«ርቄ እኖራለሁ ብዬ አስቤ አላዉቅም» ብፅዓት ሥዩም | ባህል | DW | 06.09.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

«ርቄ እኖራለሁ ብዬ አስቤ አላዉቅም» ብፅዓት ሥዩም

የሚስረቀረቀዉ ድምፅዋ በመሰንቆ ጋር ሲታጀብ የስንቱን ባህላዊ ሙዚቃ አፍቃሪ ልብ እንዳሸፈተ ለአድማጭ እንተዉ። በተለይ አዲስ አበባ ቂርቆስ አካባቢ ይገኝ በነበረዉ የምሽት ክበቧ ትታወቃለች። ድምፃዊት ብፅዓት ሥዩም!ከአበበ ፈቃደ ጋር በቅብብል በመሰንቆ ታጅበዉ ከሚያዜሙት ሌላ «አደራ ልጄን» እንዲሁም «እንሰባሰብ» የተሰኙት ዜማዎችዋ መለያዋ ናቸዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:18
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
15:18 ደቂቃ

«ርቄ እኖራለሁ ብዬ አስቤ አላዉቅም» ብፅዓት ሥዩም

ብፅዓት ግን ጠፋች ብለን ስናፈላልግ ፤ ምን እስዋ ብቻ፤ እዉቁን አርቲስት ባልዋን ተስፋዬ ገብረሃናንም ነዉ ይዛ የጠፋች አሉ። ሁለቱም አሉ በጤና፤ ከሁለት ልጆቻቸዉ ጋር በደስታ።

«ተወኝ ያገሬ ልጅ ፤ እንደራስ ነዉ ፍርድ፤ ጭምት ያሳብዳል፤ አጅሬ መዉደድ፤ ትቼህ ረስቼህ፤ ሆኜ እንደነገሬ፤ በምን አስታዉሼህ፤ አሞኝ ዋለ ዛሬ» ብፅዓት ስዩም በመሰንቆ ታጅባ በቅብብል ባዜመችዉ በዚህ ዘፈንዋ ታዋቂነትዋ ይበልጥ ያጎላበት፤ ተወዳጅነትን ያጎናፀፋት ነበር። ድምፃዊት ብፅዓት ስዩምን፤ ፈልገን ይኸዉ አዉስትራልያ ሜልበር ከተማ ላይ አገኘንሽ አልናት በስልክ። «አዎ» አለች ብፅዓት፤ «በአዉስትራልያ መኖር ከጀመርኩ የፊታችን 2008 ዓ,ም መስከረም ሲገባ ስምንት ዓመት ይሆነኛል።» ስትል ለቃለ ምልልሱ በመጋበዝዋ በማመሥገን ነበር። ምነዉ ርቆ መኖር መርጠሽ ነዉ? አልናት « አንዳንዴ ሁኔታዎች ያስገድዳሉ። እኔ ዉጭ ሀገርን ከሚጠሉ ሰዎች መካከል አንዷ ነበርኩ፤ የእግዚአብሄር ፈቃድ ሆነና እዚህ እንድቀር ሁኔታዎች አስገደዱኝ እንጂ፤ እኔ ከሀገሪ የመራቅ ችግር የለብኝም በግሌ በራሴ ችግር ምክንያት ከሀገር ወጥቼ እንድኖር ተገድጃለሁ»

ሁለት ትልልቅ ልጆች አድርሰሻል፤ ባለቤትሽ ታዋቂዉ ተዋናይና ደራሲ አርቲስት ተስፋዬ ገብረሃናም አብሮሽ ነዉ፤ እና ኑሮን በአዉስትራልያ እንዴት አገኘሽዉ? «ኑሮ ጥሩ ነዉ ትሮጫለሽ ትደክሚያለሽ ፤ ምንም ዓይነት ማኅበራዊ ኑሮ የለም፤ ሁሉም የራሱን ኑሮ ለማሟላት ስለሚሯሯጥ ማንም ከማንም ጋር አይገናኝም፤ ወዳጄ የምትይዉ ቤተሰብ የምትይዉ ሰዉ የለም። እንደ ኢትዮጵያ ቁጭ ብሎ ከአንቺ ጋር የሚያወራ የሚጫወት ሰዉ እዚህ የለም። ሥራዉ ጥሩ ነዉ ትሰርያለሽ። አዲስ አበባ የሚባል ሪስቶራንት ከፍቼ እኔና ባለቤቴ አብረን እየሰራን ነዉ። መልካም ነዉ። ግን፤ ምንም ሆነ፤ ምንም፤ ማን እንደ ሀገር፤ ሀገር ይናፍቃል።»

ብፅዓት ስዩም ልክ እንደ አዲስ አበባዉ የምሽት ክበብዋ አዉስትራልያ ሜልበርን ያለዉም አዲስ አበባ ሬስቶራንት ሞቅ ደመቅ ያለ ይሆን? «አይደለም» ባይ ናት፣ ቤቱ ባህላዊ ምግብ ይሸጥበታል እንጂ ሙዚቃ አታቀርብም። ኢትዮጵያዊዉ ሁሉ፤ ለሥራ ለኑሮ ስለሚሯሯጥ ጊዜ አግኝቶ ወደ ሬስቶራንት የሚመጣዉ ጥቂት በመሆኑ ሙዚቃ ማቅረቤ ቀርቶአል። በዚህ ምክንያት ከሙዚቃዉ መድረክ ከሙዚቃዉ ዓለም ተለየሽ ማለት ይሆን ታድያ? ላልናት ጥያቄ ብፅዓት ስዩም።

«ቆየሁ! ቆየሁ ከተለያየሁ። መዝፈን እፈልጋለሁ፤ መጫወት እፈልጋለሁ፤ ግን ከማንም ጋር እድሉን አላገኘሁም፤ ከራር፤ መሰንቆ የሚጫወቱ ኢትዮጵያዉያን እዚህ አሉ፤ ግን ሁሉም ለራሱ ኑሮ ሯጭ ስለሆነ፤ የራሱን ኑሮ ስለሚኖር፤ ልምድ የምናደርግበት አንድ የጋራ ጊዜን ማግኘት አልቻልንም። በዚህ ላይ እዚህ ሀገር መድረክ ላይ ልስራ ብለሽ ስታስቢ ሊከፍሉሽ ያሰቡትን ገንዘብ መጠን ስትሰሚ በጣም አነስተኛ በጣም የሚያስቅ ዓይነት ነዉ፤ በዚህ ምክንያት ነዉ መዝፈን ያቆምኩት።»
ስለዚህ የማስደምጣችሁ ምንም ዓይነት ዘፈን የለኝም በቅርቡ አትጠብቁኝ እያልሽን ይሆን ያለሸዉ?

«እኔ አሁን ልቤ ተነስቷል፤ ግጥም ዜማ መሰብሰብ ጀምሬአለሁ፤ መዝፈን የምጀምረዉ ግን አዲስ አበባ ላይ ነዉ። ወይም እንደድሮዬ፤ አዲስ አበባ ዋናዉ መቀመጫዬ ይሆንና እየዞርኩ ሙዚቃዬን ማሳየት ነዉ የምፈልገዉ፤ እግዚአብሄር ዕድሜና ጤናዉን ከሰጠኝ። ጨርሴ ሥራዉን አቁሜያለሁ ማለት አይደለም። የሚመቻች ነገር ሳገኝ ሙዚቃዬ የማሳየዉም ሆነ የምዘፍነዉ በደስታ ነዉ። አሁን በጣም ዝም ያለ የተረጋጋ ኑሮ ላይ ነኝ፤ ከተስፍሽ ጋር ትያትር በመድረክ ላይ እጫወታለሁ፤ በቤተ-ክርስትያን አገለግላለሁ፤ እዘምራለሁ...»

ድምፃዊት ብፅዓት ሥዩም ምኝዎትዋ እንዲሳካ እየተመኘን ሙሉ ቃለ-ምልልሱን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic