ሰላም የራቃት ሊቢያ | አፍሪቃ | DW | 07.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ሰላም የራቃት ሊቢያ

የቀድሞው የሊቢያ መሪ ሙአማር ኤል ጋዳፊ ከስልጣን ከተወገዱ ከአራት ዓመታት በኋላ ሃገሪቱ አሁንም ተከፋፍላ በርስበርስ ጦርነት ማጥ ውስጥ ትገኛለች። በነዳጅ ዘይት በታደለችው ፣ ግን በተመሰቃቀለችው ሰሜን አፍሪቃዊት ሃገር ውስጥ እስካሁን በአግባቡ የሚሰራ ማዕከላይ መንግሥትም የለም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:54
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
07:54 ደቂቃ

ሊቢያ

በሊቢያ ሁለት ተቀናቃኝ መንግሥታት፣ ሁለት ምክር ቤቶች፣ ሁለት ማዕከላይ ባንኮች እና ሁለት ብሔራዊ የነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪዎችም አሉዋል። በሃገሪቱም ውስጥ የሚገኙት በደርዘን የሚቆጠሩ የሚሊሺያ ቡድኖችም የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው የሚንቀሳቀሱት። ከፊል የሃገሪቱ አካባቢዎችም በፅንፈኞች እና ራሱን እስላማዊ መንግሥት ወይም በምሕፃሩ « አይ ኤስ » ብሎ ከሚጠራው አሸባሪ ድርጅት ጋር ቅርበት ባለው ቡድን ሚሊሺያዎች ጥቃት መረጋጋት ተጓድሏቸው ይገኛሉ። ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘው እና በምሥራቃዊ ሊቢያ የቶብሩክ ከተማ የተቋቋመው መንግሥት በሃገሪቱ ጦር ይደገፋል። ሌላው እውቅና ያላገኘው በመዲናይቱ ትሪፖሊ የተቋቋመው የሊቢያ መንግሥት ነው። ሃገሪቱ እንደተከፋፈለችው ሁሉ 180 እንደራሴዎች ባሉት በቶብሩክ ምክር ቤት የሚወከሉት አንጃዎችም በመካከላቸው ከፍተኛ ልዩነት ይታይባቸዋል። ከፊሎቹ ሃገሪቱ የምትገኝበትን ውዝግብ ለማብቃት የሚፈልጉት እና የተመድ ያቀረበውን የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ምሥረታን የሚደግፉ ሲሆን፣ አክራሪዎቹ ሙስሊሞች እና በእነርሱ አንፃር ጠንካራ ርምጃ ይወስዳሉ የተባሉት የቶብሩክን መንግሥት የሚደግፉት ጄኔራል ኸሊፋ ሐፍታርም ከትሪፖሊ መንግሥት ጋር ተጣማሪ መንግሥት ይመስረት የሚለዉን ሀሳብ፣ የራሳቸውን ስልጣን ይቀንሳል በሚል ስጋት ተቃወሙታል።

ይኸው የተመድ ጥረት ግን በሃገሪቱ የቀጠለውን ግጭት እና ሁከት አላበቃም። በትሪፖሊ እቅድ ሚንስትር ሰሞኑን የታገቱ ሲሆን፣ የትሪፖሊ መንግሥት ለዚሁ የኃይል ተግባር የጦር ኃይሉን ተጠያቂ አድርገዋል። በተለይ በደቡብ ሊቢያ የምትገኘው የሴብሀ ከተማ በተለያዩት ቡድኖች የቀጠለው ሁከት ሰለባ ሆናለች። በከተማይቱ ዋነኞቹ ጎሳዎች መካከል ግጭት አዘውትሮ ይነሳል። ይህንኑ በትንሽ ፀብ የሚፈነዳውን ሁከት በገለልተኝነት ለማብረድ እና የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እና ሕዝብ የሚገለገልባቸውን የመንግሥት ሕንፃዎችን ለመከላከል በ2014 ዓም መጀመሪያ ከሚስራታ ወደ ሴባህ በመሄድ በከተማይቱ አንድ ጽሕፈት ቤት የከፈተው የጦር ቡድን ቃል አቀባይ መሀመድ ግሊዋን የውጥረቱን ምክንያት እንዲህ ያስረዳሉ።

« ሰሜን ምሥራቃዊ ሊቢያ እአአ በ«የካቲት 17» ዓብዮት ነፃ በወጣበት ድርጊት ሰበብ ከ«ኡሌድ ስሊማን» ጎሳ ጋር ህብረት ፈጠርን። የ«ኡሌድ ስሊማን» ጎሳ የቀድሞው የሃገሪቱ መሪ ሙአማር ጋዳፊን ከስልጣን እስከተወገዱበት ጊዜ ድረስ ይደግፍ የነበረ ሲሆን፣ ከቀድሞው መሪ ውድቀት በኋላ ከ«ካዳፋ» ጎሳቸው ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋርጦዋል። ይህ ዋነኛው የውዝግቡ መንስዔ ነው፣ ምክንያቱም፣ የ«ኡሌድ ስሊማን» ጎሳ በ«የካቲት 17» ዓብዮት አንፃር ከጎናቸው ቢቆሙ በወደደ ነበር። ይህ ራሱን የቻለ አንድ አወዛጋቢ ምክንያት ሆኖዋል። ከዚህ ሌላ ደግሞ የሊቢያን ደቡባዊ ድንበር የሚቆጣጠሩት በዚሁ አካባቢ የሚኖሩት፣ እንዲሁም፣ በሰሜናዊ ቻድ እና ሰሜን ምሥራቃዊ ኒዠር ም የሚገኙት የ«ቱቡ ጎሳ » አባላት ለ«ካዳፋ » ጎሳ ፣ የ« ቱዋሬግ » ጎሳ ደግሞ ለ«ኡሌድ ስሊማን» ጎሳ ድጋፋቸውን የሰጡበትም ድርጊት ሌላው የውዝግቡን ያባባሰው ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል። እንደሚታወቀው፣ ጋዳፊን ከስልጣን ያስነሳውን የ«የካቲት 17» ን ዓብዮት ይደግፉ የነበሩት የ«ቱቡ ጎሳ» አባላት ከጋዳፊ በኋላ በሃገሪቱ ስልጣን ላይ በወጡት ወገኖች ችላ በመባላቸው ነበር የ«ካዳፋ ጎሳ»ን መደገፍ የጀመሩት። እነዚሁ የቱቡ ጎሳ አባላት እንደ ሃገሪቱ ዜጋ ባለመታየታቸው ብሔራዊ መታወቂያ እንኳን አልተሰጣቸውም ነበር፣ በዚህም የተነሳ እውቅና ባገኘው የቶብሩክ መንግሥት አንፃር የሚታገለውን ተቀናቃኝ ቡድን ጎራ ተደባልቀዋል። »

በሊቢያ በሚገባ የሚሰራ የፍትህ አውታር ባለመኖሩ በሴባህ ከተማ ለሚታየው ሁከት፣ ግጭት፣ ውጥረት መፍትሔ የሚያፈላልጉት ወይም ለወንጀል ፍርድ የሚሰጡት ያካባቢው ጎሳዎች ኃላፊዎች ናቸው። ይኸው የተጣለባቸው ኃላፊነት ምን ያህል አዳጋች እንደሆነ የገለጹት የ«ኡሌድ ስሊማን ጎሳ» መሪዎች ስለዚሁ ተግባራቸው ሲያስረዱ፣

« በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሁኔታዎችን እናረጋጋለን። ቀጥለንም፣ ወንጀለኞቹን ለአንድ ገለልተኛ ኃይል እናስረክባለን። በመጨረሻም፣ ከሌሎች ጎሳዎች ሽማግሌዎች በመገናኘት እንመካከራለን።»

ይህም ቢሆን ግን፣ የከተማይቱ 94,000 ሕዝብ ራሱን ከጥቃት ለመከላከል የራሱን ርምጃ መውሰድ ጀምሯል። ሁሉም፣ ከየራሱ ጎሳ ጋር መሰባሰቡን የመረጠበት አዝማሚያ እንደሚታይ ነው አንዱ በህብረተ ሰቡ ውስጥ ተሰሚነት ያላቸው አቡ አዞም አል አፊ ያስረዱት።

« ከቅርብ ዘመዶቻቸውአጠገብ ለመሆን ሲሉ ቤታቸውን የለቀቁ ቤተሰቦች አውቃለሁ። ይህ አዝማሚያ ካለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት ጎልቶ ይታያል። ዛሬ እንኳን ነዋሪዎች፣ የሚኖሩበት አካባቢ ለጎሳቸው አባላት ደህንነት አስጊ ነው እያሉ፣ መኖሪያ ቤታቸውን ለሽያጭ እያቀረቡ ነው። »

እና በከተማይቱ ሴብሃ የሚገኙት የተለያዩት ጎሳዎች ለህልውናቸው በመስጋት በየጎሳቸው መሰባሰብ የያዙበት ድርጊት፣ በጎሳዎች መካከል መቀራረብ ሊኖር እና ከተማይቱም ውላ አድራ ልትረጋጋ የምትችልበትን ሁኔታ ይበልጡን አዳጋች እያደረገው መሄዱን አቡ አዞም አል አፊ በቅሬታ ገልጸዋል።

Audios and videos on the topic