ሮቦቶች በእኛ ዓለም | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 13.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ሮቦቶች በእኛ ዓለም

በዓለማችን በዘመናዊ ስነ-ቴክኒክ እገዛ ከጥቃቅን ሮቦቶች አንስቶ እስከ ግዙፍ ሮቦቶች ምርት እየተራቀቀ በመሄድ ላይ ይገኛል። ሮቦቶች ለሰው ልጅ ሲበዛ ከባድ እና አደገኛ የሆኑ ተግባራትን ይፈጽማሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:22

ረቂቅ ሮቦቶች

አንዳንዴ በዓይን ለመታየት እጅግ አዳጋች ደቂቃን ናቸው። አንዳንዴ ደግሞ እጅግ ግዙፍ። ሲሻቸው በተገጠሙበት ሥፍራ ሆነው ክንዳቸውን በፈለጉት አቅጣጫ ያሽከረክራሉ። አንዳንዴ ደግሞ እንደ ታንክ በተገጠመላቸው ሰንሰለት ላይ እየተሽከረከሩ እጅግ አደገኛ የሚባሉ ቦታዎች ድረስ ይዘልቃሉ። በሰማዩ ላይ አየሩን እየቀዘፉ መክነፍም ተክነውበታል። በአይነት፤ በቅርጽ እና በተግብር ዘርፈ ብዙ ናቸው፤ ሮቦቶች። ሮቦቶች በምድራችን እጅግ የተወሳሰቡ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ። የሰው ልጅ በሮቦት ስነ-ቴክኒክ የደረሰበት እመርታ አንዳንድ ጊዜ ለማመን ይከብዳል። የቅርብ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ከፊል ማሽን ከፊል ሕይወት ገጽ የያዘ ሮቦት ዓሣ በምርምር መሥራት ተችሏል።

ሮቦቶች እጅግ የረቀቀ እና የተወሳሰበ ደረጃ ላይ ስለመድረሳቸው የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እና ክስተቶች አመላካች ናቸው። «ለሳይንስ እመርታ የአሜሪካን ማኅበር» በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ (AAAS) የተሰኘው ተቋም ዓርብ፤ ሐምሌ 1 ቀን፣ 2008 ዓ.ም ባወጣው እትሙ አንድ አስደናቂ የምርምር ውጤት ለንባብ አብቅቷል። ከፊል ማሽን እና ከፊል ሕይወት ያለውን ነገር በማዳቀል ሣይንቲስቶች ጄል ፊሽ የተሰኘው የዓሣ አይነት ሮቦትን መሥራት መቻላቸውን ጽሑፉ አስነብቧል። ሮቦት ዓሣው የተሠራው የሁለት ቀናት ዕድሜ ካለው የአይጥ ጽንስ 20 ሺህ የልብ ሴሎች እና የፕላስቲክ ውህደት ነው። የሮቦት ዓሣው ግራ እና ቀኝ የፕላስቲክ ክንፎች ውስጥ በስልት የተደረደሩት ሴሎች ብርሃን ሲያርፍባቸው አጸፌታ በመስጠት ሮቦት ዓሣው መንቀሳቀስ ችሏል።

ጃርሶ ጸጋዬ ከበደ

ጃርሶ ጸጋዬ ከበደጃርሶ ጸጋዬ ከበደ በዶርትሙንድ የስነ-ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ በድኅረ-ምረቃ ዲግሪውን ለመያዝ የሮቦቶች እና ምጡቅ አስተሳሰብ ስልታቸው ላይ ጥናቱን እያከናወነ ነው። ተወልዶ ያደገው፤ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስም ትምህርቱን ያጠናቀቀውም ሆለታ ከተማ ውስጥ ነው። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪውን ይዟል። ጀርመን ሀገር ለትምህርት ከመጣ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል። ጃርሶ የስለሮቦት ምንነት በበርካታ የምርምር ተቋማት የተለያዩ ትርጓሜዎች ቢሰጡትም በጥቅሉ ግን ሮቦት ምን ማለት እንደሆነ እንዲህ ያብራራል።

ሮቦቶች በአይነት እና ዘርፋቸው በርካታ ቢሆንም በዋናነት ግን በሁለት ይከፈላሉ። እነሱም ኢንዱስትሪ ውስጥ ተተክለው ክንዳቸውን ባሻቸው አቅጣጫ እያሽከረከሩ ተግባራቸውን የሚፈጽሙ እና በተለያዩ ቦታዎች የሚንቀሳቀሱ ሮቦቶች ናቸው።

ሮቦቶች ለህክምና፣ ለጦር ሠራዊት ግልጋሎት፣ ለቤት ውስጥ እገዛ፣ ለመዝናኛ፣ ለውድድር እና በትርፍ ጊዜ መዋያ ተብለው ይሠራሉ። በዓለም አቀፉ የኅዋ ምርምር ተቋም ላይ በዜሮ የስበት ኃይል ግልጋሎት የሚሰጠው ካናድራም እና የከርሰ ምድር ቁፋሮ እንዲያከናውን ወደ ማርስ የተላከው የማርስ አሠሣ ተልዕኮ ተሽከርካሪ ሮቦት በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ (MER) ተጠቃሾች ናቸው።

ጃርሶ ጸጋዬ ከበደ፤ በዶርትሙንድ የስነ-ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ በድኅረ-ምረቃ

ጃርሶ ጸጋዬ ከበደ፤ በዶርትሙንድ የስነ-ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ በድኅረ-ምረቃበቅርቡ አሜሪካን ውስጥ ጥቁሮች በተደጋጋሚ በነጭ ፖሊሶች መገደላቸውን በመቃወም አምስት ፖሊሶችን ገድሎ ሰባቱን ያቆሰለው ሚካ ጆንሰን የተባለው አሜሪካዊ ጥቁር የቀድሞ ወታደር የተገደለው ከሮቦት በሚወነጨፍ ቦንብ እንደሆነ ተገልጧል። ከሮቦት የሚወነጨፍ ቦንብ በአሜሪካ ምድር ጥቅም ላይ ሲውል የመጀመሪያው ነበር።

የሮቦት ስነ-ቴክኒክ ምርምር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለማችን እጅግ እየረቀቀ ነው። ከቻይና የመጣ የሮቦት ቁሳቁስ ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ መገጣጠሙ ተነግሯል። ሆኖም ያላቸው ተማሪዎች እንዲመራመሩበት መንገዱን ማመቻቸት ይገባል ብሏል አጥኚው ጃርሶ።

የሮቦት ሳይንስን እጅግ የረቀቀ ደረጃ አድርሰዋል በሚባልላቸው ጃፓኖች ዘንድ ሮቦቶች እንግዶችን በሰላምታ ተቀብለው በማስተናገድ፤ የደንበኛውን ማንነት መዝግበው የመኝታ ክፍሎችን እስከማሳየት ደርሰዋል። ሮቦቶቹ የሰዎችን የፊት ገጽታ በማንበብም ስሜትን መግለጥ ይችላሉ።


ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic