ሰላም ያጣችው ደቡብ ሱዳን | አፍሪቃ | DW | 27.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ሰላም ያጣችው ደቡብ ሱዳን

ደቡብ ሱዳን እአአ በ2011 ዓም ከሱዳን ተገንጥላ ነፃ መንግሥት ካቋቋመች ወዲህ ሰላም እና መረጋጋት አልሰፈነባትም። እንደሚታወቀው ደቡብ ሱዳን አዲስ ቀውስ ውስጥ የወደቀችው በፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና ከሥልጣን ካባረሩዋቸው የቀድሞው ምክትላቸው ሪየክ ማቸር መካከል የሥልጣን ሽኩቻ በተነሳበት እአአ ታህሳስ 2013 ዓም ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:36
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:36 ደቂቃ

ሰላም ያጣችው ደቡብ ሱዳን

ለውዝግቡ ገላጋይ ሀሳብ በጠፋበት ባሁኑ ጊዜ ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች በተለይ በአፐር ናይል እና በዩኒቲ ክፍለ ግዛቶች ውጊያውን ቀጥለዋል።

የደቡብ ሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናት እና ከጦር ኃይሉ በከዱ መኮንኖች ከጥቂት ጊዜ በፊት ያቋቋሙት ቡድን ዓማፅያን በሁለቱ ነዳጅ ዘይት አምራች ግዛቶች ውጊያው ተጠናክሮ በመካሄድ ላይ መሆኑን አረጋግጠዋል። በመዲናይቱ ጁባ የሚገኘው የደቡብ ሱዳን መንግሥት የማስታወቂያ ሚንስትር ማይኮ ማክዌልዌይስ በአፕር ናይል ዋና ከተማ ማላካል የሚገን አንድ የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ ተቋም አሁን እስከ ቅርብ ጊዜ በፊት ድረስ በሀገሪቱ ጦር ያገለግሉ በነበሩት ሜጀር ጀነራል ጆንሰን ኦሎኝ በሚመሩ ዓማፅያን ቁጥጥር መዋሉን አስታውቀዋል። ይሁንና፣ በዚሁ ጊዜ የመንግሥቱ ጦር በዩኒቲ ግዛት የሚገኙትን የነዳጅ ዘይት አምራች ከተሞችን ሌር እና ፓሉዎጅን ከዓማፅያኑ ቁጥጥር የማስለቀቅ ድል ማስመዝገቡን እንደተሳካለት ማክዌልዌይስ አክለው ገልጸዋል።

« ማላካል በወቅቱ በዓማፅያኑ ቁጥጥር ነው የምትገኘው። በከተማይቱ ዙርያ ውጊያውም አሁንም እንደቀጠለ ነው። የመንግሥቱ ጦር ከተማይቱን መልሶ ለመያዝ ዘመቻውን አጠናክሮዋል። ዓማፅያኑ በበኩላቸው በመንግሥቱ ጦር እጅ ስር የምትገኘውን የማሉድን ከተማ ለመያዝ እና የጥቃት ተግባራቸውን ለማስፋፋት በመሞከር ላይ ናቸው። ሆኖም፣ የመንግሥቱ ጦር ኃይላት ራሳቸውን መከላከላቸውን እና ዓማፅያኑንንም ከዩኒቲ ግዛት በጠቅላላ ነፃ አድርገዋል። የአፐር ናይልን ግዛት በሚመለከት ዓማፅያኑን በመከታተል ጥቃታቸውን በተቻለ ፍጥነት እናዳክማለን። ዓማፅያኑ ከሱዳን መንግሥት ግልጽ ድጋፍ በማግኘትም ላይ ናቸው። »

ይሁንና፣ በሜጀር ጀነራል ጆንሰን ኦሎኝ የሚመሩት ዓማፅያን ፕሬዚደንት ኦማር ኤል በሺር ከሚመሩት የሱዳን መንግሥት የጦር ድጋፍ ያገኛሉ መባሉን ሀሰት ሲሉ አስተባብለዋል። አዲሱ ያማፅያን ቡድን የማላካል ከተማን መያዙን ሜጀር ጀነራል ሎኝ እና ከቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ሪየክ ማቸር እና ከ«ኤስ ፒ ኤል ኤ» ምሥራች ጆን ጋራንግ ልጅ ማቢዮር ጋራንግ ጋር ጉድኝት የፈጠረው ራሱን ፀረ ደቡብ ሱዳን መንግሥት ጦር ወይም በተቃውሞ ላይ ያለው «ኤስ ፒ ኤል ኤም» ብሎ የሚጠራው ቡድን ቃል አቀባይ ካነሎት ሎኝ ሙልዴንግ አረጋግጠዋል።

« የነዳጅ ዘይቱን ንጣፍ በጠቅላላ ተቆጣጥረናል። ከሰሜን ሱዳን የጦር ድጋፍ አግኝተን ቢሆን ኖሮ፣ መዲናይቱን ጁባ በሀያ አንድ ቀናት ውስጥ መያዝ በቻልን ነበር። ምክንያቱም ቦታው አስተማማኝ ነው፣ የተቋማቱን ስራ ያስተጓጎለ ችግርም አላጋጠመም። »

በአፐር ናይል ያካሁዱት ውጊያ የተሳካ እንደነበር ነው የአዲሱ የደቡብ ሱዳን ዓማፅያን ቡድን ቃል አቀባይ ብርጋዲየር ጀነራል ኒያጓል አጃክ ዴንግ የገለጹት።፣

« ማላካልን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረናል። የመንግሥቱን ጦር ከከተማይቱ አባረናል። በቦታው አለመኖራቸውን ነው ያየማረጋግጥላችሁ። »

በነዳጅ ዘይት አማራጮቹ የአፐር ናይል እና በዩኒቲ የቀጠለው ውጊያ ባካባቢው ነዋሪዎች እና በተልዕኮው አባላት ተግባር ላይ አሳሳቢ መዘዝ ማስከተሉን በደቡብ ሱዳን የተሰማራው የተመድ ተልዕኮ ኢሌን ማርጋሬት ሎይስ ገልጸዋል።

« በመንግሥቱ ጦር እና በቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር ሪየክ ማቸር ታማኝ ኃይላት መካከል በቀጠለው ውጊያ ሲቭሉ ህዝብ እየተገደለ ነው። ከመኖሪያ ቀያቸው እየተፈናቀሉም ነው። እኛም ባካባቢው በነፃ መዘዋወር ባለመቻላችን ችግር አጋጥሞናል። የሰላሙ ውል ባፋጣኝ መደረስ አለበት። እና የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ባለው አቅም ሁሉ በመጠቀም ተቀናቃኞቹ ወገኖች አንድ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የተጀመረውን የሰላም ድርድር ውጤት እንዲቀበሉ አስፈላጊውን ተፅዕኖ እንዲያሳርፍ ጠይቀናል። »

እንደሚታወሰው፣ በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን፣ በምህፃሩ በኢጋድ ሸምጋይነት ከበርካታ ወራት በፊት በተደጋጋሚ በአዲስ አበባ በተደረጉት ድርድሮች የተዘጋጀውን የሰላም ስምምነት ሳይፈርሙ ቀርተዋል።

የሰላም ስምምነት እስካልተደረሰ ድረስም የሲብሉ ሕዝብ ስቃይና ሞት መቀጠሉ እንደማይቀር የገለጹት ባካባቢው የሚንቀሳቀሰው ድንበር የማይገድበው የሀኪሞች ድርጅት ባልደረቦች ከውጊያው ለማምለጥ ከህሙማኑ ጋ በ መገደዳቸውን ነው ያመለከቱት። የደቡብ ሱዳን የርስበርስ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ያጠፋ ሲሆን፣ 2,5 ሚልዮን ሰዎችን በርዳታ ላይ ጥገኛ ማድረጉን የተመ የሕፃናት መርጃ ድርጅት የምሥራቃዊ እና ደቡባዊ አፍሪቃ የመገናኛ ክፍል ኃላፊ ጄምስ ኤልደር ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል።

« የደቡብ ሱዳን ጊዚያዊ ሁኔታ ከገመትነው በላይ እየከፋ ሄዷል። ሁለቱም ተቀናቃኝ ወገኖች የዝናቡ ወራት ከመጀመሩ በፊት ሰፊ አካባቢ ለመቆጣጠር በየበኩላቸው ጥቃታቸውን አጠናክረዋል። የሚያሳዝነው፣ አሸናፊ በሌለበት በዚሁ ውጊያ በተለይ በህፃናት ላይ ግድያ፣ የክብረ ንጽህና መድፈር እና እገታን የመሳሰለ የኃይል ተግባር እየተፈፀመ መሆኑን የሚያመለክቱ አሳዛኝ ዘጋባዎች ደርሰውናል። የደቡብ ሱዳን ህፃናት በወቅቱ የሚገኙበት ይህን ይመስላል። »

የሰብዓዊ ርዳታ ሰጪ ድርጅቶች እንደሚታወቀው አንዳንድ ሰራተኞቻቸው ከተገደሉባቸው በኋላ አካባቢውን ለቀው መውጣታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከአንዳንድ አቅጣጫ ወቀሳ ማሰንዘሩ አልቀረም፣ የተመድ ባለሥልጣን ግን ርምጃው ትክክለኛ መሆኑን ነው ያስረዱት።

« እንደ ማንኛውም ግብረ ሠናይ ድርጅት የፀጥታ ጥንቃቄዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል። የሰራተኞቹን ደህንነት ማስጠበቅ የመጀመሪያ ኃላፊነቱ ነው። ሁኔታው ተለዋዋጭ ነው። እና ተፋላሚዎቹ ወገኖች የሰብዓዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ለማክበር ዝግጁ ካልሆኑ እና ለሲቭሉ ሕይወትም ክብር ካልሰጡ ወደ አስተማማኝ ቦታ ከመሄድ በስተቀር ሌላ አማራጭ የለንም። እኛ እንደ ዩኒሴፍ ሁሌ ሲቭሉ አጠገብ በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ነው የምንሰራው። ዩኒሴፍ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከሲቭሉ ሕዝብ ጋ ባደረገው ቃለ መጠይቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ህፃናት መገደላቸውን፣ ሌሎች መታገታቸውን ወይም ለውጊያ ተግባር መመልመላቸውን ለማወቅ ችሏል። ካለፉት ዓመታት ወዲህ እንደምንሰማው በዓለማችን ውስጥ በህፃናት ላይ እጅግ አስከፊ በደል እየተፈፀመ ነው። ይህ ቃለ መጠይቅ የህፃናቱ ችግርን ምን እንደሚመስል በግልጽ እንድንረዳው ጠቅሞናል። »

Das Logo und der Schriftzug der Hilfsorganisation UNICEF sind am 5. Februar 2008 an der Zentrale in Koeln zu sehen.

ጄምስ ኤልደር አንዲት ጥቃት የደረሰባቸውን እና ሁለት መንታ ወንዶች ልጆቻቸውን ከእገታ ያዳኑ ናታሻ የተባሉ እናት ጠቅሰው እንደገለጹት፣ ወይዘሮዋ ከአጥቂዎቻቸው ማምለጥ ቢሳካላቸውም በመንደራቸው የነበሩ ብዙ ወጣቶች እና ወንዶች የመገደል እጣ ገጥሟቸዋል። እርሳቸውና ሌሎች ከጥቃቱ የተረፉት የመንደራቸው ሰዎችም በወቅቱ በህልውና ለመቆየት በመጣጣር ላይ ይገኛሉ። የሲቭሉ ሕዝብ ህልውና በተፋላሚ ወገኖች ርምጃ ላይ ጥገኛ መሆኑን ሊረዱት እንደሚገባ የዩኒሴፍ ባለሥልጣን ጄምስ ኤልደር አሳስበዋል።

« ተቀናቃኞቹ ወገኖች ሲቭሉን ሕዝባቸውን ደህንነት ለመከላከል ብዙ ሊሰሩ ይገባል። ለዚህ ውዝግባቸውም በወታደራዊ ርምጃ መፍትሔ ሊገኝ እንደማይችል ሊረዱትም ይገባል። ፊት ለፊት ተገናኝተው መወያየት እና አዲሷን ሀገራቸው ደቡብ ሱዳንን መገንባት ነው የሚጠበቅባቸው። »

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic