ርእደ-መሬት በስምጥ ሸለቆ ከተሞች | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 01.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ርእደ-መሬት በስምጥ ሸለቆ ከተሞች

በኢትዮጵያ በቅርቡ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጦች ተከስተዋል። ወትሮ በተንጣለለበት የእሳት ሐይቅ ላይ የሚንተከተከው የኤርታአሌ ቅልጥ አለት ከረቡዕ ጥር 10 ቀን 2009 ዓም ጀምሮ ሞልቶ መፍሰስ ይዟል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:56

የመሬት መንቀጥቀጥ በኢትዮጵያ

ሁሉም ረጭ ባለበት፤ ድንገት በእኩለ-ሌሊት ነው የተከሰተው። ብርጭቆዎች ከየመደርደሪያቸው እየተውረገረጉ ረግፈዋል፤ ትሪዎች ከየተሰቀሉበት ግድግዳ እየሸሹ ከመሬቱ ጋር ኹካታ ገጥመዋል። ከአልጋቸው ተንከባለው የወደቁም ነበሩ፤ ከዚያ ባለፈ ግን ምን ያኽል ጉዳት እንደደረሰ በውል አይታወቅም፤ የመሬት መንቀጥቀጥ በኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ ከተሞች።  ርእደ-መሬቱ ከኤርታአሌ ቅልጥ አለት ሐይቅ ሙላት አቅራቢያ እስከ ላንጋኖ፤ ከዝዋይ እስከ አዋሳ ታይቷል፤ በሌሎች ከተሞችም ንዝረቱ ተሰምቷል።  ከሰሜን እስከ ደቡብ የተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚገኙበት ታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ውስጡን ሁሌም እንደተናጠ ነው።

በኢትዮጵያ በቅርቡ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጦች ተከስተዋል። እሁድ ኅዳር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በአንኮበር እና ደብረ-ብርሃን መካከል ከአንኮበር በስተ-ደቡብ በሚገኝ ሥፍራ የተከሰተው ርእደ-መሬት መጠኑ 4,6 የሚደርስ ነበር።  የመሬት መንቀጥቀጡ ንዝረት በወቅቱ እስከ አዲስ አበባ ድረስ ሊሰማም ችሎ ነበር። ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ከመሬት መንቀጥቀጡ ባሻገር ሌላም አስገራሚ ክስተት ተፈጥሯል።

 

ወትሮ በተንጣለለበት የእሳት ሐይቅ ላይ የሚንተከተከው የኤርታአሌ ቅልጥ አለት ከረቡዕ ጥር 10 ቀን 2009 ዓም ጀምሮ ሞልቶ መፍሰስ ይዟል።  የርእደ-መሬት ሳይንስ ባለሞያው ዶክተር አታላይ አየለ ወንድም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጂዖፊዚክስ፣ የኅዋ ሳይንስ እና ስነ-ፈለክ ተቋም ዋና ኃላፊ ናቸው። የኤርታአሌ ቅልጥ አለት ሐይቅ ሞልቶ እየፈሰሰ ነው መባሉን መስማታቸውን ተናግረዋል። 

«የኤርታአሌ የማግማ ሐይቅ (የቅልጥ አለቱ ሐይቅ) ሞልቶ  ፈሷል መባሉን ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ሀገር ጎብኚዎች  ለመስማት ችለናል።  እኛ ግን በእኛ ጣቢያዎች መረብ የመዘገብነው  በጣም ትንሽ የቅልጥ አለት እንቅስቃሴ የሚያመላክት መረጃ ነበር። ከዚህ በፊት እንደሚደረገው ብዙ የመሬት እንቅስቃሴ አልመዘገብንም።  እና ይህ ማለት ቅልጥ አለቱ ወደ ላይ ወጥቶ  ምንም እንደ መሬት መንቀጥቀጥ ብዙ እንቅስቃሴ ሳይፈጥር መፍሰስ ችሏል። በአካል ሄደን ለማመሳከር፤ የመስክ ሥራ ለመሥራት አልተቻለም።  ግን እስካሁን ያለን መረጃ ይኼ ነው።  አሁን ምን ደረጃ ላይ እንዳለም አናውቅም።»

በአፋር የኤርታሌ ሐይቅ ውስጥ ሲንፈቀፈቅ ዘመን የፈጀው ቅልጥ አለት ከወትሮው በተለየ መልኩ ከመፍሰሱም ባሻገር በአቅራቢያው የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል። እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂዖፊዚክስ፣ የኅዋ ሳይንስ እና ስነ-ፈለክ ተቋም መረጃ ከሆነ፦ ዓርብ ጥር 19 ቀን 2009 ዓም የተመዘገበው ርእደ-መሬት ልኬት ደግሞ ከቀድሞዎቹ ከፍ ያለ ነው። ንዝረቱም አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች ተሰምቷል። 

«ጃንዋሪ 27 ደግሞ (ጥር 19 ቀን 2009) በእኛ ልኬት መጠኑ ወደ 5.1 [የሚደርስ የመሬት መንቀጥቀጥ ተመዝግቧል]። ግን ብዙ ዓለም አቀፍ ማዕከላትን ስናመላክት መጠኑ ከዚያም በላይ ወደ 5.2  እና 5.3  ይደርሳል ተብሎ የሚገመት የመሬት መንቀጥቀጥ ኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ። ተፈጥሯል።  ከምሽቱ አንድ ሰአት ነው፤ መጥፎ ሰአት ነው።  ብዙ ሰው ጉዳት ሊደርስበት በሚችል መልኩ ነው [የተከሰተው]  ሁሉም ሰው በየቤቱ ሊገባ ስለሚችል ማለት ነው።  እናም በጣም ብዛት ባላቸው የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ  ውስጥ ባሉ ከተሞች  ተሰምቷል፤ አዲስ አበባን ጨምሮ ማለት ነው።»

የአውሮጳ እና ሜድትራኒያን የርዕደ-መሬት ጥናት ማዕከል (European-Mediterranean Seismological Centre) በበኩሉ በሬክተር ስኬል መለኪያ 5.3 እንደተመዘገበ ገልጧል። ተቋሙ ጠንካራ ያለው ርእደ መሬት የተከሰተው ከአዋሳ ሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ 73 ኪሎ ሜትር ርቀት ከምሽቱ 1 ሰአት ከ29 ደቂቃ ላይ እንደነበር ጠቅሷል።

የመሬት መንቀጥቀጥ ሊቆጣጠሩት የማይችሉት የተፈጥሮ አደጋ ነው። እናም ከተሞች ከመገንባታቸው በፊት ገና ሲታቀዱ አንስቶ ርእደ-መሬት ከግንዛቤ የሚገባ ጉዳይ መሆኑን  የከተማ ቅየዳ (አርኪቴክት) ባለሞያ የሆኑት ዶክተር ውብሸት ብርሃኑ አፅንኦት ይሰጣሉ። 

«ገና ሲታቀድ ጀምሮ ነው(planing level) መጀመሪያ መፍትኄ ለመፈለግ ጥረት የሚደረገው። ችግር ሲፈጠር ሰዎች የሚሰባሰቡበት ገላጣ ቦታ በቅርብ ርቀት መገኘት መቻል አለበት።  እንግዲህ ህንጻዎቹ ጋር ከመድረሳችን በፊት  ገና በዕቅድ ደረጃ ማለት ነው መሬት አጠቃቀም ላይ፤ ችግር ሲመጣ  መቋቋም እንዲቻል። ለምሳሌ እሳት ሲኖር ወጥተህ ሌላ ቦታ ላይ ገላጣ ቦታ ላይ እንደምትሄደው ርእደ-መሬትም የዚያን አይነት  በየአካባቢው ያስፈልጋል።»

ሽመልስ ወልደ ሠርባ የተባሉ በዶይቸ ቬለ የአማርኛ ቋንቋ ክፍል የፌስቡክ ተከታታይችን ነዋሪነታቸው የተፋፈጉ ቤቶች በሚበዙባት በመዲናዪቱ አዲስ አበባ አይደለም።  ርእደ-መሬቱ ሲከሰት አዋሳ በሚገኝ እቤት ውስጥ ግድግዳ ተደግፈው ነበር። እንዲህ ነበር ያሉን፦ «...ምሽት ወደ 1፡30 ሀዋሳ ላይ የተከሰተ ሲሆን ግድግዳ ተደግፌ ስለነበር፥ ግርግዳውን ሌላ ሰው ከውስጥ እየገፋው መስሎኝ ነበር፤ ክስተቱን አጠገቤ የነበሩትም ሰዎች አስተውለውታል፡፡ በኔ ግምት ለ5 ሰከንዶች የቆየ ይመስለኛል፡» ብለዋል።  ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም የመሬት መንቀጥቀጡን በስምጥ ሸለቆ ከተሞች ውስጥ መታዘባቸውን ተናግረዋል። 

በኮንስትራክሽን ሚንስትር የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ዋና ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ሥዩም መሥሪያ ቤታቸው ለመሬት መንቀጥቀጥ ብሎ በተለይ እንደማይንቀሳቀስ ገልጠዋል። ሆኖም ግን ርእደ-መሬት በአጠቃላይ የግንባታዎች ደኅንነት ጉዳይ ጋር እንደሚካተት አክለዋል።

Baustelle in Addis Abeba, Äthiopien

 

«የመሬት መንቀጥቀጥን በተለየ መልኩ እንደ አንድ ጉዳይ አንስተን የተንቀሳቀስንበት የለም፤ በተለይ በእኛ በዳይሬክተር ደረጃ። አጠቃላይ በሆነ ግን በግንባታ ዙሪያ የኮንስትራክሽን ሴፍቲ (የግንባት ደኅንነት) በሚለው ነው አሁን ብዙ የምንሠራው። ይሄ ደግሞ የሚመልሰው ርእደ-መሬቱን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ከባቢያዊ ጉዳዮችን እና የሰዎች ደኅንነት፣ ከአካባቢ ደኅንነትን ነው። እና ይሄንን በተመለከተ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በውይይት እየሠራን ነው። ርእደ-መሬትን በተመለከተ [ነገሬ ብለን] ከሌሎች ድርጅቶች ጋር እየሠራን ያለንበት ያን ያህል የምገልጽልህ ትልቅ እንቅስቃሴ የለም።»

ሆኖም ማንኛውም ግንባታ ሲከናወን ሊተገበር የሚገባው ኮድ ወይንም መመሪያ እንዳለ አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል። ተሻሽሎ ቀረበ ያሉት መመሪያም ግንባታ ሲከናወን ከንድፉ አንስቶ የመሬት መንቀጥቀጥን ከግንዛቤ ያስገባ መሆን እንደሚገባው ያመላክታል ብለዋል። መመሪያው ለዩኒቨርሲቲዎች እና ለተለያዩ ተቋማት በመጀመሪያ ዙር መሰራጨቱንም አክለዋል። 

ዶክተር ውብሸት ብርሃኑ «በጥራት ደረጃ ከፍተኛ ነው» ባይባልም በንድፍ ወቅት ከፍተኛ የደኅንነት ቁጥጥር እንዳለ ይናገራሉ። የግንባታ ኮዱን ተከትሎም በጥሩ ደረጃ የሚሠራ ሰው እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።  ሕጉ ቢኖርም አሠራር ላይ ግን ጠበቅ ማለት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

«በቅርብ ጊዜ እየተከሰተ ያለውን ነገር ስናይ በጣም የበለጠ ጥብቅ መሆንን ይፈልጋል።እስካሁን ድረስ ባለው ሁኔታ እንግዲህ ትልልቅ ከተሞቻችን እንደ አዲስ አበባ  አካባቢ ርእደ-መሬት ተከስቶ  የሕንፃዎች የመቋቋም ኃይል አላየንም። እግዚአብሔርም ይከልክልልን ይኼንን መቼም የምንመኘው ነገር አይደለም። ነገር ግን ቀድሞ መጠንቀቅ የግድ ይላል። ህጉ አለ፤ ያንን በጥብቅ  ከተሠራበት  በበቂ ደረጃ  ለመቋቋም የምንችል ነገር አድርጌ ነው የምወስደው።»

የመሬት መንቀጥቀጥ በተለያዩ ጊዜያት ሊመጣ የሚችል እውነታ እንደሆነ በመረዳት ተጠንቅቆ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ዶክተር ውብሸት ተናግረዋል። ህንፃ ደረጃ ከመደረሱ በፊትም በከተማ ደረጃ በአግባቡ ማቀድ ያስፈልጋል ብለዋል። ያም ማለት፦ የህንፃዎችን አቀማመጥ፣ የመሬት አጠቃቀም ሁኔታ፤ ክፍት ቦታ መኖሩ፤ የመንገድ ዲዛይኖች በአጠቃላይ ርእደ-መሬትን ባገናዘበ መልኩ ትኩረት  እንደሚያሻው ገልጠዋል። 

ዶክተር አታላይ አየለ ወንድም በበኩላቸው መሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰት እና ጉዳት ቢደርስ ፈጣን ርዳታ መስጠት የሚችል አካል በብሔራዊ ደረጃ መቋቋም እንዳለበት ጠቁመዋል። በሌሎች ሃገራት የመሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰት ለዜጎች ጥበቃ የሚያደርጉ ጠንካራ(ተቋማት (civil protection frame work) እንዳሉ በመጥቀስ በኢትዮጵያም ይህ ሊኖር እንደሚገባ አመላክተዋል።

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ከተከሰተው በሬክተር ስኬል 3,5 ከተመዘገበው ርእደ መሬት ጋር ተመሳሳይ የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ከአምስት ወራት በፊት ደቡብ ፔሩ ውስጥ  ተከስቶ ቢያንስ የ4 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፎ አልፏል። ከ10 በላይ ሰዎችን አቁስሏል፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ደርምሷል።

በዓለማችን ብርቱ የተሰኘው ርእደ-መሬት የተከሰተው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በግንቦት 22 ቀን 1960 ዓመት ነው። በወቅቱ በደቡብ አሜሪካዋ ቺሊ የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 9.5  ሜጋ ዋት እንደነበር የዩናይትድ ስቴትስ የከርሰ-ምድር ጥናት ተቋም የድረ ገጽ ዘገባ ይገልጣል። የቺሊው ርእደ-መሬት ለ5,700 ሰዎች እልቂት ሰበብ ነበር። ርእደ-መሬቱ 3,000  ሰዎችን ቁስለኛ ሲያደርግ 58,622 ቤቶችን ደረማምሷል። አጠቃላይ ውድመቱ $500 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርስ መገመቱን የአሜሪካው ብሔራዊ የውቅያኖስ እና ከባቢ አየር አስተዳደር ሰነድ ይጠቅሳል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

    

Audios and videos on the topic