ሮም፤ ከ600 በላይ ስደተኞች ባህር ላይ ለአደጋ ተጋልጠዋል | ዓለም | DW | 11.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ሮም፤ ከ600 በላይ ስደተኞች ባህር ላይ ለአደጋ ተጋልጠዋል

በአብዛኛው የኤርትራ እና የሶማሊያ ዜግነት ያላቸው 620 ስደተኞችን የጫነች ጀልባ በሜድትራንያን ባህር ላይ ሞተሯ በመላሸቱ ሰዎች ለአደጋ መጋለጣቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘገበ።

የማልታ ጋዜጣ በሣተላይት ስልክ ያነጋገረው በጀልባዋ ላይ የሚገኝ ስደተኛ ብዙዎቹ መታመማቸውን፣ እንዲሁም ምግብ እና ውሃ መጨረሳቸውን ተናግሯል። ስደተኞቹን የጫነችው ጀልባ ከሊቢያ ዋና ከተማ 66 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ሳብራታ ከተባለ ቦታ አርብ ጉዞ ሳትጀምር አልቀረችም ተብሏል። የጣሊያን ድንበር ጠባቂዎች ስደተኞቹን ለመታደግ ጥረት እንደጀመሩ ተጠቅሷል። የማልታ ጋዜጣ በስልክ ያነጋገረው ኤርትራዊ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ስደተኞችም በጀልባዋ ላይ መኖራቸውን ተናግሯል። በአነስተኛ ጀልባዎች ከሊቢያ ወደቦች በመነሳት ወደ አውሮጳ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት ማሳየቱ ይነገራል። የተሻለ የኑሮ እና የሥራ እድል ፍለጋ እንዲሁም የመንግስታት ጭቆና ስደተኞቹ የሜድትራኒያንን ባህር ለማቋረጥ ከሚገደዱባቸው ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ። ባለፈው አመት ብቻ 218,000 ሰዎች የሜድትራኒያን ባህርን በጀልባ ማቋረጣቸውን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን አስታውቋል። 3,500 ያህሉ ግን ከጉዞው መጨረሻ መድረስ ሳይችሉ በባህሩ ላይ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ