ርዋንዳ እና አወዛጋቢው የፕሬዚደንቱ የስልጣን ዘመን | አፍሪቃ | DW | 10.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ርዋንዳ እና አወዛጋቢው የፕሬዚደንቱ የስልጣን ዘመን

የርዋንዳ ላዕላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ እአአ በ 2017 በሚካሄደው ምርጫ ለሶስተኛ ጊዜ እጩ ተወዳዳሪ ሆነው መቅረብ እንደሚችሉ አስታወቀ። ይኸው የላዕላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ግን አወዛጋቢ መሆኑ አልቀረም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:06
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
05:06 ደቂቃ

ምክንያቱም በሃገሪቱ ሕገ መንግሥት መሰረት፡ የፕሬዚደንቱ የስልጣን ዘመን በሁለት የተገደበ ነው።
ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ለሶስተኛ የሥልጣን ዘመን መወዳደር እንዲችሉ ሕገ መንግሥቱን ይሻሻል አይሻሻል በሚለው ጉዳይ ላይ የሃገሪቱ ምክር ቤት እንደራሴዎች የሃገሪቱን ፕሬዚደንት ሥልጣን በሁለት ዘመን በሚገድበው አንቀጽ 101 ላይ ማሻሻያ ለውጥ ይደረግበት በሚለው ሀሳብ ላይ ባለፈው ሀምሌ ወር ክርክር ካካሄዱ በኋላ ሀሳቡን መደገፋቸው ይታወሳል። የፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ለሶስተኛ የሰባት ዓመት ዘመነ ሥልጣን እንዲወዳደሩ ፍርድ ቤቱ ያሳለፈው ብይን ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ግን በሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ ይደረግ አይደረግ የሚለው ጥያቄ በሬፈረንደም የሕዝቡን ድጋፍ ማግኘት ይኖርበታል።
ፍርድ ቤቱ በዚሁ ትናንት ባሳለፈው ብይን ዋነኛው የርዋንዳ ተቃዋሚው የአረንጓዴ ፓርቲ ካጋሜ ለሶስተኛ የሰባት ዓመት የስልጣን ዘመን በእጩነት መቅረብ ይችሉ ዘንድ መንግሥታቸው በሕገ መንግሥቱ ላይ የማሻሻያ ለውጥ እንዲደረግ የጀመረውን ጥረት ለማከላከል እአአ ባለፈው ሀምሌ 29 ቅሬታውን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ያቀረበውን ክስ ውድቅ አድርጎዋል። ፓርቲው ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ስለሚወስደው ቀጣይ ርምጃ የፓርቲው ፕሬዚደንት ፍራንክ ሀቢኔዛ ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል።


« በላዕላዩ ፍርድ ቤት ውሳኔ አልተደሰትንም፣ ምክንያቱም፣ ፍርድ ቤቱ ያስገባነውን የክስ ማመልከቻ በመደገፍ ውሳኔ ሊሰጥ የሚያስችሉትን ተጨባጭ ምክንያቶች አቅርበንለት ነበር። ብይኑ የተነሳንበትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ አያግደንም። በጀመርነው ዴሞክራሲያዊ ትግል እንቀጥልበታለን።»
ፍርድ ቤቱ ላስተላለፈው ብይን አሳማኝ ማስረጃ አለማቅረቡን ነው ሀቢኒየዛ ያስረዱት።
« የሕዝቡን ፍላጎት ማክበር የተሰኘው ምክንያት ትልቁ መነሻ ምክንያታቸው እንደነበር የፍርድ ቤቱ ዳኞች ተናግረዋል። ግን ይኸው ፕሮዤ የተጀመረው በሕዝቡ ሳይሆን፣ በጥቂት ሚንስትሮች እና የምክር ቤት እንደራሴዎች መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን። ጠቅላላ ሂደቱ በሕግ አንፃር ነበር፣ ምክንያቱም፣በመንግሥት ባለስልጣናት ግፊት የተነቃቃ ነበር። ይህን ነበር እንደ መከራከሪያ ሀሳብ ያቀረብነው።»
የአረንጓዴው ፓርቲ ፕሬዚደንት ፍራንክ ሀቢኒየዛ እንዳስረዱት፣ የፕሬዚደንት ፖል ካጋሜን የስልጣን ዘመን ለማራዘም የተጀመረውን ጥረት ለማስቆም በተለያዩ ዘዴዎች ለመጠቀም ወስኖዋል።


« አቤቱታችንን ለፕሬዚደንቱ ማቅረባችን አይቀርም። ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 98 መሰረት፣ የሃገሪቱ ፕሬዚደንት የሕገ መንግሥቱ ዋነኛ ተከላካይ ነው። እና ለላዕላዩ ፍርድ ቤት የምናቀርበው የይግባኝ ማመልከቻ አዎንታዊ መልስ ካላገኘ፣ ሕገ መንግሥቱ እንዳልተከበረ ለሃገሪቱ ፕሬዚደንት እናሳውቃለን። በሁለተኛ ደረጃ፣ በአሩሻ ፣ ታንዛንያ ለሚገኘው የአፍሪቃ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ተመልካች ፍርድ ቤት ማቅረብ የምንችልባቸው ሌሎች የሕግ አሰራሮች መኖራቸውን በጠበቃችን አማካኝነት እየፈተሽን ነው። ሶስተኛ፣ በሃገሪቱ ሬፈረንደም ቢደረግ፣ ሕዝቡ ድጋፉን እንዳይሰጥ የመቀስቀስ ዘመቻ እንጀምራለን። »
ካጋሜ እአአ በ1994 ዓም የርዋንዳ የጎሳ ጭፍጨፋ ካበቃ ወዲህ ሃገሪቱን ቢመሩም፣ ፕሬዚደንት ሆነው የተመረጡት እአአ በ2000 ዓም ሲሆን፣ 800,000 የቱትሲ ጎሳ እና ለዘብተኛ ሁቱዎች ከተገደሉበት የጎሳ ጭፍጨፋ በኋላ ሃገሪቱን በማረጋጋታቸው ቢወደሱም፣ ማንኛውንም ተቃውሞ ለማፈን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ይከተላሉ በሚል በመብት ተሟጋቾች ይወቀሳሉ።


አርያም ተክሌ
ልደት አበበ

Audios and videos on the topic