ርዋንዳ ከአሰቃቂው የዘር ፍጅት እንዴት አገገመች? | አፍሪቃ | DW | 30.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ርዋንዳ ከአሰቃቂው የዘር ፍጅት እንዴት አገገመች?

ርዋንዳ ከ25 አመታት በፊት የተፈጸመውን ፍጅት ለመዘከር በዝግጅት ላይ ነች። አገሪቱ ዜጎቿ ከማይኮሩበት ግን ደግሞ ከማይረሱት የታሪክ ጠባሳ ብዙ ብትራመድም ዛሬም መፍትሔ ያላገኙ ቁርሾዎች አላጧትም። ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የገነባችው የፖል ካጋሜ አገር ከ25 አመታት በፊት የጥቃት ሰለባ የሆኑ ቱትሲዎች ባሉበት ሁሉ ጥብቅና ልትቆምላቸው ትሻለች

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:35

የርዋንዳ ፍጅት 25ኛ አመት በሚቀጥለው ሳምንት ይዘከራል

ከ25 አመታት በፊት በርዋንዳ ሰው በሰው ላይ ተነሳ። ወታደራዊ ባለሥልጣናት፣ ፖለቲከኞች እና ባለወረቶች ጭምር ጥቃቱን በማቀነባበር ቀዳሚ ነበሩ። የተደራጁ ወሮበሎች በቆንጨራቸው ጠላት ባሏቸው ያገራቸው ሰዎች ላይ እጃቸውን አነሱ። ጥቃቱን ሸሽተው በአብያተ-ክርስቲያናት የተጠለሉትን በቁማቸው አቃጠሏቸው። አስከሬኖቻቸውን ወደ ወንዝ ወረወሩ። አንዳንዶች የዘር ግንዳቸው ከወደ ኢትዮጵያ ይመዘዛል የሚሏቸው ቱትሲዎች ጥቃቱ የበረታባቸው ሰለባዎች ነበሩ። በሥልጣን ላይ የነበረው መንግሥት በቀጥታ እጁን ባስገባበት በዚያ አሰቃቂ የ100 ቀናት ጥቃት ለዘብተኛ ሑቲዎች ጭምር በገፍ ተገደሉ።

የዘር ማጥፋት መከላከያ ኮሚሽን ዋና ጸሓፊ ዤን ዳማስኔ ቢዚማና "እስከ 2000 ዓ.ም. በተካሔደ የማጣራት ሥራ በዘር ማጥፋቱ የተገደሉ ከ አንድ ሚሊዮን በላይ መሆናቸው ተደርሶበታል። በ2002 ይፋ በተደረገ ሰነድ መሠረት 1,074,017  ሰዎች ተገድለዋል።  ይሁንና ከዚያ በላይ እንደሚሆን እንገምታለን። ምክንያቱም ሰዎች ተገድለው ወደማናውቀው ቦታ ተጥለዋል" ሲሉ ዛሬም ድረስ የሰለባዎች ትክክለኛ ቁጥር እንደማይታወቅ ይናገራሉ። 

ዤን ዳማስኔ ቢዚማና ርዋንዳ ይኸ የዘር ማጥፋት ታሪኳ ደግሞ እንዳይፈጸም ያቋቋመችውን ኮሚሽን በዋና ጸሐፊነት ይመራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ከ25 አመታት ገደማ በፊት የተፈጸመው የዘር ማጥፋት በተለይ በአንድ ጎሳ ላይ በመበርታቱ የአገሪቱን አንድነት ክፉኛ ጎድቶታል። ዋና ጸሐፊው "ባለፉት 25 አመታት የርዋንዳ ትልቁ ፈተና ብሔራዊ አንድነትን መልሶ መገንባት ነበር። ምክንያቱም ድርጊቱ የማኅበረሰቡን አንድ ክፍል ለይቶ የማጥፋት ተግባር ነው። በርዋንዳ ይኸ ጥቃት የደረሰው በቱትሲ ላይ ነው። በዚህ አሰቃቂ ድርጊት ምክንያት የአገሪቱ አንድነት ተሰብሯል" ሲሉ ያብራራሉ። 

ከዚያም በፊት የብሔር ግጭት በርዋንዳ እንግዳ አልነበረም። በተለይ በሑቱዎች እና በቱትሲዎች መካከል የበረታ መቃቃር ነበር። ተመሳሳይ ቋንቋ በሚናገሩት፣ በተመሳሳይ አካባቢ በሚኖሩት እና ተመሳሳይ ልምድ እና ባሕል በነበራቸው በሑቱዎች እና በቱትሲዎች መካከል የነበረው ውጥረት የበረታው በተለይ አገሪቱ በቅኝ ከተገዛች በኋላ ነበር። 

ጭፍጨፋው ከመከሰቱ ቀደም ብሎ የሚጓዙበት አውሮፕላን አየር ላይ ፈንድቶ ሕይወታቸውን ያጡት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጁቪናል ሐቤሪማና ተቀባይነታቸው አሽቆልቁሎ ወደ ሑቱዎች አዘንብለው ነበር። የዛሬው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ የሚመሩት የርዋንዳ አርበኞች ግንባር ከሐቤሪማና መንግሥት የሰላም ስምምነት ቢፈርምም በአገሪቱ የተንሰራፋውን ኹከት ለመግታት አልተቻለም። የሐቤሪማና ሞት ውጥረቱን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት መቃብር ከተተ።  ከዚያ በኋላ የተፈጠረው ሁሉ  ርዋንዳ ዜጎቿ የማይኮሩበት ግን ደግሞ የማይረሱት የታሪክ ጠባሳ ነበር። ከኪጋሊ በስተሰሜን የሚገኘው መታሰቢያ የመቶ ቀናቱን ጭፍጨፋ ሰለባዎች ይዘክራል። በዚያ በየመንገዱ ተገድለው በየጥሻው የወደቁ ራስ ቅሎች፤ አጥንቶች ተሰብሰበዋል። 

በየዕለቱ እስከ አስር ሺሕ የሚደርሱ ርዋንዳውያን ለሶስት ወራት ሲጨፈጨፉ የተቀረው ዓለም ያደረገው አንዳች ነገር አልነበረም። ሁሉም ነገር ከአሰቃቂ ደም መፋሰስ በኋላ መቋጫ ያገኘው በወቅቱ የ36 አመት ጎልማሳ በነበሩት ስደተኛ ፖል ካጋሜ የሚመራው የርዋንዳ አርበኞች ግንባር ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት አሸንፎ አገሪቱን በቁጥጥር ሥር ሲያውል ነበር። 

ባለፉት 25 አመታት በፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ መንግሥት ርዋንዳ እንደገና ተሰርታለች። "ጉዳዩ ባለፉት 25 አመታት ሁሉም ሩዋንዳውያን አንድ አገር እንደምንጋራ መረዳት አስችሏል። ሁላችንም ተመሳሳይ መብቶች አሉን። ይሁንና የሕግ የበላይነትን መልሶ መገንባት ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል። የርዋንዳ መንግሥትም ይኸንንው ሥራ ለ25 አመታት ሲያከናውን ነበር። አገሪቱ ሙሉ በሙሉ በመረጋጋቷ ምክንያት የዕርቅ ሒደቱ ትልቅ እርምጃ ተራምዷል። ሕዝቡ በባለስልጣናት እና በአስተዳዳሪዎቹ እምነት ስላለው ይኸ ጠቃሚ እርምጃ ነው። አሁን ሕዝቡ የሚጠይቀው አንድ ነገር ብቻ ነው። ይኸውም የሽግግር ሒደቱን ማፋጠን" የሚሉት ዤን ዳማስኔ ቢዚማና የአገራቸው የ25 አመታት ጉዞ ስኬታማ ቢሆንም ፈተናዎች እንዳላጡት አይሸሽጉም።

ከጭፍጨፋው ሩብ ምዕተ-ዓመታት በኋላ በእርግጥ ርዋንዳ በብልፅግና መንገድ ላይ ትገኛለች። ወደብ አልባዋ ትንሽ ሀገር የጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት፤ የመረጋጋት እና ሰላም ባለቤት ሆናለች። አስራ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ዜጎቿ ነፃ የትምህርት አገልግሎት፣ የተሻለ የጤና መድኅን ዋስትና ያገኛሉ። አማካኝ የዕድሜ ጣሪያ በእጥፍ ጨምሯል።  ከአገሪቱ የታችኛው ምክር ቤት አባላት ከግማሽ በላይ ሴቶች ናቸው።

 

የደቡብ አፍሪካው የዕርቅ እና የፍትኅ ማዕከል ተመራማሪ ፓትሪክ ሐጃያንዲ "በልማት እና በአመራር ረገድ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ርዋንዳን መልሶ በመገንባት ስኬታማ ሥራ አከናውነዋል። ከጅምላ ጭፍጨፋው በኋላ የፈራረሰችው አገር ዛሬ ያላትን ቁመና እንድታገኝ አድርገዋል። ፕሬዝዳንቱ አገራቸውን የውጭ መዋዕለ-ንዋይ እንድታገኝ ሰርተዋል እንዲሁም በአግባቡ ከሚመሩት አገራት ጎራ እንድትመደብ አድርገዋታል"  ሲሉ የአገሪቱ ሥኬት የፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ጥረት እንደሆነ ይመሰክራሉ። 

የርዋንዳ የቀደመ ታሪክ በዛሬ አቋሟ ላይ ጫና ማሳደሩ ግን አልቀረም። በለንደን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪው ፊል ክላርክ  «የ1994ቱ የጅምላ ጭፍጨፋ በፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ እይታ ከፍ ያለ ፋይዳ ነበረው ብንል ማጋነን አይሆንም። በሑቱ እና በቱትሲዎች መካከል ያለውን ማኅበረ ኤኮኖሚያዊ የዕኩልነት መዛባት ለመጀመሪያ ጊዜ ለማቃነት የሞከረው የአሁኑ መንግሥት ነው" ሲሉ ይናገራሉ። 

ተንታኞች እንደሚሉት ይኸ በፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ እና በመንግሥታቸው ዘንድ አለ የሚባለው አረዳድ ለአምባገነንታቸው ምንጭ ሳይሆን አልቀረም። በፖል ካጋሜ እይታ ፖለቲካዊ ተቃውሞ የኹከት ምንጭ ነው። በጅምላ ጭፍጨፋው አስቀያሚ ሚና የነበረው የብዙኃን መገናኛ መገደብ ይኖርበታል። በፖል ካጋሜ አንጋብጋቢ የቤት ሥራዎች ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች መከበር ትኩረት ከሚሰጣቸው ጎራ አይደለም። የፕሬዝዳንቱ ዋንኛ ትኩረት ከ25 አመታት በፊት የተፈጸመውን ድርጊት ከመደገም መከላከል ይመስላል። ፊል ክላርክ "ይኸ በመላ ቀጠናው የሚገኙ ቱትሲዎችን ከጥቃት እስከ መጠበቅ ይሰፋል። ከርዋንዳ ዋንኛ ሥጋቶች መካከል በቡሩንዲ፣ ምሥራቃዊ ኮንጎ እና በዩጋንዳ የሚገኙ ቱትሲዎች እጣ ፈንታ ነው። ባለፉት 25 አመታት ቱትሲዎች የሥልታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑባቸው አገሮች ይገኛሉ። ስለዚህ ርዋንዳ ቱትሲዎች በየትኛውም አገር ቢገኙ ራሷን የደኅንነታቸው ጠበቃ አድርጋ ትቆጥራለች" ሲሉ ይገልጹታል። 

ርዋንዳ በምትጎራበታቸው እና ቱትሲዎች በሚገኙባቸው አገራት መካከል አንዳቸው የሌላቸውን ተቃዋሚ የማስጠለል እና የማስታጠቅ ውንጀላዎች በተደጋጋሚ ይሰማሉ። በቅርቡ ይኸው ውዝግብ ከፍ ካለ ደረጃ ላይ ደርሷል። ርዋንዳ ከጎረቤት ዩጋንዳ የምትዋሰንበትን ድንበር እስከ መዝጋት ደርሳለች። የዩጋንዳ መንግሥት በበኩሉ የጦፈ የንግድ ልውውጥ በሚካሔድበት ድንበር የፖል ካጋሜ መንግሥት ያሳለፈውን ውሳኔ የንግድ ማዕቀብ ሲል ወንጅሏል። በማካሬሬ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ተንታኙ ምዋንጉሒ ኤንድቤዛ በጎረቤታሞቹ መካከል ለበላይነት የሚደረግ ትንቅንቅ ይታያቸዋል። ምዋንጉሒ ኤንድቤዛ "በቀጣናው የበላይ ለመሆን በሚያደርጉት ፉክክር ቅራኔ ውስጥ ሳይገቡ አልቀረም። የቀጣናው የበላይ ማነው?  ይኸ በፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ እና በፕሬዝዳንት ካጋሜ መካከል ያለ የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፍክክር ነው" ሲሉይናገራሉ። 

የዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና የርዋንዳው አቻቸው ፖል ካጋሜ ትውውቃቸው ረዘም ያለጊዜ ያስቆጠረ ነው። ሁለቱ መሪዎች የዛሬን አያድርገውና ወዳጆች ነበሩ። የቀድሞውን የዩጋንዳ አማጺ የዛሬውን ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒን በጎርጎሮሳዊው 1986 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን ካስወነጨፏቸው መካከል ፖል ካጋሜ ቁልፉ ሰው ነበሩ። የርዋንዳ አርበኞች ግንባር የተባለው አማጺ ቡድን የተወለደው ሙሴቬኒ ከሚመሩት ብሔራዊ የተቃውሞ ንቅናቄ ውስጥ ነበር። አማፂ ቡድኑ ርዋንዳን ወርሮ ካጋሜ ሥልጣን ሲይዙ የሙሴቬኒ ንቅናቄ ድጋፍ አድርጓል። ርዋንዳዊው ተንታኝ ክሪስቶፈር ካዩምባ እንደሚሉት ግን ሁለቱ መሪዎች ተደጋግፈው ሥልጣን ከተቆናጠጡ በኋላ ቀስ በቀስ ግንኙነታቸው ሻክሯል። 

"ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ እና የጦር ጄነራሎቻቸው የርዋንዳ መሪዎች የእነሱ ዕዳ እንዳለባቸው ያምናሉ። ምክንያቱም ጁቪናል ሐቤሪማናን ከሥልጣን በማስወገድ እና የጅምላ ጭፍጨፋውን በማስቆም አግዘዋቸዋል" ሲሉ ክሪስቶፈር ካዩምባ ያስረዳሉ። 

በቀጣናው ከፍ ያለ ተፅዕኖ የሚመኙት ካጋሜ በሙሴቪኒ እንደ ታናሽ መታየታቸውን የሚወዱት የሚቀበሉትም አይመስልም። ሙሴቬኒ የተቃቃሩት ደግሞ ከካጋሜ ብቻ አይደለም። ባለፉት ጥቂት አመታት ከቡሩንዲ ያላቸው ግንኙነት መሻከር ጠንቶበታል። በፖል ካጋሜ እና ዘራቸው ከሑቱ ጎሳ የሚመዘዘው የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ያላቸው ግንኙነት ለዚህ አስተዋፅዖ አበርክቷል። የቡሩንዲው ተመራማሪ ፓትሪክ ሐጃያንዲ ግን ጉዳዩ ከዚህ ከፍ ያለ አሳሳቢ ምክንያት ጭምር እንዳለው ይናገራሉ።  ፓትሪክ ሐጃያንዲ "በርዋንዳ የሚወራው ሁሉ ሁሉም ሰው የአንድ አገር ዜጋ ስለመሆኑ ነው። ይኸን ጉዳይ ወረድ ብለህ ከሰዎች ጋር ስትጫወት ግን እንደ ጨፍጫፊ በሚቆጠሩት በሑቱዎች ዘንድ የመገፋት ስሜት እንዳለ ትገነዘባለህ" ሲሉ ተናግረዋል። 

ይኸ ማለት ሑቱዎች ዛሬም የጅምላ ጭፍጨፋው ጠንሳሽ፣ አቀነባባሪ እና ፈፃሚ ተደርጎው የመቆጠራቸው ጣጣ ነው። ጉዳዩ ዛሬም አይታመኑም የሚል ስሜት አሳድሯል። ፓትሪክ ሐጃያንዲ ቡሩንዲ በዜጎች መካከል የጎሳ አሰላለፍ የፈጠረውን ክፍተት አስቀርታ አንድነት መፍጠሯ በካጋሜ ዘንድ እንደ ሥጋት ተቆጥሯል የሚል ዕምነት አላቸው። ተንታኙ በበርካታ ችግሮች የሚዋከቡት ንኩሩንዚዛ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተቃዋሚዎችን ሳያግዙ አይቀርም የሚለው ወቀሳም አይዋጥላቸውም።  "በድንበር አካባቢዎች ባለው ክፍተት ምክንያት ከአንዱ አገር ወደ ሌላው የጦር መሳሪያ ይሸጋገር ይሆናል። በቡሩንዲ በኩል የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥትን በአመፅ የመጣል ፖሊሲ ያለ ግን አይመስለኝም" የሚሉት ፓትሪክ ሐጃያንዲ በቡሩንዲ ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶች አይዋጡላቸውም። 

ፊል ክላርክ እንደሚሉት ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በበኩሏ ዛሬም ድረስ ራሷ ባለኮሰችው እሳት ትለበለብ ይዛለች።  ተመራማሪው "አሁን በኮንጎ የሚታየው በ1994 በርዋንዳ ከተፈጠረው ጋር ግንኙነት እንዳለው ምንም ጥርጥር የለውም። ባለፉት 20 አመታት ምሥራቃዊ ኮንጎ በተለያዩ ጊዜያት በርዋንዳ እና ዩጋንዳ ወታደሮች ተወሯል። ዩጋንዳ እና ርዋንዳ አማፅያንን በእጅ አዙር መጠቀማቸውም አልቀረም" የሚል እምነታቸውን ለDW ገልጸዋል። 

ርዋንዳ በዓለም መድረክ በስኬት እየተወደሰች ከጎረቤቶቿ ግን በጎሪጥ እየተያየች ዜጎቿ ያለቁበትን የዘር ፍጅት 25ኛ አመት ለማሰብ ተዘጋጅታለች። በበርካቶች ዘንድ አደራ እንዳይደገም የሚል አቋም በግልፅ ይነጸባረቃል። በቅጡ ያልረጋው የቀጠናው ፖለቲካ እንዳይደፈርስ ሥጋት መኖሩን ግን ፊል ክላርክ ታዝበዋል። "የርዋንዳ ጅምላ ጭፍጨፋ ለ25ኛ ጊዜ የሚታሰበው በቀጠናው ያለው የርስ በርስ ሽኩቻ በተደጋጋሚ በሚታይበት በዚህ ጊዜ ነው። በአገሮቹ መካከል ላለው ግጭት መፍትሔ እንዲፈልጉ በመሪዎቹ ላይ ከፍ ያለ ጫና አለ" ሲሉ ተናግረዋል። 

ጫናው ግን ተንታኞቹ እንደሚሉት ከምዕራባውያኑ አገራት ለመምጣቱ ማረጋገጫ የለም። ርዋንዳ ዛሬም በምዕራባውያን እርዳታ ላይ ጥገኛ ብትሆንም የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ዴሞክራሲያዊ መልክ ይኖረው ዘንድ ግፊት የሚያደርግ እምብዛም አልተገኘም። 

የአፍሪካ ኅብረት በቀጣናው የሰፈነውን ውጥረት ማርገብ ተስኖታል። ቡሩንዲ፣ ዩጋንዳ እና ርዋንዳን ያቀፈው የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ማኅበረሰብ (EAC) በገዛ አባሎቹ ዘንድ መግባባት መፍጠር የሚችልበት ሥርዓት የለውም። የርዋንዳው ክሪስቶፈር ካዩምባም ሆኑ የብሩንዲው ፓትሪክ ሐጃያንዲ ኹነኛው መፍትሔ የአገራቱ ዜጎች በመሪዎቻቸው ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ማድረግ ነው የሚል ዕምነት አላቸው። "ዜጎች ችግር የለባቸውም። ለመገበያየት፣ አንዳቸው የሌላቸውን አገር ለመጎብኘት ፈቃደኛ ናቸው" የሚሉት ፓትሪክ ሐጃያንዲ ቀውስ ቢፈጠር ሰለባ የሚሆኑት የአገራቱ ነዋሪዎች መፍትሔ ለመፈለግ ቸልተኛ መሆን የለባቸውም የሚል አቋም አላቸው።

እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic