ሰላም የጠማት ደቡብ ሱዳን | አፍሪቃ | DW | 29.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ሰላም የጠማት ደቡብ ሱዳን

ከጎርጎሪዮሳዊዉ2011ዓ,ም ጀምሮ ደቡብ ሱዳን ዉሉ በጠፋበት የእርስ በርስ ጦርነት ዉስጥ ገብታለች። በሀገሪቱ ፕሬዝደንትና በቀድሞዉ ምክትላቸዉ መካከል የተጀመረዉ የፖለቲካ አለመግባባት የሀገሪቱን ሁለት ግዙፍ ጎሳዎች ደም ማቃባቱን ቀጥሏል።

በረደ ሲባል እየባሰ የሚሄደዉን ግጭት ጦርነት ለማስቆም የተካሄዱ ድርድሮችም ሆኑ የሽምግልና መድረኮች አልቦ ፍሬ ቀርተዋል። ሰክኖ የከረመዉ የአማፅያንና የመንግሥት ወታደሮች ጦርነትም ዳግም አንሰራርቷል።

ቤንትዊ ከ17 ወራት በፊት፤ ዩኒቲ ግዛት ዉስጥ በምዕራብ በኩል የምትገኘዉ ይህች ከተማ ተቃጠለች። በሕይወት የተረፉት የከተመዋ ኗሪዎች በሙሉ በሚባል ደረጃ የተመድ ባዘጋጀዉ የስደተኞች መጠለያ ገቡ። በጎዳናዎቿ ላይ ለቁጥር የሚያዳግት የአማፅያኑ አስከሬን ወድቋል። ወኔያቸዉ ያልነረደዉ ወታደሮች በአማፅያኑ ላይ የተቀዳጁትን ድል በተጨባጭ ሊያሳዩ ወስደዉን እኛ በደቡብ ሱዳን ጦር ክፍት ተሽከርካሪ ላይ ተቀምጠናል። ከመካከላቸዉ አንዱ ወጣት ወታደር ከእንግዲህ እዚህ የሚፈጠር ምንም ነገር አይኖርም አለን።

«አሁን ሁኔታዉ ሰላም ነዉ። ከእንግዲህ የሚፈጠር ምንም ነገር አይፈጠርም። አሁን ሲቪሎቹ ተረጋግተዉ ወደዉስጥ እንዲመለሱ እየጠበቅን ነዉ።»

Südsudan Bentiu Soldaten der SPLA

የመንግሥት ወታደሮች

ደቡብ ሱዳን ለረዥም ዓመታት ከቆየችበት የእርስ በርስ ጦርነት ከሱዳን በጎርጎሪዮሳዊዉ 2011ዓ,ም ተገንጥላ ነፃነቷን ካረጋገጠች በኋላ ያገኘችዉን ሰላም ብዙም አላጣጣመችም ተመልሳ በ2013 ታኅሳስ ወር ወደዚሁ አዙሪት ስትገባ። በወቅቱ ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ምክትላቸዉ የነበሩት ሪየክ ማቻርን መፈንቅለ መንግሥት አሲረዉብኛል በማለት ከሰዋል። ከዚህኛዉ የፖለቲካ አለመግባባት የተነሳዉ ዉዝግብም የእርስበርስ ጦርነትን ወለደ። ሀገሪቱ በሁለቱ ግዙፍ ጎሳዎች ጎራ ተከፍላለች። በፕሬዝደንቱ ዲንካ እና በአማፂዉ መሪ ኑየር ጎሳዎች።

ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ይህ የእርስበርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ለሶስተኛ ጊዜ ሰሞኑን ወደዚያዉ አመራን። ዋና ከተማ ጁባ በእነዚህ ጊዜያትም ቢሆን በመጠኑ ለዉጦች አሳይታለች። በያለበት የግንባታ ሥራ ይካሄዳል፤ አዳዲስ ሆቴሎችም ተከፍተዋል። ሆኖም ግን ታሪክ ራሱን ሊደግም ዳርዳር የሚል ይመስላል፤ በላይኛዉ የናይል እና በዩኒቲ ግዛቶች አማፅያን ተጨማሪ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል። ለጊዜዉ የመንግሥት ኃይሎች የበላይነትን የያዙ ይመስላል። የመንግሥት ጦር ቃል አቀባይ ፊልፕ አጉየር አሁን ቢያንስ አማፅያኑ ጥቃት እንደሚያደርሱ ያመኑ ይመስላል፤

«አማፅያኑ ዳግመኛ በፍፁም ጥቃት አይሰነዝሩም ማለት በጣም አስቸጋሪ ነዉ። ለበርካታ ሰዎችም የደህንነት ስጋት አለ፤ እናም አማፅያኑ አሁንም በአፐር ናይል የፀጥታ ስጋት ሊፈጥሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ማላካልን በምንም መንገድ በድጋሚ ሊይዙ አይችሉም።»

Südsudan Juba Sprecher der Regierungstruppen

ቃል አቀባይ ፊልፕ አጉዌር

በዚህ መካከልም የስቃዬ ተሸካሚ ሲቪሉ ዜጋ ነዉ። በቤንቱዊ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከ60,000 የሚበልጡ ዜጎችን ይገኛሉ። ወደመኖሪያ ቀየዉ ስለመመለስ የሚያወራ አንድም የለ። የተመድ እስከሰኔ ድረስ 4,6ሚሊዮን ደቡብ ሱዳን ዜጎች በቂ ምግብ እንደማያገኙ እየገለጸ ነዉ። ይህም ማለት ከሀገሪቱ ዜጎች 40 በመቶ የሚሆነዉ ሕዝብ ማለት ነዉ። ከአንድ ዓመት በፊት ነዉ ፊሊፕ አጉየር ሀገሪቱን የገጠማትን ችግር የመለወጥ ኃላፊነት በፖለቲከኞቿ እጅ መሆኑን የገለፁት፤ ዘንድሮም እሱኑ ነዉ የሚደግሙት። አዛኙ እዉነት ፖለቲከኞቿ ባሳዩት ስግብግብነት፤ የስልጣን ጥማትና የብቀላ መንፈስ ለወራት የተካሄዱ ዉይይቶችና ድርድሮች ያለዉጤት አብቅተዋል። የተፈረሙ የተኩስ አቁም ስምምነቶችም አልተከበሩም። የሀገሪቱን የፖለቲካ መሪዎች በግል የሚያዉቁትና በሽምግልና ድርድሩ ላይ በተደጋጋሚ የተሳተፉት ቄስ ፓሪዴ ታባን «አምላክ ወተትና ማር የምታፈልቅ ምድር ሰጥቶን ነበር» ምን ያደርጋል ይላሉ፤

«በጣም ያሳዝናል ምክንያቱም አባቶቻችን ነፃነታችንን ለማስገኘትና ከሰሜኑ መንግሥት ብዝበዛ ለማላቀቅ ከባድ ዉጊያ አካሂደዉ ነበር። እግዚአብሔር ይህችን ምድር በወተትና ማር አበልጽጓት ነበር። ሆኖም የራሳችን ሰዎች በስስት፤ በስልጣን ጥማት፤ በበቀለኝነትና ይቅርባይነትን በማጣት እንዲሁም ይቅርታ ባለመፈለግ እና በሚሰሯቸዉ ተግባራት ሁሉ ይህቺን ሀገር ሊያወድሟት ነዉ።»

Südsudan Kuron Bischof Paride Taban

ቄስ ፓሪዴ ታባን

የደቡብ ሱዳን ወተትና ማር የነዳጅ ሃብቷ ነዉ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2011ዓ,ም መንግሥት ከፍተኛዉን ምርት አቅርቦ ነዉ ነበር። በቀን 350,000 በርሜል። አሁን 160,000 በርሜል ብቻ ሆኗል። አማፅያኑ የሳልቫኪር መንግሥትን ይደጉማል የሚሉት የነዳጅ ዘይት ያለበትን አካባቢ ለመቆጣጠር በተደጋጋሚ ይሞክራሉ። እነሱም ራሳቸዉ ቢሆኑ የነዳጅ ምርቱን ለራሳቸዉ ለመጠቀም መፈለጋቸዉን ታዛቢዎች ይናገራሉ። ሲትዝን የተሰባለዉ ጋዜጣ ዘጋቢ ኒሃል ቦል የደቡብ ሱዳን ጦርነት መንስኤዉ ያላት ነዳጅ ዘይት መሆኑ ያደባባይ ምሥጢር መሆኑን ያስረዳል፤

«ጥሬ ሃብት ለመቀራመት ነዉ የሚዋጉት። ለምን እንደሚዋጉ ዓላማም ሆነ ግልፅ ሃሳብ የላቸዉም። የነዳጅ ጦርነት ነዉ። ላለፉት 17ወራት አማፅያኑ ለምን እንደሚዋጉ ተጨማጭ ነገር ማቅረብ አልቻሉም። መንግሥትም እንዲሁ። መንግሥትም ምንም አዲስ መመሪያ አላወጣም። የነዳጅ ዘይቱን ማንም አእንዳይገዛ «የደም ዋና» ነዉ ተብሎ መሰየም አለበት። ያኔ ጦርነቱ ያከትማል።»

አድሪያን ክሪሽና ያን ፊሊፕ ሾልስ/ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic