ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳቱ በአውሮጳ ምክር ቤት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 26.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳቱ በአውሮጳ ምክር ቤት

አውሮጳ ለዜጎቿ ዋስትና ልትሰጥ ብሎም ዕድል ልታመቻች ይገባል፥ ለእዚያም አዲስ አንቀሳቃሽ ኃይል ያሻታል ሲሉ የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ በአውሮጳ ምክር ቤት ተናግረዋል። የፍራንሲስን ንግግር የምክር ቤቱ አባላት ያጤኑት ይኾን?

አዳራሹ ከአፍ እስከገደፉ ጢም ብሎ ሞልቷል። የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ ልዩ መልዕክት ይዘው መጥተዋልና፥ ሰዉ ሁሉ በጉጉት ነው የሚጠብቃቸው። የአውሮጳ ምክር ቤት አባላት ለጉባኤ ሲሰየሙ እንደጎብኚ ከፎቁ ላይ ቁጭ ብሎ መመልከት ስለሚፈቀድ በርካታ ጎብኚዎች የእንግዳ መቀመጫዎቹን አጣበዋል። «ዛሬ እዚህ ከፊታችሁ የቀረብኩት አዲስ የተስፋ መልዕክት ሰንቄ ነው» አሉ ጳጳሱ። በአውሮጳ ምክር ቤት ታዋቂ እና ጠንካራ ተቺዎች ፊት ቆመው ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳቱ ንግግራቸውን ቀጠሉ።

«አውሮጳውያን በአዲስ ዋስትና የአውሮጳ ኅብረት ተቋማትን እንዲሁም መሠረታዊ የተግባር ዕቅዶችን በወዳጅነት እና በደስታ መቀበል ይችሉ ዘንድ፥ የአውሮጳ ማንነትን የማጠናከሩ ኃላፊነት የተጣለው በእናንተ በሕግ አውጪዎቹ ላይ ነው።»

የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ

የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ

አውሮጳ ብዙውን ጊዜ እንደ «መከነች አያት» ነው የምትታየው። አውሮጳዊ እሴቶች እና የጋራ ብልፅግና መርኅ ወደ ጎን የተገፉ ይመስላል። ብቸኝነትን አጥብቆ የሚሻው አውሮጳዊ ቁጥር ከምንጊዜውም በላይ ጨምሯል። እንደ እኔ እንደ እኔ አሉ ጳጳሱ፥

«እንደ እኔ እንደ እኔ በእዚህ ዘመን የአውሮጳ ፅኑዕ ደዌ ሆኖ የተስፋፋው አንዱ ከአንዱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የማይፈልግበት የብቸኝነት ኑሮ ነው።»

ፍራንሲስ በመቀጠል አውሮጳ፣ ዜጎቿ እና ፖለቲከኞቿ የእያንዳንዱን ሠብዓዊ ፍጡር ክብር ከምንም በላይ ሊያጤኑት ይገባል ሲሉም ጥሪያቸውን አሰምተዋል። ግለኝነት እና ስግብግብነት ያጠቃት አውሮጳን አሰናብተን የኹሉም የሆነች አውሮጳን ማነቃቃት አለብን ብለዋል። ወጣቶች ዕድሉን ሊያገኙ፣ ሥራም ሊሰጣቸው ይገባል በማለት ሲናገሩ፤ ከፍተኛ የጭብጨባ ድጋፍ፥ በተለይ ከግራ ዘመም እና ለማኅበራዊ ሕይወት ትኩረት ከሚሰጡት ሶሻል ዲሞክራት ፖለቲከኞች አግኝተዋል። ስደተኞችን በተመለከተም ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አበክረው አስገንዝበዋል።

የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ

የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ

«አውሮጳ የፈላሲያንን ችግር ልትቆጣጠር የምትችልበት ብቸኛው መንገድ፥ የእራሷን ባህላዊ ማንነት አስተማማኝ አድርጋ፥ የአውሮጳውያንን ደኅንነት የሚያስጠብቁ፣ እንዲሁም የስደተኞችን ዋስትና የሚያረጋግጡ በቂ ሕግጋትን ስትተገብር ነው። አውሮጳ ፥ ለስደተኞቹ ዋነኛ የፍልሰት ሰበብ የሆኑት፣ በስደተኞቹ የትውልድ ሃገራት የሚገኙ ማኅበራዊ እና ውሳጣዊ ግጭቶች መፍትሔ እንዲያገኙ የሚረዳ ተገቢና ቆፍጣና ፖለቲካ ስታራምድ ብቻ ነው ችግሩን የምትፈታው።»

የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን መሪ ፍራንሲስ 750 የምክር ቤት አባላት እና እድምተኞች በተጨናነቁበት አዳራሽ ስደተኞችን በተመለከተ ሲናገሩ ሐዘን ባጠላበት ስሜት ነበር። ይሁንና አማራጭ ለጀርመን፥ በጀርመንኛ ምኅፃሩ AFD የተሰኘው የጀርመን የፖለቲካ ፓርቲ የጳጳሱን ንግግር ተችቷል። አውሮጳ ለስደተኞች ጎርፍ ተጠያቂ አይደለችም፤ በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት መንኮታኮታቸውን በግልፅ መናገር ያሻል ብሎዋል የፖለቲካ ድርጅቱ።

ጳጳሱ ንግግራቸውን በመቀጠል፥ እኛ በየቀኑ የምግብ ቁልሎች ከየገበታችን ወዲያ ስንደፋ፤ በዓለም ዙሪያ በረሀብ የሚሰቃዩትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችንም ልናስባቸው ይገባል ሲሉ በሐዘን ድባብ ተውጠው አሳስበዋል። የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ በአውሮጳ ምክር ቤት ተጋብዘው ንግግር ሲያደርጉ ጥበቃው እጅግ ጥብቅ እንደነበረም ተገልጧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic