛ ነኝ ብላለች።

የአሜሪካ የሥነ-ምድር ጥናት ማዕከል ሰሜን ኮሪያ ከዚህ ቀደም የኑክሌር ፍንዳታ ባካሔደችበት ቦታ አቅራቢያ በሬክተር ስኬር መለኪያ 6.3 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን ገልጧል። ሰሜን ኮሪያ አደረኩት ካለችው የሐይድሮጅን ቦምብ ሙከራ በኋላ የቀጠናውን አገራት ጨምሮ ዩናይትድ ስቴትስ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሥጋት ተጭኗቸዋል።የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒሥትር ሺንዞ አቤ የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታ መርኃ-ግብር ከባድ እና አስቸኳይ ሥጋት ፈጥሯል ብለዋል። የሰሜን ኮሪያ የአሁኑ ሙከራ በጃፓን ሰማይ ላይ ሚሳይል ከተኮሰች ከጥቂት ቀናት በኋላ የተደረገ ነው።

የጀርመኗ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል እና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳን ኤማኑዌል ማክሮ ሙከራውን በፅኑ ኮንነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስቸኳይ እርምጃ እንሲወስድ ጥሪ አቅርበዋል። ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ተቆጣጣሪ ድርጅት በበኩሉ የሰሜን ኮሪያን ሙከራ "የሚያሳዝን ድርጊት" ብሎታል። ሁሉም ወገኖች እንዲረጋጉ ጥሪ ያቀረበችው ሩሲያ ቀውሱን ለመፍታት ሁነኛው መንገድ መነጋገር ብቻ ነው ብላለች። ቻይና የንግድ ሸሪኳ የተሳሳተ እርምጃዋን እንድታቆም ጥሪ አቅርባለች። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ማኅበራዊ ድረ-ገፃቸው ባሰፈሯቸው ተከታታይ መልዕክቶች ሰሜን ኮሪያ በቃላትም ይሁን በድርጊቷ ጠብ ጫሪነቷን ቀጥላለች ሲሉ ወቅሰዋል።  

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ