ሮማ፤ ከሰጠመችዉ መርከብ ነፍስ የማዳኑ ተግባር መጠናቀቁ | ዓለም | DW | 29.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ሮማ፤ ከሰጠመችዉ መርከብ ነፍስ የማዳኑ ተግባር መጠናቀቁ

አድርያቲክ ዉቅያኖስ ዉስጥ መስጠም ከጀመረችዉ መርከብ ተሳፋሪዎችን የማዳኑ ተግባር መጠናቀቁን የጣሊያን መንግሥት አስታወቀ።

478 ሰዎችን አሳፍራ የነበረችዉ የሰዉ እና እቃ መጫኛ መርከብ ትናንት ነዉ በጉዞ ላይ ሳለች የእሳት ቃጠሎ የገጠማት። በአደጋዉ የአምስት ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። ከግሪክ ኮርፉ ደሴት ወደጣሊያኗ አንኮና ወደብ ስትጓዝ በነበረችዉ መርከብ ላይ አሁን ካፒቴኑና አራት የነፍስ አድን ሠራተኞች ብቻ እንደሚገኙ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ማቴዎ ሬንዚ ገልጸዋል። መርከቧን የመጎተት ሙከራ ገመዱ በመበጠሱ ሲሰናከል፤ እሳትም ከጥቅም ዉጭ እንዳደረጋት ተዘግቧል። የነፍስ ማዳኑን ተግባር እጅግ አስቸጋሪ የነበረዉ የአየር ጠባይ አዳጋች እንዳደረገዉ ነዉ የተገለጸዉ። የነፍስ ማዳኑን ተግባር ያስተባበሩት ጆቫኒ ፔቶሪኖ፤

«የአየር ሁኔታ ነፍስ የማዳን ተግባሩን በጣም ነዉ ያወሳሰበዉ፤ አምስትና ስድስት ጫማ ከፍታ ባለዉ ማዕበል እየተደራረበ ይነሳ ነበር። ይህ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነዉ።»

በወቅቱ ከባድ ግርግር እንደነበር ያመለከቱት ተሳፋሪዎች በበኩላቸዉ በነፍስ አድኑ ተግባር የረኩ አይመስሉም። መርከቧ የጫነቻቸዉ የነፍስ ማዳኛ ጀልባዎች በቂ እንዳልነበሩ በመጥቀስም ለጊዜዉም ቢሆን ለመዳን ወደመርከቧ የላይኛዉ ክፍል መዉጣት መገደዳቸዉን ይናገራሉ። ከመንገደኞቹ አንዱ፤

«ዘይት የተሞሉ በርካታ እቃዎች ነበሩ። ከ100 የሚበልጡት እቃ መጫኛዎች የወይራ ዘይት የያዙ ማጠራቀሚያዎችን እንደጫኑ እርግጠኛ ነኝ። እዚያ ነዉ እሳቱ የተነሳዉ እናም ከሰዓት በኋላ ስምንት ሰዓት ገደማ ነዉ የታየዉ መሬቱን አግሎት ማለት ነዉ። ጭስም ተከተለ።»

ዘግይተዉ የወጡ ዘገባዎች እንዳመለከቱት የጣሊያን የባህር ወደብ ጠባቂዎች ተጨማሪ ሁለት አስከሬን ዛሬ አዉጥተዋል፤ ይህም የሟቾችን ቁጥር ሰባት አድርሶታል።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ